
ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በባሕርዳር ከተማ ሙሉዓለም የባሕል አዳራሽ ውስጥ በድምቀት እየተከበረ ነው። በድል በዓል ዝግጅቱ ላይ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው፣ የተለያዩ አባት አርበኞች እና ጥበበኞች ተገኝተዋል።
ከንቲባ ድረስ ሳህሉ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያንም አልፎ ለመላው አፍሪካዊያን እና ለዓለም ጥቁሮች የነጻነት ምልክት ነው ብለዋል። “ዓድዋ የመላው የዓለም ጥቁሮች በዓል ነው” ሲሉም ገልጸዋል። የዓድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነትን እና አሸናፊነትን ያየንበት ነው ብለዋል። ከዓድዋ ድል በሀገራዊ አንድነት የጋራ አጀንዳ ይዞ በተግባቦት መሥራት ለውጤት እንደሚያበቃ ተምረንበታል ሲሉም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው “የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ለመግዛት የመጣ ጠላት ድባቅ የተመታበት እና በእግሩ የተነዳበት ድል ነው” ብለዋል። የዓድዋ ድል የተገኘው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደብረት በጠነከረ እና በተሰናሰለ አንድነት ያመጡት ድል ስለመኾኑም ተናግረዋል። የአሁኑ ትውልድም በአንድነት በመቆም የሀገሩን ታሪክ ማወቅና መጠበቅ እንዳለበት አቶ ዳኝነት መልእክት አስተላልፈዋል።
ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የተገኙ ምሁራንም በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው የድል በዓሉን የተመለከቱ ጽሑፎችን ለታዳሚው እያቀረቡ ነው።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!