የዓድዋ ድል በዓል በመሰቀል ዓደባባይ በድምቀት እየተከበረ ነው።

65

የዓድዋ ድል በዓል በመሰቀል ዓደባባይ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 127ኛው የዓድዋ የድል በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የእንኳን አደረሳችሁና የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ደማቸውን አፍስሰው፣አጥንታቸውን ከስክሰው ፣በመስዋእት ሀገር ያጸኑ ጥንት የኢትዮጵያ ጀግኖች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡፡

ላለፉት ጊዚያት በዓሉን በዚህ መልኩ በድምቀት ለማክበር መንግሥታዊ ፍላጎት እንዳልነበር የተናገሩት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በዓሉ ዛሬ የተከበረበትን ኹኔታ አመስግነዋል፡፡

ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኀበር የድል ታሪኮችን ሲያከብር የሚያሳስበው ጉዳይ፤ እንዲህ አይነቱ ታላቅ በዓል በመንግሥት ደረጃ እንዴት በድምቀት ይከበር የሚለው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ 127ኛው የዓድዋ በዓልን መከላከያ ያከበረበትን ኹኔታ ሲገልጹም “የድሉ በዓል ወደ ቤቱ ገብቷል፣በባለቤቶቹ በድምቀት ተከብሯል፣ደስም ብሎናል ነው ያሉት፡፡” በዓሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኹሉ የድል በዓል ነውና በድምቀት ማክበር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

የዓድዋ ድል ለመላው ዓለም የይቻላል መንፈስን ያወረሰ ነው፣የምናከብረው የነጻነት በዓል ሳይኾን የድል በዓል መኾኑን ተገንዝቦ መንግሥት ለምናከብረው የድል ታሪክ ድምቀት አካል በመኾኑ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

የዛሬው በዓል በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የማኀበሩ አባላት በተገኙበት እየተከበረ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የዓድዋ በዓል እየተከበረ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት እየተከበረ በሚገኘው የዓድዋ ድል አከባበር ሥነሥርዓት ላይ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ባስተላለፉት መልእክት ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያሳረፉበት የዓድዋ ድል በዓል ታሪካዊ ይዘቱን እና ሕዝባዊ እሴቱን ጠብቆ መከበር አለበት ብለዋል።

የዓድዋ ድል ምስጢር ከተለያዩ ሕዝቦች የተገኙ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ባሕላዊ የጦር ስልቶች፣ የሕዝቡ አንድነት እና ጀግንነት መኾናቸውን ጠቅሰዋል ሚኒስትሩ፡፡

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ዝግጅትም የበዓሉ አዘጋጅ ከኾነው ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በጋር መስራቱን ተናግረዋል፡፡ የዓድዋ የድል ታሪክ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአድዋ ድል በውጭ ጋዜጦች!
Next article127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በደሴ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።