
ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የባርነት ቀምበር የተሰበረበት የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ከፍ ከፍ ያለበት የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን የድል በዓል ነው።
ይህ ድል በቀላሉ አልተገኘም ደም እና አጥንት እንዲሁም ሕይወት ተገብሮበታል። በርካቶች ስለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ በክብር አልፈዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ዓድዋ በ1888 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና በጣልያን መንግሥት መካከል የተደረገ ጦርነት ነው ብለዋል።
ጦርነቱን በበላይነት አሸንፎ ሀገር ለመውረር የመጣው የጣልያን ወታደር ተንኮታኩቶ የወደቀበት፣ አዋርጄ፣ ሀገር ዘርፌ እመለሳለሁ ብሎ በማን አለብኝነት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ የመጣው ወራሪ የተዋረደበት የድል በዓል ነው ብለዋል።
አውሮፓውያን የአፍሪካ አህጉርን በእጣ ተከፋፈሉ። ነጭ የበላይ ጥቁር የበታች የሚል እምነት አደረባቸው።
ኢትዮጵያ ሲደርሱ ግን እንዳሰቡት አልኾነም። እምቢ ለሀገሬ ፣ እምቢ ለወገኔ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በንጉሡ አዋጅ በአንድ ከትቶ ጠበቃቸው። ሀገራዊ አንድነት ያሰባሰባቸው የአንድ ብርቅየ ሀገር ሕዝቦች ስለአንድነት ስለ ፍቅር ስለነጻነት በአንድ ተባበሩ።
በወቅቱ ለዘር፣ ለቀለም፣ ለቋንቋ እንዲሁም ለብሔር ቦታ ያልነበራቸው ድንቅ ሕዝቦች ስለአንድ ሀገራቸው በጋራ በአንድነት ዘመቱ። ለወራት ባደረጉት ጉዞ አንዱ አንዱን እየረዳ ፣አንዱ አንዱን እያገዘ በፍቅር ተጓዙ። አንድነታቸውን ሀገራቸውን ከባዕድ ወረራ ነጻ ለማድረግ ተጠቀሙበት።
ለሀገራቸው ሲሉ ልጅ፣ ሚስት እና እናት የሚለው ነገር ማነቆ አልኾነባቸውም። በፍቅር የተገመደው አንድነታቸው ለድላቸው እርካብ ኾናቸው። በመተባበር እና በአንድነት በመሰለፋቸው ኢትዮጵያዊያን በዓለም አደባባይ በተለይ በአውሮፓውያን ዘንድ ግርማ ሞገሳቸው ገዘፈ። ይህን የተገመደ አንድነት ለዛሬ ማንነታችን መጠቀም እንደሚገባ ፕሮፌሰር አደም ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር አደም ሀገርን እንደነበረ ለማስቀጠል በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የነበረው አንድነት ማስቀጠል ተገቢ ነው ብለዋል።
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሀገር ማለት ጀግኖች አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ለትውልዱ ያስረከቧት ከእንቁ የከበረች፣ ለዘላለም የምታበራ ሀገር እንጂ ዛሬ ውስጠ ወይራ ብልጣ ብልጦች በሚሸርቡት ተንኮል ልክ የወረደች አይደለችም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሔር ሙዚየም ተብላ ትታወቃለች። ይህን የብሔር ሙዚየምነቷን በዓድዋ ጦርነት አስመስክራለች። ሕዝቦቿ ለሀገራቸው አንድነት ሲሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጦርነቱ ታድመዋል። ዛሬም ከመለያየት ይልቅ መተባበር፣ ከፀብ ይልቅ ፍቅርን ልናስቀድም ይገባል ብለዋል።
በአድዋ ዘመን የነበረው አብሮነት፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ዛሬም ቀጥሎ ስሟ በዓለም አደባባይ ገዝፋ የምትታይ ሀገር ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትጠናከረው ለ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን ችግር ገጠማት ማለት የአፍሪካ ቀንድ ችግር ላይ ወደቀ ማለት በመኾኑ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያዊያን ጎን መሰለፍ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስጠበቁበትን አንድነታቸውን፣ ኅብረታቸውን እና መተሳሰባቸውን በኢትዮጵያ መዲና፣ በአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በኾነችው አዲስ አበባ ሙዚየም ከፍተን ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የከፈሉትን ዋጋ ፣አንድነታቸውን ፣ኅብረታቸውን ለአፍሪካውያን ብሎም ለዓለም ሕዝብ ማሳየት አለብን ብለዋል። ኢትዮጵያ ያደረገችውን ተጋድሎ፣ የከፈለችውን መስዋዕትነት ማሳየትና ማስረዳት ይኖርብናል ብለዋል።
ፕሮፌሰር አደም ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሀገር ከኾነች የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰላማቸው ተጠብቆ፣ አንድነታቸው ጸንቶ፣ በአብሮነት ለነጻነት እና ለአፍሪካ ብልጽግና እንደሚተጉ የተለያዩ ጥናቶች ሲቀርቡ መከታተላቸውን ገልጸዋል። ያለዚያ የአንዱ ዳፋ ለአንዱ ይተርፋል እንዲሉ አወዳደቃችን የከፋ ይኾናል ብለዋል።
በአድዋ ድል ዘመን የነበረውን አንድነት ዛሬ በመድገም የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ ተገቢ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck