“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

55

ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነው ብሏል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው። ሙሉ የመግለጫው መልእክት ቀጥሎ ይቀርባል።

የካቲት 23/1888 ዓ.ም አባቶቻችን የተጎናፀፉት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ነፃነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ሊገፍ የመጣውን የሰለጠነ ወራሪ ጦር በታላቅ በጀግንነት፣ ወኔ፣ በአንድነትና በጽናት ያሸነፉትበት እለት ነው፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድ የፍቅር ገመድ ያሰናሰለ የነፃነት እና ሉዓላዊነት ብስራት ነዉ፡፡ ድሉ የኢትዮጵያ ሕብረብሔራዊ አንድነት የጸናበት የማዕዘን ድንጋይም ነው። የዓድዋ ድል ከጊዜያዊ ውጤቱ ባሻገር የዓለም የሰው ልጆችን ታሪክ ጭምር የቀየረ በደማቅ ቀለም የተፃፈ ድል ነው፡፡

ድሉ ከማሸነፍም ባሻገር የኢትዮጵያዊ አንድነት የፀናበትና የመተባበራችን ዉጤት ማሳያ መስታወት ኾኖ ሲዘከር ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ለአንድ የጋራ ሀገራቸው ከአራቱም አቅጣጫ በአንድ ጥሪ ተሰባስበው፤ የጋራ ጠላትን ድል በመንሳት ሕልውናቸውን ያረጋገጡት አንዱ እና ዋነኛዉ በዓድዋ ድል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥቅማቸው የሚከበረው በመተባበር እንጂ በመለያየት እንዳልኾነም የዓድዋ
ድል ኽያዉ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ፤ በአንድነት አብረው በጋራ ሲሰለፉ ምን አይነት ውጤት እንደሚያመጡ በዓድዋ ድል ተረጋግጧል፡፡

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነፃነትን ያበሰረ ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ መፀነስ ትልቅ መሠረት የጣለ ክስተትም ሆኗል፡፡

በዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የነበራቸው የአመራር ብቃት፣ ፅናት፣ ጀግንነትና የዓላማ አንድነት ምንግዜም የሚታወስ ነዉ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን በውስጣቸው የነበረዉን ልዩነት ወደ ጎን በመተዉ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለማጽናት በጋራ መቆማቸዉ የዓድዋን ድል እንድንጎናፀፍ አድርጎናል፡፡

የዓድዋ ድል መንፈስ በቀጣይ ተከታታይ ትውልዶች አዕምሮ ውስጥ የተቀረፀ የድል ሐውልት በመኾኑ፤ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ሀገራዊ ፈተናዎች በጋራ ርብርብ መፍታት እደምትችል ቁምነገር ያስጨበጠ ነው፡፡

የዛሬው ትውልድ በዓድዋ ድል የታየውን የአባቶቹን ጀግንነት፤ አንድነት እና የዓላማ ዕናት በተለያዩ መስኮች መድገም ይኖርበታል፡፡ በዘመናችንም በሕዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የአሸባሪዎችን ጥቃት በመመከት በአረንጓዴ አሻራ፤ እና በሌሎችም መስኮች የታየው ኅብረትና ያመጣው ውጤት፤ በዓድዋ ድል መንፈስ መንቀሳቀስ ውጤቱ አጥጋቢ እንደሚኾን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

የዛሬዉ ትዉልድ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ከግቡ ማድረስ እንደምንችል ከዓድዋ ድል ትምህርት መዉሰድና በተሰማራንበት መስክ ሁሉ የአባቶቻችንን
የአሸናፊነት መንፈስ በመሰነቅ ለአገራችን የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።

ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ127ኛዉ የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!!

ዓድዋ፡ አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት!!

የካቲት 23/2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous articleበወረኢሉ ታቦተ ጊዮርጊስ ከመንበሩ ወጥቶ የዓድዋ የድል በዓል እየተከበረ ነው።
Next article“ቀደምት አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ