
ደብረታቦር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከ127 ዓመታት በፊት የካቲት 23/1888 ዓ.ም በአውሮፓ ገናና የነበረውን ጣሊያንን በሀገር ፍቅር፣ በአንድነትና በጀግንነት ወኔ ድባቅ በመምታት የጥቁር ህዝቦች ነጻነትና አሸናፊነት የተበሰረበት ቀን ነው፡፡
ይህ ታላቅ የድል በዓል በእቴጌ ጣይቱ የትውልድ ሀገር በደብረታቦር ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
አውሮፓውያን አልሰለጠነም ያሉትን አፍሪካን ተቀራምተው ቅኝ በመግዛትና ጥሬ ሀብትና ጉልበትን ለመዝረፍ ባደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያን ባትጋሩኝ ያለው ጣሊያን እንደቋመጠው ሳይኾን የረገጣት የኢትዮጵያ ምድር ረመጥ ኾናበት በሽንፈት ተባሯል፡፡
ከሀገር ውስጥ አሥተዳደር እስከ ውጪ ዲፕሎማሲ የተካኑት የዚያኔው ንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ ጣሊያን ዕለት ከዕለት እንደ ፍልፈል አፈር እየቆፈረና ግዛት እየተጋፋ ቢያስቸግራቸው ከድርጊቱ እንዲታቀብ በሽማግሌም በውልም መክረውት ስላልተመለሰ በመጣበት መንገድ ለማስተናገድ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት አውጀው ዓድዋ ላይ አስተናገዱት፡፡ በእብሪትና በንቀት ለመጣባቸው ጣሊያን የጋለ አሎሎ ኾነው ጠበቁት፡፡ የእምዬ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱም በሀገር አሥተዳደር የተካኑ ብቻ ሳይኾኑ በጦርነትም ጊዜ መኳንንቱንና ወይዛዝርቱን አቀናጅተው በማዝመት ታሪክ ይዘክራቸዋል፡፡
የጦር መላ በመዘየድና ጣሊያን ከናቃት ኢትዮጵያ ምድር ላይ ውኃ! ውኃ ብሎ ውኃ ኾኖ እንዲቀር ያደረጉና የዓድዋ ድል መሐንዲስ ናቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል፡፡
የዘንድሮው የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል እቴጌ ጣይቱ ፊደል ከሥነ ምግባር፣ ትህትናና ሀገር አሥተዳደር ባጠኑበት ትውልድ ሀገራቸው በጌምድርም በድምቀት ተከብሯል፡፡
መላ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በዘርና በጎሳ ሳይለያዩ ከአራቱም አቅጣጫ ተሰባስበው በንጉሳቸው ሥር ኾነውና ለሀገራቸው ክብር መስዋእትነት በመክፈል ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ነስተው ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የድል ብስራት ያሰራጩበትን በዓል በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡
በአማራ ልዩ ኀይል የ1ኛ ሻለቃ፣ 1ኛ ብርጌድ፣ 3ኛ ሻምበል፣ 1ኛ የመቶ አባል ረዳት ሳጅን አምላክ ጌታቸው ቀደምት አባቶቻችን ተክለውልን ያለፉትን አኩሪ ታሪክ ጠብቀን እኛም ሌላ ታሪክ እየሠራን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
ረዳት ሳጅን አምላክ አክላም እንደ እቴጌ ጣይቱ ሁሉ እኔም ለሀገሬ በትጋትና በታታሪነት ሠርቼ ለማለፍ እሞክራለሁ፣ ሴት እህቶቼም ጠንካራ ኾነው ማለፍ አለባቸው ብላለች፡፡
የደብረታቦር ነዋሪ ወይዘሮ አዱኛ ታረቀኝ በበኩላቸው የዛሬው ትውልድ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስረክቡንን ጀግንነትና ወኔ ጠብቀን ለልጆቻችን ማስረከብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ታሪክን ለማሳሳት የሚሞክሩ አንዳንድ ኀይሎች እንደሚሉት ሳይሆን አጼ ምኒልክ የሀገር አንድነትንና ነጻነትን አስጠብቀው የቆዩ ጀግና መሪ፤ ጀግና አባት መኾናቸውንም አስረግጠው ገልጸዋል፡፡
ቀደምት ጀግኖች አርበኞች በተዘከሩበት የዓድዋ በዓል ንግግር ያደረጉት የደቡብ ጎንደር ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ሊቀመንበር አቶ ያዛቸው አሉላ የዓድዋ ድል ለጭቁን የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ድፍረትን ያስተማረ ታላቅ ገድል መኾኑን አስታውሰዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ገድል ለመድገም ለሀገራችን አንድነት ዳር ድንበር፣ መከበርና ለነጻነቱ ታጋይ እንዲኾን አሳስበዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቸ ሁሉ የሀገር ፍቅርን፣ ጀግንነትንና አንድነትን በመመሥረት ኢትዮጵያን ማጽናት ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ናቸው፡፡ ምክትል ከንቲባው አክለውም የእቴጌ ጣይቱ የትውልድና ዕድገት ቦታ በኾነው በጌምድር – ደብረታቦር ሐውልታቸውን በማቆም ትውልዱ ከብልህነትና ጀግንነታቸው እንዲማርና እንዲዘክራቸው እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በድል በዓሉ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የደቡብ ጎንደርና የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ባለስልጣናት፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶ የተገኙ ሲኾን ለእቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ሐውልት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ በጣይቱ አደባባይ ተቀምጧል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck