
ደብረ ማርቆስ :የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በደብረማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ተከብሯል። በበዓሉ ላይም የፈረስ ትርዒት ፣ ግጥሞች እና ድራማዎች ቀርበዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ የጸጥታ አካላት እንዲሁም የዞንና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ስለሺ ተመስገን የዓድዋ ድል የዓለምን የፖለቲካ አቅጣጫ የቀየረ ፤ የነጮችን የዘር የበላይነት ትምክህትና ዕብሪት ልክ ያስገባ ፤ የጥቁሮች መመኪያ ፤ የእኩልነት ማረጋገጫ ማህተም ልዩ ታሪክ ያለው በዓል ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቀን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫችን ፣የጀግንነት ውርሳችን፣ የመቻቻል ተምሳሌታችን፣ የሀገር ፍቅር ዓርማችን ፣ የእምነት ጽናታችን ፣የነገ የአሸናፊነት ተስፋችን ነው። ከዚህ ታሪካዊ በዓልም መሪዎች የሚኒልክን የአመራር ጥበብና ጀግንነት ፤ አዛኝነትና ቅንነት ትምህርት ሊወስዱበት ይገባል ብለዋል ምክትል ከንቲባው።
ታሪክ ካለፈው የምንማርበት፣ አኹን ላይ ኾነን አዲስ ታሪክ የምንሰራበት ለወደፊት ታሪክ ለመስራት ወኔ የምንሰንቅበት በመኾኑ አዲሱ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ በመተረክ ብቻ የሚኖር ሳይሆን ታሪካቸውን በበለጠ ድልና ጀግንነት አሻራውን የሚያሳርፍበት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
ወጣቶች ከዛሬዋ የድል ቀን ትምህርት በመውሰድ ያላቸውን እምቅ እውቀትና ጉልበት በጥበብና በማስተዋል በመጠቀም ሀገራዊ አንድነትን የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ምክትል ከንቲባው።
የበዓሉ ታዳሚዎችም በዓሉ ከኹልጊዜው በደመቀ መልኩ መከበሩን ጠቁመው የአሁኑ ትውልድ ከመለያየት ወጥቶ በአንድነት፣ በመካባበርና በመደጋገፍ ታሪኩን ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ ፦አማረ ሊቁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck