“ቀደምት አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

62

ባሕር ዳር:የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ በመታሰቢያ በዓሉ ላይ ርዕሰ ብሔር ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የዓድዋ በዓል ተራ በዓል አይደለም ያሉት ርዕሰ ብሔሯ ዘርፈ ብዙ ትርጉም፣ ዘመን ተሻጋሪ አበርክቶ እና የጋራ ታሪክ ያለው በዓል ነው ብለዋል፡፡ የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት መስፋፋትን የገታ፣ ለዘመናዊቷ አፍሪካ መመሥረት መሠረት የጣለ እና ለፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሳት እርሾው ዓድዋ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ለዚህ ታላቅ ድል እና ገድል ያበቁን እልፍ ኢትዮጵያዊያን ውድ የኾነ ሕይዎታቸውን ለግሰው ነው ብለዋል፡፡

በፋሽሽት ጣሊያን ሁለተኛ ወረራ ወቅት የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በጋራ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ በየቦታው ለተቃውሞ ወጥተው ነበር ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በመልዕክታቸውም “አንድ የነጻነት፣የክብር ተምሳሌት ብትኖረን፤ አንድ ነጻ ጥቁር መንግሥት ያውም የነጭን ወረራ የረታ ቢኖረን፤ እንዴት እርሷን ለመውረር ተነሱ” የሚል ነበር ብለዋል፡፡ ለሁላችን አርዓያ እና ተምሳሌት አለን በምንልበት ዘመን የኢትዮጵያን መውረር አንቀበልም ብለው መሞገታቸውን ታሪክ መዝግቦታል ብለዋል፡፡

የዚያ ዘመን የመላውን ዓለም ጥቁር ሕዝብ አንድነት እና መተባበር ያስተዋለ ዓድዋ ፤ መንደርም፣ ሰፈርም እንዳልኾነ ይገባዋል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ የዓድዋ ድል የዓለም ነው ብለዋል፡፡ ለሉዓላዊነት መከበር፣ ለነጻነት መረጋገጥ እና ለጭቆና መገርሰስ የተነሱ ኹሉ የዓድዋ ድል መንፈስ በውስጣቸው አለ ብለዋል፡፡

“ቀደምት አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በሚያራርቁን ጉዳዮች ላይ ከመንጠልጠል አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ ማጠንጠን ሀገራዊ ፋይዳ አለው ነው ያሉት፡፡ አኹናዊቷ ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ድርቅ እና መፈናቀል ያጎሳቆላቸው በርካታ ዜጎች አሏት፡፡ ለእነርሱ መድረስ እና እነርሱን ማዕከል አድረጎ መስራት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ዓድዋ ከኢትዮጵያ በተሻለ በውጭው ዓለም ጥቁር ሕዝብ ዘንድ በወጉ እና በልኩ ይከበራል ለማለት ያስደፍራል ያሉት ርዕሰ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሌሎች የተቀበሉትን እና ያከበሩትን ታላቅ የድል በዓል በተሻለ መንገድ ማክበር እና መቀበል ታሪካዊ ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ አንድ ማኀበረሰብ እንመሰርታለን ካልን ከልዩነት ይልቅ አብሮነት፤ ከሚነጣጥሉ ይልቅ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ መስራት ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous article“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Next article“የካቲት 23 ተጨንቆ የነበረዉ የዓድዋ መሬት”