የሴቶች ተጋድሎ በዓድዋ ዘመቻ!

126

ባሕር ዳር:የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓድዋ ጦርነት የሴቶችን ሚና ለመዘከር ሲታሰብ ቀድመው ወደአዕምሮ የሚመጡት እቴጌ ጣይቱ ናቸው።
እቴጌ ጣይቱ በዓድዋ ድል አንጸባራቂ ሚና ተጫውተዋል። የእቴጌ ጣይቱ የዓድዋ ገድል የሚጀምረው ለዓድዋ ጦርነት መነሻ ከሆነው ከውጫሌ ውል ስምምነት ነው፡፡

ኮንት አንቶኔሊ የውጫሌ ውል እርሱ እንደፈለገው እንደማይሆን እና 17ኛዋ አንቀጽ እንደተሰረዘ በሰማ ጊዜ
እቴጌ ጣይቱ እና አጤ ምኒልክ በተቀመጡበት እልፍኝ ገብቶ የ 17ተኛዉ ክፍል ተሰርዞአል ተብሎ ተጻፈ በማለት አጤ ሚኒልክን ይጠይቃል ፤ አጤ ሚኒልክም አንተና እኔ ተነጋግረን አንተ ወደህና ፈቅደህ የተጻፈ ቃል ነዉ ሌላ አልታከለበትም ባስተርጓሚህ የተናገርከዉ ነዉ አሉት።

ኮንት አንቶኔሊ እንዳልተሳካለት አውቆ የውሉን ወረቀት ቀዳደውና ጦርነቱ እንደማይቀር ተናግሮ ከእልፍኝ እየወጣ እያለ እቴጌ ጣይቱ ከት ብለዉ በመሳቅ” የዛሬ ሳምንት አድርገው በዚህ የሚደነግጥ የለም ሂድ የፎከርክበትን አድርግ … ወታደር ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነዉ እንጅ ሞት አይደለም አሁንም ሂድ አይምሽብህ፤ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገዉ፤ እኛም ከዚሁ እንቆይኸለን ያንተ ፍላጎት ኢትዮጵያ በሌላ መንግሥት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መኾኗን ለማሳወቅ ነው፤ ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም

ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” በማለት ፈጽሞ በሀገራቸው እንደማይደራደሩ መናገራቸውን ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

ለዓድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረውን የጣልያኖች የተሳሳተ አካሄድና መሰሪነት ቀድመው የተረዱትና በባለቤታቸው በአጼ ምኒልክ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደሩት እቴጌይቱ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ።

ለኢትዮጵያውያን ድል ማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተው የጠላትን የውሃ ምንጭ ማቋረጥ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን የውጊያ ስልት ብልሀት ያሳየ ድርጊትም ነበር።

አጤ ምኒልክ በተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ እንደተገለጸው እቴጌ ጣይቱ በዓድዋ ዘመቻ ላይ የራሳቸውን ጦር እየመሩ ዘምተዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት በስራቸው ያስተባብሯቸው የነበሩ በርካታ ሴቶችም፤ በጦርነቱ ጉዞ ላይ ሆነ በጦርነት ጊዜ ለሠራዊቱ በየቀኑ ምጣድ እየጣዱ እንጀራ ይጋግራሉ ፣ ጠላ ይጠምቃሉ ጠጅ ይጥላሉ ፣ ወጥ ይሰራሉ ፣ ግብር ያበላሉ ፣ ቁስለኛ
ያክማሉ ፣ በፉከራና በእልልታ ተዋጊውን ያበረታታሉ ከዛ ባለፈም ጣልያኖች ባረፉበት አካባቢ በመሔድ ይሰልሉና መረጃ ያቀብሉ ነበር።

በዓድዋው ዘመቻ ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እንደዘመቱ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሠራዊቱ በእግሩ ብዙ መንገድ ይጓዛል አቀበት ቁልቁለት ይወጣል ይወርዳል። ጠንክሮ እንዲዋጋም ስንቅና ትጥቅ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። በእቴጌይቱ የሚመራው በርካታ የሴት ሰራዊት የስንቁን ዝግጅት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በወኔ መወጣቱን ፀሐፌ ትዕዘዝ ገብረስላሴ ሁኔታውን እንዲህ ይገልጹታል “አጼ ሚኒልክ በአዳራሽ እቴጌ ጣይቱ ባለሟሎችዋን በእልፍኝ ወይዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል ይዘምታሉ። ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ ስለምንድን ነው ያልክ እንደሆን ይህን ታሪክ መመልከት ነው። በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር በአራት ድንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር ግብሩ ይጎድል ይመስልሃል” ብለዋል።

ከሸዋ እና ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የተመመው ሠራዊት በጥቅምት ወርኢሉ ከተህ ላግኝህ በተባለው መሰረት ከተተ። ከጥቅምት ጀምሮ እሰከ የካቲት የዓድዋ ድል ባሉት አምስት ወራትና ከድሉ በኋላም ተዋጊ ሰልፈኛው እስኪመለስ ድረስ ስንቁን፣ ለስንቁ ማዘጋጃ የሚሆን ቁሳቁሱን፣ የጠጅና የጠላ በርሜሉን፣ የኩሽና ዕቃውን ..ኹሉ ከአህያና ከአጋሰስ የተረፈውን ተሸክመው የሚጓዙት ሴቶች ነበሩ።

እህል ፈጭተው ፣ሊጥ አቡክተው፣ ምጣድ ጥደው ፣እንጀራ ጋግረው ፣ ወጥ ሰርተው ጠላ ጠምቀው፣ ጠጅ ጥለው የሚመግቡትም እንዲኹ እነሱ ነበሩ።

ሰራዊቱ በምድብ በምድብ እየሆነ በገፍ ይጓዝና የደረሰበት ቦታ ለምግብ ያርፋል ፤ ሴቶቹ ዕቃ ተሸክመው አብረው ቢጓዙም ቢደክሙም የሠፈረውን ሰራዊት የመመገብ ሃላፊነት እነሱ ትከሻ ላይ የወደቀ በመኾኑ ረፍት የላቸውም። በእሾህ በጋሬጣ እግሩ የተጎዳውን አጥበው ያክማሉ። ለዛሬ አብልተው አጠጥተው ለነገው ደግሞ ያዘጋጃሉ ይፈጫሉ፣ ያቦካሉ፣ ይጋግራሉ።

በዓድዋ ጦርነት ሴቶች ሰራዊቱን በማጀገን ወኔኛ ሆኖ እንዲዋጋ ሚናቸው የጎላ እንደነበር የዳግማዊ ምኒልክ ጸሐፌ ትእዛዝ የነበሩት፤ ንቡረ ዕድ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋዊ ጽፈዋል ፤ አዝማሪ ጣዲቄ ተጠቃሽ የሴት አርበኛ እንደነበረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። አዝማሪዋ በሠላሙ ጊዜ ንጉሡን እና ንግሥቷን የምታዝናና፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ሠራዊቱን በሽለላና ቀረርቶ የምታበረታታ ነበረች። ይህም ሴቶች ሰራዊቱን በዘፈን ግጥም ፣በእልልታ አጀግነው በወኔ እንዲዋጋ አድርገዋል።
በዓድዋው ጦርነት የኢትዮጵያ ሴቶች ሚናቸው ከምግብ ማብሰል፣ ልብስና እግር ከማጠብ፣ ሰራዊቱን ከማጀገን ያለፈ ነው ። ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ አጼ ሚኒሊክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ሴቶች በጦርነት መካከል ጥይት አቀብለዋል ፤ቁስለኛ አግልለዋል ፤ በባሕላዊ ህክምና ቁስለኞችን አክመዋል፤ በጦርነቱ የተሰውትን ጀግኖች አፈር አልብሰዋል፤ ከዚህ ባለፈ በጦርነቱም ተሳትፈዋል ብለዋል።

በአዋጊነት ጦር መርተው፣ መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዘው አዋግተዋል። በዘመቻው ወቅት ሚናቸው ከፍተኛ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪካቸው ጎልቶ ባይጻፍም ፤ ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ ፤ በውጊያ ከደጀንነት እስከ አዋጊነት ከሠራዊቱ ሳይነጠሉ ረጅሙን የውጊያ ወራት አሳልፈዋል።

ዘጋቢ ፦ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous article127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በደሴ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
Next article“ዓድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ምልክት ፣የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ነው።” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር)