“ዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፤ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው!” አዝማሪ ጣዲቄ

187

ባሕር ዳር:የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሕዝቦች ቀንዲል፤ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ብርሃን ለኾነው የነጻነት ድል ምንጭ ኾና የተገኘችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝብ በተለይም ደግሞ አፍሪካዊያን የከፋ የመከራ እና የጨለማ ዘመንን አሳልፈዋል፡፡ ከዚያ ጨለማ ከኾነ የባርነት እና የጭቆና ዘመን ይወጡ፤ በነጻነት ብርሃንም ይመላለሱ ዘንድ የዓድዋን ድል ተምሳሌት፤ ኢትዮጵያን ደግሞ አብነት አደረገላቸው፡፡

የዓድዋ ድል የአንድ ጀምበር የጎራዴ ትርዒት፣ የታንክ እና መድፍ ጩኽት እንዲኹም የሁለት ሀገራት ሕዝብ ጦርነት ብቻ አልነበረም፡፡ የዓድዋ ድል የቆዳ ቀለምን ለይቶ ሥር ለሰደደው የበላይ እና የበታች ትርክት እና ሥነ-ልቦናዊ ጦርነት የማያዳግም ምላሽ የሰጠ የበታችነት ስሜት ፍጹም ወጌሻ ነው፡፡

የዓድዋ ድል “ከእኛ በላይ” ያሉት ልካቸውን አውቀው ማንነታችንን ጠይቀው፣ ተደራጅተው መጥተው፣ ተንጠባጥበው እንዲመለሱ ምክንያት ኾኗል፡፡ አንገታቸውን የደፉትም በወገኖቻቸው ደም በተገኘ ነጻነት ቀና ብለዋል አልፈዋል፡፡ የዓድዋ ድል ዘመን ተሻጋሪ የነጻነት አበርክቶው ከእልፍም እልፍ ያለ ትርጉም ያለው ነው፡፡

የዓድዋ ጦርነት ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር፣ ከሊቃውንት እስከ ቀሳውስት የተሳተፉበት እና ዘርፈ ብዙ ተጋድሎ የተደረገበት ተዓምረኛ ጦርነት ነው፡፡ የአባቶች ጸሎት፣ የእናቶች ምርቃት እና የሕጻናት ሽኝት ዓድዋን ለስኬት አብቅተውታል፡፡ ገበሬው በምርቱ፣ ወጣት በጉልበቱ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ ሙያ ያለው በክህሎቱ በዘመኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለዓድዋ አበርክቶ ያልነበረው ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡

በዓድዋ ጦርነት የላቀ ሚና እና የጎላ ተሳትፎ ከነበራቸው ባለሙያዎች መካከል ዓለም አጫዎቾች ወይም አዝማሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት የላቀ ተሳተፎ ከነበራቸው መካከል የዘመኑ ጥበበኛ የመረጃ ሰዎች እንደ ነበሩ የሚነገርላቸው አዝማሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አዝማሪዎች ስለዓድዋ ጦርነት ሁለት የጎሉ አበርክቶዎች ነበሯቸው ያለን አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የመጀመሪያው ከዓድዋ ትውልድ ውጭ ያለ ሁሉ ልክ በጦርነቱ ሂደት እንደተሳተፈ ኹነቱን በእዝነ ኅሊናው እንዲመለከት ማስቻላቸው ነበር ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በወቅቱ የነበሩትን አርበኞች ሥነ-ልቦና በማጠንከር፤ ንጉሠ ነገሥቱን፣ እቴጌይቱን፣ መኳንንቱን እና ሹማምንቱን በማጀገን አይተኬ ሚና ተጫውተዋል ይላሉ፡፡

በዓድዋ ጦርነት እስከ አውደ ውጊያ የደረሰ እና የላቀ ተሳትፎ ከነበራቸው አዝማሪዎች መካከል አዝማሪ ጣዲቄ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህች ጥበበኛ አዝማሪ ገና ጦርነቱ ሳይጀመር እና ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መስክ ለመፍታት ጥረት ላይ ባለበት ወቅት ጣሊያን ለጊዜ መግደያ እና ለማታለያ እርቅ ብለው ወደ ንጉሱ ሲልኩ ነገሩ ያልጣማት አዝማሪ ጣዲቄ፡-

አውድማው ይለቅለቅ በሮቹም አይራቁ፤
ቀድሞም ያልኾነ ነው ውትፍትፍ ነው እርቁ
ስትል የጦርነቱን አይቀሬነት አስጠንቅቃለች፡፡

ጦርነቱ ሊጀመር ቀናቶች በቀሩት ወቅትም ጦርነቱ ሀገርን እና ክብርን፤ ድንበርን እና ወገንን የማዳን ተልዕኮ ያለው መኾኑን አዝማሪ ጣዲቄ በጥበቧ ጠቁማለች፡፡ ጦርነቱ ድንበር ጥሶ፤ ባሕር አቋርጦ የመጣን ወራሪ ለመመከት የሚደረግ የክብር እና የማንነት ጉዳይ መኾኑን ለማሳየት፡-

ባህር ዘሎ መምጣት ለማንም አይበጅ፤
እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጅ፤
አትረጋም ሀገር ያለ ተወላጅ፡፡
ኸረ ጉዱ በዛ፤ ኸረ ጉዱ በዛ፤
በጀልባ ተሻግሮ ሐበሻን ሊገዛ፤

ስትል ወረራው ክብርን፣ ነጻነትን እና ማንነትን የማስከበር ተጋድሎ ስለመኾኑ ለማሳየት ጥረት አድርጋለች፡፡

አዝማሪ ጣዲቄ በታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት ብስለት እና ብቃት፤ ምጡቅ እና ረቂቅ የኾኑ በርካታ የሽለላ እና የዘፈን ግጥሞችን አርበኞች በተሰባሰቡበት ሁሉ አድርሳለች፡፡ ግጥሞቿ እና የምታስተላልፋቸው መልዕክቶች ንጉሠ ነገሥቱን የሚያነቁ፣ መኳንንቱን እና ሹማምንቱን የሚያስጠነቅቁ እና አርበኞችን ለላቀ ግዳጅ የሚያበቁ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

የአዝማሪ ጣዲቄን ሙያዊ ተጋድሎ ያስተዋለው ሐኪም ሜረብ የተባለው ፈረንሳዊው ከዝነኛው የስፓርታ የጦር ሜዳ ገጣሚ ቲርቴዎስ ጋር አመሳስሏታል፡፡ ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የአዝማሪ ጣዲቄን አበርክቶ እና አስተዋጽኦ ባለመዘንጋት ሽልማቶችን፣ ወይዘሮ የሚል ማዕረግ እና በአዲስ አበባ ጣዲቄ የሚባል የሰፈር ስያሜ ሰጥተዋት እንደ ነበር ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሃፋቸው ጽፈዋል፡፡

ጣዲቄ እና ሌሎች አዝማሪዎች በዓድዋው ጦርነት ወቅት በየዓውደ ውጊያው እና በየጦር ሰፈሩ እየተገኙ ካበረከቷቸው ዘመን ተሻጋሪ ግጥሞች መካከል የተወሰኑት እስከዚህ ትውልድ ድረስ እየወረዱ እና እየተወራረዱ ደርሰዋል፦

ማን እንደ አንተ አርጎታል
የእርሳሱን ጉትቻ
የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ፡፡

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፡፡

ዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፡፡

ምንጭ፡- ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ”፤ ተድላ ዘ ዮሐንስ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከወልወል እስከ ጎንደር”

ዘጋቢ፦ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከፍ ያለው የዓድዋ ዘመን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ዛሬም መደገም አለበት፡፡” የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙሉዓዳም ታምሩ
Next articleበዓድዋ ድል ዘመን የነበረውን አንድነት እና መተባበር ለአሁኑ ዘመን ሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ።