ነጋሪት ማስጎሰም፤ ሰላቶን ማሳደድ ነበረ ሥራችን፤ ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን! ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እትጌ ጣይቱ

166

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ከእያንዳንዱ ጠንካራ ወንድ ጀርባ አንድ ጠንካራ ሴት አለች” ይላሉ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው፡፡ እውነት ነው ከአፍሪካዊያን የነጻነት አባት ክንደ ብርቱው እምዬ ምኒልክ ጀርባ የማትታጠፈው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ኃይለ ማርያም ነበረች፡፡ “ሥምን መላዕክ ያወጣዋል” እንዲሉ ጣይቱ የዓለም ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ብርሃን ሆናለች፡፡ ዓድዋ ነጻነትን ያገኘንበት ሳይሆን ባርነትን ፈጽሞ ያላየንበት በዓል ነውና፤ ከዚህ የዓለማችን ልዩ የበዓል ክስተት ጀርባ ያች ደርባባ ንግሥት እና የጦር ባለመላ አብዝታ ትከበራለች፡፡

ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ከሚለው የንግሥና ሥሟ ጋር አብሮ የሚሄድ ምግባር፤ ሥሟን ሥራዋ የሚመሰክርላት በሳል እቴጌ፡፡ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ በዓድዋ ተራሮች አናት ስር ልክ የዛሬ 127 ዓመት ላይ የለኮሰችው የድል ችቦ በመላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ዘንድ አበራ፡፡ የባርነት ወጌሻ፣ የሴት ባለመላ፣ የዓድዋ ጦርነት ድል ቀንዲል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቆርቋሪ እና መሥራች እንደነበሩ የሚነገርላቸው እቴጌ ጣይቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት፣ ሊቅ እና ጥንቁቅ፣ የአጼ ምኒልክ አማካሪ፣ የልብ ሴት እና የትዳር አጋር ናቸው፡፡

ትልቁ ራስ ጉግሳ የጎንደሯን ባላባት ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ወይዘሮ ሂሩትን ይወልዳሉ፡፡ ወይዘሮ ሂሩት ከራስ ገብሬ እና ከወይዘሮ ሳህሊቱ የሚወለዱትን ደጃዝማች ኃይለ ማርያምን አግብተው ደጃዝማች ብጡልን እንደወለዱ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ደጃዝማች ብጡል ደግሞ የጎጃም ደብረ መዊዕ ባላባት የኾኑትን ወይዘሮ የውብዳርን አግብተው ነሐሴ 12/1832 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ በደብረ ታቦር ከተማ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ይወልዳሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን አብዝተው በማዕረግ ስማቸው “ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ እንደ ሴት ብልህ እንደ እናት ሩህሩህ፤ እንደ ሚስት መካሪ እንደ ተዋጊ አባራሪ፤ እንደ ንግሥት እመቤት እንደ ጦረኛ ኩራት የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ለዳግማዊ ምኒልክ ገጸ በረከት፣ ለዘውዳቸው ጉልላት እና ለቤተ መንግሥታቸው ውበት ነበሩ ይባላል፡፡

አፈወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ» በሚለው መጽሐፋቸው «አጼ ምኒልክ ከልጅነት ጀምረው ሲመኟት እና ሲያልሟት ትኖር የነበረችው ጣይቱ ብጡል በ1875 ዓ.ም ደብረ ብርሃን ገባች። ንግሥተ ሸዋ ኾነች፤ በእለተ ፋሲካ አንኮበር መድኃኔዓለም ቆርበው ተጋቡ። … ፀሐይቱ ለማለት ጣይቱ ተባለች ነገር ግን ከጣይቱ እጣይቱ ለመባል ይገባታል» ይሉናል።

ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ “ጣይቱ ብጡል” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ደግሞ የአፄ ፋሲል ተወላጅ ከኾኑት ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ፍፃሜ መንግሥት) የሚመዘዝ የዘር ሐረግ ያላቸው እቴጌዋ በሳል፣ አስተዋይ እና ተራማጅ ነበሩና የኋላ ኋላ በጋብቻ ሸዋ ድረስ ዘልቀው በመተሳሰር በዘመነ መሳፍንት የቆሰለችውን ኢትዮጵያ መርምረው እና አክመው አንድና ጠንካራ ማዕካላዊ መንግሥት እንዲኖራት አድርገዋል ይላሉ፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ሳይኾን ለሚወዱት ሕዝብ ጭምር ዘውድ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የቻሉትን ሁሉ እንዳበረከቱ ይናገራሉ፡፡

ፋሽሽት ጣሊያን ከምኒልክ ይልቅ ጣይቱን አብዝታ ትፈራ ነበር ይባላል፡፡ አወዛጋቢውን የውጫሌ ውል ሥምምነት ተከትሎ በአንቀፅ 17 ስር ክፉኛ የተበሳጩት እቴጌዋ የያዙት አቋም ግልጽ እና የማያወላውል ነበር፡፡ “…እኔ ራሴ ሴት ነኝ ጦርነት አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህን መሰሉን ሥምምነት ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ” ሲሉ አይቀሬውን ጦርነት በጸጋ፣ በልበ ሙሉነት እና በጀግንነት ተቀብለውታል፡፡

የተናገሩትን የሚተገብሩት፣ ለሀገራቸው ክብር እና ለሕዝባቸው ፍቅር ጦርነትን ያክል ፈታኝ ዳገት ከመወጣት ያልገደባቸው ንግሥት በአይቀሬው የዓድዋ ጦርነት በመሪነት ከፊት ተሰለፉ፡፡ 3 ሺህ እግረኛ እና 6 ሺህ ፈረሰኛ አስከትለው ውጣ ውረድ የበዛበትን የጦርነት ጉዞ በድል አድራጊነት አጠናቀቁ፡፡ መቀሌ ላይ በስልት የጀመሩትን የጦርነት ጥበብ ዓድዋ ላይ በሰይፍ እና በጎራዴ የሰላቶን ጦር እየቀሉ ነጻ ሕዝብን እና ነጻ ሀገርን አስቀጠሉ፡፡

ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ሀገራቸውን ከውርደት ሕዝባቸውን ከባርነት በመታደግ አፍሪካ የማትረሳው ውለታን አበረከቱ፡፡ ዳሩ እቴጌዎም ሰው ነበሩና እጅግ የሚወዷቸውን እና የሚያከብሯቸውን የትውልድ አጋራቸውን እምየ ምኒልክን በሞት ያጡት እቴጌ በመጨረሻም እንዲህ ብለው ያንን ደማቅ እና ታሪካዊ የመሪነት ዘመናቸውን አጠናቀቁ፡-

ነጋሪት ማስጎሰም፤ ሰላቶን ማሳደድ ነበረ ሥራችን፣
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን!

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓድዋ ድል ዘመን የነበረውን አንድነት እና መተባበር ለአሁኑ ዘመን ሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ።
Next article“በቀጣይ ዓመት የዓድዋ ድል በዓልን አፍሪካዊ ወንድሞቻችን አካትተን አፍሪካዊ ክብረ በዓል ለማድረግ እንሠራለን” ፊልድ ማርሻ ብርሃኑ ጁላ