በወረኢሉ ታቦተ ጊዮርጊስ ከመንበሩ ወጥቶ የዓድዋ የድል በዓል እየተከበረ ነው።

55

በወረኢሉ ታቦተ ጊዮርጊስ ከመንበሩ ወጥቶ የዓድዋ የድል በዓል እየተከበረ ነው።

ወረኢሉ: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ የድል በዓል በወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከመንበሩ ወጥቶ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።

የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከዓድዋ ጦርነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው። ታቦቱ ወደ ዓድዋ ከዘመቱ ታቦታት መካከል አንዱ እንደኾነ ይነገራል። አፄ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ድል አድርገው ሲመለሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን አሠርተው ስሙን ደብረ ሰላም እንዳሉት ይነገራል።

ወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በንጉሥ ናኩቶለዓብ ዘመን እንደተሠራ ይነጋረል።

የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መላከ ሰላም አባ ተፈራ ውለታለው የዓድዋ ድል በሚታሰብበት የካቱት 23 ታቦተ ጊዮርጊስ ከመንበሩ ወጥቶ በዓሉ እንደሚዘከር ነግረውኛል።

አፄ ምኒልክ በወረኢሉ በነበሩበት ጊዜ በደብረ ሰላም ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ኪዳን ያስደርሱበት፣ ቅዳሴ ያስቀድሱበት፣ ስብሐተ እግዚአብሔር ያቀርቡበት እንደነበርም ነግረውኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚታሰብበት በ23ኛው ቀን የተገኘው ድል የጊዮርጊስን ተራዳዒነት ያሳዬ ነውም ብለዋል። የዓድዋ ድል ሲታሰብ ታቦቱ የሚወጣበት የእግዚአብሔርን ረዳትነት፣ ጠባቂነት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተራዳዒነትና ለምልጃ ፈጥኖ ደራሽነትን ለማሳብ እንደኾነም ገልፀዋል። በበዓሉ የምኒልክ በድል አድራጊነት እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ጋር የነበራቸው ግንኙነትም ይነገርበታል፣ ታሪክ ይዘከርበታል ነው ያሉት።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን ጠላት እንዳይደፍራት፣ በቅዱስ መንፈስ እንደረዳቸው እና በዓድዋ ድል ላይ ተራዳዒነቱ የታየበት እንደነበርም ነግረውኛል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀጣይ ዓመት የዓድዋ ድል በዓልን አፍሪካዊ ወንድሞቻችን አካትተን አፍሪካዊ ክብረ በዓል ለማድረግ እንሠራለን” ፊልድ ማርሻ ብርሃኑ ጁላ
Next article“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት