‹‹በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተን ዕውቅና ላገኘን የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጠን ይገባል፡፡›› የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች

1158

‹‹በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተን ዕውቅና ላገኘን የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጠን ይገባል፡፡›› የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች

‹‹የመሪ ዕቅድ ክለሳ ጠይቀናል፤ ዕቅዱ ጸድቆ ሲመጣ ለማኅበራት ምልሽ ይሰጣል፡፡›› የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር

‹‹በቀን 02/09/2011ዓ.ም ‹የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ይስተካከልኝ› ብሎ በጠየቀው መሠረት የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት በቀን 13/10/2011ዓ.ም ምላሽ ሰጥቷል፡፡›› የአማራ ክልል የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር በማኅበር የተዳራጁ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጠያቂዎች ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማገኘት 283 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 66 ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዕውቅና ያገኙ መሆናቸውንና 217 ኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
አቶ መለሰ ጌታሁን በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር በማኅበር ተደራጅተው ዕውቅና ካገኙት 66 የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ በአንዱ አባል ናቸው፡፡ ‹‹የመኖሪያ ቤት ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው፡፡ ይህንን በመረዳት መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተን ዕውቅና ላገኘን የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጠን ይገባል›› ብለዋል፡፡ በየጊዜው የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳማረራቸው በመግለጽና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውም መሆኑን በማመልከት የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ምንተስኖት አዳነ ደግሞ በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ተደራጅተው ዕውቅና ለማገኘት ከሚጠባበቁ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የአንዱ አባል ናቸው፡፡ ‹‹ዕውቅና እንሰጣለን ብለው አደራጅተዋል፤ በውሉ መሠረትም ዕውቅና ሊሰጡን ይገባል›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ይሰጠን ጥያቄ ስናቀርብ ‹ቦታ የለንም› እያለን ነው፡፡ ለነዋሪዎች የቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ እንዳለ እንውቃለን፤ መሪዎች የዜጎችን ችግር ተረድተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጡን ይገባል›› ብለዋል፡፡
የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበር የሥራ ሂደት ተተኪ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ኃይሉ በሰጡት ምላሽ ደግሞ ‹‹የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የዜጎችን የመደራጀት መብት መሠረት በማድረግ አደራጅተናል፡፡ ዕውቅና ለሚገባቸውም ዕውቅና እንዲሰጥ ተደርጓል፤ ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ መሬት የለኝም ብሏል›› ብለዋል፡፡

‹‹241 ማኅበራት ግን ከተደራጁበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ዓመት ስላልሞላቸው ዕውቅና ለመስጠት አይቻልም›› ብለዋል አቶ ሙሉጌታ፡፡ በመጪው ጥር አካባቢ አንድ ዓመት ሲሞላ ዕውቅና እንደሚሰጣቸውም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ይህንን ይበሉ እንጂ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ ቁጥር 28/2009 ዕውቅና ለማግኘት የተደራጁ ማኅበራት አንድ ዓመት እንዲጠብቁ አያዝዝም፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አግልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ዘለቀ በከተማ አስተዳደሩ ከ2006 ጀምሮ ለ186 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡ ከተማዋም ከሌሎች ከተሞች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቦታ ለነዋሪዎች ከሰጡት ከተሞች ግምባር ቀደም እንደሆነች ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት ግን በከተማ አስተዳደሩ ተደራጅተው ቦታ ለማገኘት ለሚጠባበቁ ዜጎች የሚሆን ቦታ እንደሌለ ነው ያስታወቁት፡፡ ‹‹እንጅባራ ከተማ የ10 ዓመት መሪ ዕቅዷን ጨርሳለች፤ በዙሪያ የሚገኙት ወረዳዎች ወደ እንጅባራ ከተማ እንዲካለሉ የመሪ ዕቅድ ክለሳ ጠይቀናል፤ ዕቅዱ ጸድቆ ሲመጣ ለማኅበራት ምልሽ ይሰጣል፤ በዚህ ዓመት ለ16 ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምላሽ ይሰጣል›› ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ ከአርሶ አደሮች መሬት አስለቅቆ ለመኖሪያ ቤት መስሪያነት ቦታ ለመስጠትም ከፍተኛ ካሳ መጠየቁ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ደግሞ የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር በእ/ከ/አስ/671ል-24 በቀን 02/09/2011ዓ.ም ‹የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ይስተካከልኝ› ብሎ በጠየቀው መሠረት የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት በቀን 13/10/2011ዓ.ም ምላሽ መስጡትን አስታውቋል፡፡

አቶ ጌታሁን ፀሐይ በአማራ ክልል የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ፕላን ዝግጅት የሥራ መሪ ናቸው፡፡ ‹‹የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለገበያ እና ለመሳሰሉት ሥራዎች አመቺ የሆነው የመዋቅራዊ ፕላን በጥያቄው መሠረት ከተላከ ቆይቷል›› ብለዋል አቶ ጌታሁን፡፡ አጎራባች ቀበሌዎች ወደ ከተማ አስተዳደር እንዲገቡ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ የይዞታ ጥቄን በተገቢ መልኩ በመመለስ ለነዋሪዎች ቀልጣፋ አግልግሎት መስጠት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው

Previous article“የአማራ ሕዝብ አቃፊነት የረጅም ዓመታት ልምዱ ነው፤ ወገኑ አንድ ቦታ ቢጎዳበት ዘር ቆጥሮ ጥቃት ለማድረስ ሕዝቡ የተዋቀረበት ሥነ ልቦና አይፈቅድለትም፡፡” አቶ ዮሐንስ ቧያለው
Next articleየጋዜጠኛው የጉዞ ማስታዎሻ ሲቀጥል፡፡