“የካቲት 23 ተጨንቆ የነበረዉ የዓድዋ መሬት”

160

ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አቤት ያን ጊዜ ዓድዋ ተጨነቀች፣ በተኩስ ድምፅ ተናጠች፣ አቧራ አጠመቃት፣ የደም አላባ ፈሰሰባት፣ አጥንት ተከሰከሰባት፣ለክብር ያለ ጀግና ወደቀባት፣ ልበ ሙሉ ተዋጊ በሞት መካከል እየተመላለሰ የልቡን ሠራባት፣ የጠላትን አንገት እየለየ በጎራዴ መታባት፣ ደረቱን እየመረጠ በጦር ወጋባት። ጉልበት ጉልበቱን እየለየ ሰበረባት።

አይዞህ እያለ የሚያዋጋው፣ የዳኛው አሽከር እያለ የሚዋጋው፣ ተመትቶ ሲወድቅ የሚያቃስተው፣ እልል እያለ ወኔ የሚሰጠው፣ እየፎከረና እየሸሸለ ወደ ጠላት ሠፈር ገስግሶ የሚገባው ዓድዋን ከዳር ዳር ወጠራት። ዓድዋ ሞትን የናቁ ጀግኖች ፣ ሞትን የፈሩ ድንጉጦች ሲመላለሱባት፣ ጀግኖች ጠላት ሲያልከሰክሱባት አየች፣ ተመለከተች።

አቧራው ጨሰ፣ ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ፣ አጥንት እንደ አገዳ ተልከሰከሰ፣ ምድር ቁና ኾነች፣ የምትኾነውን አጣች። ዓድዋ ከባዱን ድምፅ ሰማች። ኃያሉን ጦርነት አየች። ተመትቶ የሚወድቀውን ታዘበች።

እንደነብር የፈጠኑ፣ እንደ አንበሳ የጀገኑ ጀግኖች፣ ሞትን ንቀው፣፣ኢትዮጵያን አስቀድመው፣ ሠንደቋን ከፍ አድርገው የጠላትን ጉሮሮ አነቁት፣በጦር እየወጉ፣ በጎራዴ እየሸለቱ ጣሉት፣ በሀገራቸው ምድር አስጨነቁት፣ መውጫ መግቢያ አሳጡት፣ ወደ ፊት የሚመጣውን ሲያሻቸው ደረቱን፣ ሲፈልጉ ግንባሩን፣ የሚሮጠውን አባረው ጀርባውን፣ እንዲያም ሲል እግሩን እየመቱ አስቀሩት፣ ጠላት ከአንበሳ ጋር ገጥሟልና በክንዳቸው ብርታት አደቀቁት። የጠላትን ጦር እንኳን የኢትዮጵያ ጀግኖች ምድሩ ተዋጋው፣ መውጫ መግቢያ እያሳጣ ከጀግኖች እጅ ላይ ጣለው።

የጣልያን ወታደሮች መውጫ መግቢያው ጠፋባቸው፣ እንኳን ወደ ፊት መገስገሻው ወደ ኋላ መመለሻው አቃታቸው። የመጡባትን ቀን ረገሟት፣ የተወለዱባትን እለት ጠሏት፣ ሞት በፊት በኋላቸው፣ በግራ በቀኛቸው፣ ከቦ አስጨነቃቸው፣ እሳት በኾኑ ጀግኖች በዙሪያ ገባው በእሳት ተከበው፣ ጦር እየወጋች፣ ጎራዴ እየሸለታቸው ጨነቃቸው፣፣ ጠበባቸው። ሮምን ዳግም እንደማያዩዋት፣ የጣልያን ምድር ዳግም እንደማይረግጧት፣ የኢትዮጵያ አፈር እንደሚበላቸው፣ ዘመዶቻቸውን እንደማያገኟቸው፣ የጀግኖች ጎራዴ በአንገታው ላይ እንደሚውልባቸው ባወቁ ጊዜ ነብሳቸው ተጨነቀች፣ ልባቸው በፍርሃት ቆፈን ታሠረች።

“የካቲት ሃያ ሦስት ተጨንቆ ነበረ የዓድዋ መሬት” እንደተባለ የካቲት ሃያ ሦስት የዓድዋ መሬት ተጨንቃ ነበር። በከባድ ጦርነት ተከባ ነበር። ጀግና እየፎከረ ጠላትን እየመታባት፣ አባረህ በለው እያለ እየጣለባት፣ ፈሪ እግር አውጭኝ እየሮጠባት ተጨንቃ ነበር። መቼም ጀግና የዋለባት፣ የልቡን የሠራባት ምድር ትጨነቃለችና።

የጣልያን ጦር ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ተማምኗል። በአምባላጌ እና በመቀሌ የደረሰበትን ሽንፈት በዓድዋ ሰማይ ሥር ሊክስ፣ ክብሩን እና ዝናውን ሊያስመልስ ቆርጧል። ሁልጊዜም እኛ አሸናፊዎች ነን ብሏል። ለአለቆቹ የድል ብሥራት ወደ ሮም ሊልክ ቋምጧል። የድል ብሥራት ልኮ ከአለቆቹ የሚመጣለትን ሙገሳ ለመስማትም ጓጉቷል።

ኢትዮጵያውያንም በአምላካቸው እየተመኩ፣ በጥበብ ፣ በጀግንነት እና በአንድነት እየተዋጉ ድልን ከእነርሱ ጋር ይዘዋታል። ለማንም አሳልፈው አይሰጡም። የኢትዮጵያ የጦር አመራር እና የጦርነት ውሎ ግሩም ነበር። ከጀግኖቹ ፊት መቆም የሚኾንለት አልነበረም። ጀግኖች የጦር መሪዎችና ጦረኞች ጣልያን አምባላጌ እና መቀሌ ላይ ሰባብረው ዓድዋ ላይ አድርሰዋታል። የኢትዮጵያ ጀግኖች በድላቸው ሳይኩራሩ፣ለተሰጣቸው ድል አምላካቸውን እያመሰገኑ የጦርነት ስልታቸውን ይቀምራሉ። በቀመሩት ስልት በጀግንነት ይዋጋሉ፣ ድልም ያደርጋሉ።

የጭንቋ ቀን ደረሰች። የካቲት 22 ለየካቲት 23 ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ። ከባዱ ጦርነት ሊጀመር ነው፣ የጀግና ልኩ ሊታይ ነው። የፈሪም ልቡ ሊፈተሽ ነው። ድል አድራጊውም ሊገለጥ ነው። ተሸናፊውም አንገቱን ሊደፋ ነው።

ተክለፃዲቅ መኩሪያ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴን ጠቅሰው ሲጽፉ ” ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም የጣልያን ጦር በድንገት ደረሰ። አምስት መቶ ከሚኾኑት በር ከሚጠብቁት ከራስ መንገሻ ወታደሮች ጋር ገጠመ። እነዚህም መልሰው ሲዋጉ ሁለት ባሸ ጦር ቡዙቅ ማረኩና ቢጠይቋቸው ግማሹ የአፄ ምኒልክ ጦር ስንቅ ፍለጋ መሄዱን ስለሰሙ ጣልያኖቹ በድንገት አደጋ ጥለው ለመዋጋት አራት ጀኔራሎች በአባ ገሪማ በኩል አንደኛው ጀኔራል በማርያም ሸዊቶ ተሰልፈው ይጓዛሉ ብለው ተናገሩ”

ይህ ወሬ ለአፄ ምኒልክ ተነገራቸው። ታላቅ አጋጣሚ ነበር። የጣልያን የጦር አሰላለፍ ያሳያልና። አፄ ምኒልክ ጦሩን አስነሱ። በለው ድሉ የእኛ ነው አሉ። ሠራዊቱ የንጉሡን ድምፅ እየሠማ ወደፊት ገሰገሰ። እቴጌ ጣይቱም ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ወደ ጦርነት ገቡ። የጦር መሪዎች በተሰጣቸው ትእዛዝና ሥፍራ ጦር እየመሩ ገቡ። ጦርነቱ ተፋፋመ። የኢትዮጵያ ጀግኖች ወደ ጠላት ሰፈር እየዘለሉ ገቡ። ምድር ቀውጢ ኾነች። ደም ዋጣት፣ አስፈሪ ድምፅ አስጨነቃት።

“የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ ጠላትን መደለቅ አንድነት ያውቃሉ” እንደተባለ የጦር መሪዎች እና ጦረኞች የዳኛው አሽከር እያሉ እየፎከሩና እየሸለሉ፣ ጠላትን መፈናፈኛ አሳጡት፣ በፊት በኋላው፣ በቀኝ በግራው ከበው አጣደፉት፣ እንደ ጤፍ አጨዳ አጨዱት፣ እያጨዱ አስተኙት።

በዚያን ጊዜ መነኮሳት የሰኔል ቆባቸውን እንደደፉ፣ ቢጫ ካባቸውን እንደደረቡ፣ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው፣ ግማሹ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ ፣ ግማሹ ከእቴጌ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንት እና ወታደር ዘንድ ወዲያና ወዲህ እያሉ ሲያበረታቱ ዋሉ። የኢትዮጵያ ጦር ከጦርነቱ የሸሸውን የጣልያን ጦር የራቀውን በጥይት የቀረበውን በጦርና በጎራዴ እየመታ ፈጀው። አፄ ምኒልክ ወደ ፊት እየገፉ ጦር ያነሰበትን ግንባር እየመረመሩ በፍጥነት ጦር እየላኩ አዋጉ። የጣልያን ጀንበር ዳግም ላትዘልቅ ጠለቀች፣ የኢትዮጵያ ጀንበር ዳግም ላትጠልቅ በዓድዋ ሰማይ ሥር ዘለቀች።

” ውጋ በርታ” የሚለው ነጋሪት እየተጎሰመ ጦርነቱ ተካሄደ። ጀግኖች ድል አደረጉ። ጣልያን አንገት ደፋች። በዓድዋ ሠማይ ሥር እንዳልነበር ኾነች። ተክለፃዲቅ ያን ኹነት ሲጽፉ “አቡነ ማቴዎስ የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስት እና ከመነኮሳት ጋር ኾነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁሩን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ ድሉ ተፈጸመ። የጣልያን ወታደሮች ብዙ ወደቁ። የቀሩትም ሸሹ” ብለዋል።

በእምነት ፣ በጀግንነት ፣ በአንድነት ፣ በፍፁም ቅንነት እና ኢትዮጵያዊነት የተዋጉት ጀግኖች ጸሎቱ ሳይፈፀም፣ ዜማው ሳይደመም ለዘመናት የሚበቃ፣ ከዳር ዳር የተሰማ፣ በዓለም አደባባይ የተደነቀ ድል ተቀዳጁ። የሀገራቸውን ክብርና ዝናም ከፍ አደረጉ።

“በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈጠመ ጣልያን ሀባሻ እንዳይደርስ”

ጣልያን ወደ ሀበሻ እንዳትደርስ ኾና በሠራችውና ባመጣችው መሠሪያ እየተመታች ተፈፀመች። ድምጥማጧ ጠፋ። አልሞ የማይስተው የኢትዮጵያ ጀግና ሲሻው በጠመንጃ፣ ሲሻው በጦርና በሳንጃ እየመታ ጣላቸው። በሀበሻ ምድር ፈፀማቸው።

“ባሕር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጂ
እንደ ተልባ ሥፍራ ትከዳለች እንጂ
አትረጋምና ያለ ተወላጅ። ” እንደተባለ ባሕር ዘለው፣ ተው እየተባሉ እምብኝ ብለው የመጡት ዘመን ከዳቸው፣ ጀግና በጀግንነት ቀጣቸው፣ እንደተልባ ሥፍር ተንሸራተቱ። ሀገር ለባለርስቶች እንጂ ለባንዳዎች እንደማትኾን አሳዩዋቸው። የምትረጋው ለባለርስቶች ብቻ ነው።

ተጨንቃ የነበረችው ዓድዋ ታላቁን ጦርነት ፣ ታላቁንም ድል አየች። ፈሪው ሲሮጥ ጀግናው እያባረረ ጠላት ሲወቃ፣ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከፍ ሲል፣ ንጉሡና ንግሥቲቱ ፣ መሳፍንትና መኳንንቱ፣ የጦር አበጋዞችና ጦረኞች በዚያ ጦርነት የተሳተፉና ድል የተቀዳጁ ሁሉ በአሸናፊነት ሲመላለሱ አምላካቸዉንም ሲያመሰግኑ ታዘበች። ለምስክርነት፣ ለዚያ የጀግንነት ውሎ ታዛቢነት ተቀመጠች። የታላቁ ድል መጠሪያ ኾና ትጠራለች ፣ ትታወሳለች፣ ከፍ ከፍም ብላ ትኖራለች።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቀደምት አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next article“ዓድዋ የመላው የዓለም ጥቁሮች በዓል ነው” የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)