
“ዓድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ምልክት ፣የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ነው።” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር)
ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ዓድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ምልክት ፣የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ነው ብለዋል።
የዓድዋ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃለፊ ዶክተር አየለ አናውጤ የዓድዋ ድል በሚሊዮኖች ልብ በደማቁ የታተመ፣ የታላቅ ሕዝቦች የትግል ውጤት ነው። የኅልውና እና የነጻነት ጥያቄ በአንድ ቀን የተፈጸመበት ሰብዓዊ ክብር ከፍ ያለበት ኅያው ገድል ነው ብለዋል።
ዓድዋ ቅድመ አበው በአንገዛም ፣ በአንረታም ባይነት በጋለ ወኔ እና በእውነተኛ የሀገር ፍቅር፤ የሰዎች ልበ ሙሉነት በትውልድ ቅብብሎሽ በደም እና በአጥንት ተዋርሰን እንድንኖር ያደረገ ክስተት ነው ። ዓድዋ ጽኑ መሰላል እና የማይነቃነቅ ምሰሶም ነው ብለዋል።
ዛሬ ከስብራታችን የምናገግምበት ምርኩዛችን፤ ታላቅ አቅም እና ዕውቀት ኾኖን ነገን አሻግረን የምናማትርበት ኢኮኖሚያችንን የምናዳብርበት አቅም እና እውነት ነው ብለዋል።
ዓድዋ የኢትዮጵያዊያን የጽናት ምሰሶ ፣የማይናወጥ ባሕር የማይነጥፍ ፍቅር፤ የማይቆረጥ የተገመደ የጥቁር አልገዛም ባይነት የታየበት፡ መሠረተ ጽኑ ክስተት ነው ብለዋል ዶክተር አየለ።
ዓድዋ ጸሐፍት ብዙ ቢሉለትም ከጀግኖቻችን ደማቅ ተጋድሎ በላይ ማንነታችንን ለዓለም የምናስተዋውቅበት፤ ዓድዋ ኪነ ጥበባችን፣ ዓድዋ ቅርሳችን፣ ያለፈ ታሪካችን በልኩ የሚዘከርበት ፣ በማይደበዝዝ ቀለም ጽፈን ለትውልድ የምናስተላልፈው ኅያው ምስክር፤ የጥቁር ሕዝቦች አንደበት ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ የቁርጥ ቀን ልጆች መስዋእትነት የከፈሉበት በዓል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck