
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) በክልሉና በሀገሪቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች በሰከነ መንገድ እንዲፈቱ የክልሉ መንግሥት እየሠራ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተናገሩ፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበርና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለዉ በሰሜን ሸዋ ዞን የሞጃና ወደራ ወረዳ ነዋሪዎችን አወያይተዋል፡፡ መልካም አስተዳድር፣ ልማት እና ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በአካባቢው ነዋሪዎች ሐሳብ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
መሠረተ ልማትን በተመለከተ ከጣርማበር – ሰላ ድንጋይ ያለ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የመብራት መቆራረጥ እና ዓመታትን የተሻገሩ የድልድይ ግንባታዎች ባለመጠናቀቃቸው ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው አቅርበዋል፡፡ በአካባቢያቸው ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተከናወኑ ባለመሆናቸው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፈታኝ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከፋይናንስ ተቋት ጋር በተያያዘም ‹‹የብድር አሰጣጥ ሂደቱ አስቸጋሪ ሆኗል›› ያሉት ነዋሪዎቹ የክልሉ የፋይናንስ ተቋማትና የባንኮች አሠራር ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበትም ነው የጠየቁት፡፡ የአጣዬ እና አካባቢው እንዲሁም የሀገሪቱን የወቅቱን የፀጥታ ሥጋት መነሻ በማድረግም የክልሉ መንግሥት ለሠላም ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሠራ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ ሊቆም ይገባል›› ያሉት ነዋሪዎቹ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገር የሕዝቦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ እንደሆነም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበርና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ ከኢንቨስትመንትና ከመሠረተ ልማት ተገልሎ የኖረ በመሆኑ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ይፈታሉ›› ብለዋል፡፡
‹‹የአማራ ሕዝብ ያለ ስሙ ስም ሲሰጠውና ሲበደል ኖሯል፤ እውነታው ግን ሲነገድበት ከነበረው ታሪክ ይልቅ በሀገር ጠባቂነትና በሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር ሲሰራ የነበረና ጉልህ ታሪክ ያለው መሆኑ ነው›› ብለዋል አቶ ዮሐንስ፡፡
“በሀገሪቱ በዚህ ወቅት ያለው አለመረጋጋት ትልቅ እረፍት ይነሳል፤ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍና በደል እንዲሁም እልቂት አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡ ትንኮሳዎች በየጊዜው እየጨመሩ መሄዳቸውን ያወሱት አቶ ዮሐንስ ‹‹በዚህ ወቅት ማን ምን እንደሚሠራ ጠንቅቀን እናውቃለን›› ያሉት አቶ ዮሐንስ ለክልሉ ሠላም መደፍረስ ድብቅ ተልዕኮ ይዘው የሚሠሩ አካላትንም አዴፓ ለይቶ እንደሚታገል ነው ያስረዱት፡፡
‹‹የአማራ ሕዝብ አቃፊነት የዛሬ ሳይሆን የረጅም ዓመታት ልምዱ ነው፤ ወገኑ አንድ ቦታ ቢጎዳበት ዘር ቆጥሮ ጥቃት ለማድረስ ሕዝቡ የተዋቀረበት ሥነ ልቦና አይፈቅድለትም፤ ምክንያቱም አማራ አቃፊና በፍቅር የሚያምን ነው›› ብለዋል አቶ ዮሐንስ፡፡ የትግራይ ክልል መንግሥት አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አልልክም ቢልም ተማሪዎቹ የአማራን ሕዝብ ጠንቅቀው ያውቁት ነበርና ዛሬ በሠላም ትምህርታቸዉን እየተከታተሉ ይገኛሉ በማለትም ሐሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የትግራይ ክልል ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉም እህትና ወንድሞቹን አቅፎ ደግፎ የያዘ፣ ወደፊትም የሚይዝ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎችም አካባቢዎች ከሰሞኑ የደረሰዉ እልቂት ክፉኛ እንዳሳዘናቸው የተናገሩት አቶ ዮሐንስ እየደረሰ ያለዉ ሰቆቃ ሊቆም እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ችግሮች በሰከነ መንገድ እንዲፈቱ የክልሉ መንግሥት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡ በምንም መለኪያ የአማራ ሕዝብ ገፊ አለመሆኑንና በሀገር ዳር ድንበር ማስከበርም ይሁን ቅርሶችን ጠብቆ በማቆየት ለኢትዮጵያ ባለውለታ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአማራውን የፍቅር እና የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወንድም በወንድሙ ላይ በትር ማንሳት ሳይሆን ፍቅር በመስጠት ወደ ሠላም እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አማራው ችግር ሲገጥመው እያሳዩት ላለው መተባበርም አመሥግነዋል፡፡ አማራው ዛሬም ሆነ ነገ ለፍቅርና ለአንድነት በሩ ክፍት በመሆኑ ለሀገር ሠላም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ