
ወረኢሉ: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ የድል በዓል በታሪካዊቷ ወረኢሉ በድምቀት ተከብሯል። በክብረ በዓሉ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኅሊና መብራቱን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል። በዓሉ የተከበረው የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትም ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ ነው።
የወረኢሉ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እሸቱ ታረቀኝ ወረኢሉ ንጉሥ ያረፈባት የዓድዋ ጦርነት ስልት የተቀየሰባት ታሪካዊ ሠፍራ ናት ብለዋል። የጥቅምት እኩሌታ እና የዓድዋ ድል በዓል በወረኢሉ እንዲከበር እየሠሩ መኾናቸውንም ገልፀዋል። በዓሉ በወረኢሉ በልዩ ሁኔታ እንዲከበር የሚመለከታቸው አካላት እንዲደግፏቸውም ጠይቀዋል።
ዓድዋ በዓለም ላይ ከገነኑ ታሪካዊ ሁነቶች አንደኛው መኾኑንም ገልፀዋል። አባቶች በድል አድራጊነት የሚታወቁትን ሮማውያን ድል ያደረጉ ጀግኖች መኾናቸውንም ተናግረዋል። እምዬ ምኒልክ ታላላቅ ታሪኮችን ሠርተው ያለፉ ታላቅ መሪ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ምኒልክ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር እና ኢትዮጵያ እንድትከበር ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በዓድዋ ጦርነት ጀግኖች በአንድነት የተሰባሰቡት ለሀገር ፍቅርና ክብር እንጂ የግል ጥቅም ኑሯቸው አይደለም ብለዋል። ከቀደሙት አባቶች አንድነትን መማር፤ ከራስ ክብር ይልቅ የሀገርን ክብር ማስቀደም ይገባልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃናለች ያሉት ከንቲባው ኢትዮጵያን አናጥብባት፣ የወላድ መካንም አናደርጋትምም ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ዓድዋ የነጮችን ፈላጭ ቆራጭነት የለወጠ ታሪክ ነው ብለዋል። ዓድዋ የነጭን የበላይነት የቀየረ የዓለምን አካሄድና አስተሳሰብ እያስተካከለ መኾኑንም አንስተዋል። ዓድዋ በነጭና በጥቁር ሕዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት እያስተካከለ የበላይ የሚባል እንደሌለ የታየበት ነውም ብለዋል።
ዓድዋ ነፃነታቸውን ተገፍፈው የኖሩ ሀገራት ትምህርት የወሰዱበት የአልደፈርም ባይነት ድል መኾኑንም ገልጸዋል። ዓድዋ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም ያሉት አስተዳዳሪው በዓድዋ ተስፋ፣ ጥበብ እና ፈጣሪን ማመን የሚሉ አንኳር ጉዳዮች እንደነበሩበት ተናግረዋል። ከምኒልክ አዋጅ ተስፋን ብልሃትን እና ችግርን አልፎ መሄድን እንማራለንም ብለዋል። ችግርን ለማለፍ ከችግር ባለይ የኾነ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ ከዓድዋ እንማራለን ነው ያሉት። በዓድዋ የታየውን ድል ዛሬ ላይ በልማት እና በሌሎች ትግሎች መድገም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከችግር በላይ ኾኖ ሀገርን መምራት እንደሚቻልና እንደሚያሰፈልግ ከዓድዋ እንማራለንም ብለዋል። ወሎ ከዓድዋ ጋር ታላቅ ቁርኝት ያለው መኾኑንም ተናግረዋል። የክተት አዋጅ የሠሙ ጀግኖች በተሰባሰቡበት ወረኢሉ እና ውል የተፈረመባት ውጫሌ አሻራዎች ኾነው እንዳሉም ገልፀዋል። ቃልህን ካፈረስክ ግጭት ይመጣል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ቃልን ማክበር እና ውልን መጠበቅ ተስማምቶ ለመኖር ያግዛልም ብለዋል። ለዘላቂ ሰላም ቃልን ማክበር ይገባል ነው ያሉት።
የዓድዋ ድል ባለቤቶች በመኾናችን ኩራትና ክብር ሊሰማን ይገባልም ብለዋል። ወሎ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር የእውነት መስዋእትነት የሚከፍል መኾኑንም ተናግረዋል። የንጉሥ ሚካኤል ሀገር ወሎ በዓድዋ ጦርነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው፣ ለሀገር ታጋይና ለኢትዮጵያ ክብር ዘብ የሚቆም ነውም ብለዋል። አሁን ላይ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በጥንካሬ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። በድህነት መኖርና በጦርነት ድል ካደረግናቸው ሀገራት መለመን የአባቶችን ታሪክ ማርከስ ይኾናልም ብለዋል።
ጠላቶች እርስ በእርስ እንድንጠላለፍ፣ መሪዎችን እንዳናከብር እያደረገኑን ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ችግሮችን ለመፍታት ውይይት እና ምክክር ያስፈልጋልም ብለዋል። መሪን ማክበር ከዓድዋና ከእምዬ ምኒልክ መማር እንደሚገባም ገልጸዋል። ዓድዋ የሚፀናውና ክብሩ የሚገለፀው ዛሬ ባለው ትውልድ ሥራና አንድነት ነውም ብለዋል። በአንድነት በመኾን ዓድዋን ለማፅናት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከዓድዋ ጋር የተያያዙ ታሪኮች ተጠብቀው እንዲኖሩ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኅሊና መብራቱ ወሎ ሰውን በሰውነቱ የሚያከብር ደግ ሕዝብ ያለበት መኾኑን ተናግረዋል። የዓድዋ አይነትን ድል የምናገኘው ሰዎችን በሰውነታቸው ማክበር ስንችል ነውም ብለዋል። ወሎዬዎች ሰውን በሰውነቱ የማክበር እሴት ባለቤት በመኾናችሁ ልትኮሩ ይገባልም ነው ያሉት። ሰውን በሰውነቱ ማክበር ሲቻል ከችግሮቻችን መውጣትና መሻገር ይቻላልም ነው ያሉት።
የዓድዋ በዓል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላው ጥቁሮች በዓል መኾኑን ገልፀዋል። ታላቁ የዓድዋ ድል ዘመናዊነት ኢትዮጵያን ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጋር ያዋደደ፣ የአባቶቻችን ጀግንነት፣ የሀገር ፍቅርን ያሳየ የነፃነት፣ የአይበገሬነት፣ የሕዝቦች አንድነት ሕያው ማሳያ ነውም ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትከበር ያደረገ ታላቅ በዓል መኾኑንም ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እርሾ ነውም ብለዋል። ዓድዋ ለሌሎች ሀገራት የነፃነት ትግል ተምሳሌት መኾኑንም ተናግረዋል። የጥቁር ሕዝቦችን ለነፃነት ያነሳሳ፣ ኢትዮጵያዊነት በዓለም አቀፍ አደባባይ እንዲቀነቀን ያስቻለ የድል በዓል ነውም ብለዋል። የዓድዋ የድል በዓል ለአፍሪካ ነፃነት መሠረት የጣለና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንድትኾን ያስቻለ መኾኑንም አንስተዋል።
ዓድዋ የሀገር ፍቅርና ለመሪ የሚሰጥ ክብር ያሳየ እንደኾነም ተናግረዋል። ጀግኖች አባቶች በባዶ እግራቸው ታላቅ ጀግንነት ያሳዩበትና ጠላትን ያንበረከኩበት መኾኑንም አንስተዋል። ፈተናዎችን የማለፍ ጥበብ ከዓድዋ መማር እንደሚገባም ተናግረዋል። የአባቶቻችን የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ትብብር፣ የነፃነት ጥግና ፅናት ተጋብቶብን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ዓድዋ ያበረከተውን አጋጣሚ መጠቀም አለብን ብለዋል። የዓድዋ ታሪክ እና ከታሪኩ ጋር የተያያዙ ቦታዎች ታሪክ ጎልተው እንዲወጡ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck