“የእምዬና የእቴጌ ክብር በውጫሌ ሰማይ ሥር”

106

ውጫሌ: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከአምባሰል ተራራዎች ግርጌ፣ ከሚሌ ወንዝ ራስጌ፣ ውበትና ፍቅር ከሞላበት፣ ቆንጆና ልበቀና ከሚወለድበት፣ ደጋጎቹ ከሚኖሩበት፣ የመልካምነት ምንጭ ከሚፈስስበት፣ አንድነት በቅሎ ካደገበት፣ አድጎ ከጎመራበት፣ ማርና ወተት ከመላበት ምድር፣ አንዲት የደመቀች ሥፍራ አለች። ስሟን ታሪክ ያነሳታል፣ ደጋግሞ ያወሳታል፣ በስሟ የሮም አደባባዮች ተጨንቀዋል፣ ነገሥታቱ አንገታቸውን ደፍተዋል፣ መኳንንቱና መሣፍንቱ አብዝተው ተክዘዋል፣ ጎበዛዝቱና ወይዛዝርቱ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ኖረዋል።

በራስጌዋ ያሉት የአንባሰል ተራራዎች የንብ ድምጽ እንደተሰማባቸው፣ ንቦች መልካሙን ነገር እንደቀሰሙባቸው፣ ማር እንደበዛባቸው፣ መልካሙ ማዕዛ እንደተሸተተባቸው፣ የግሸን ሊቃውንት እንደተመላለሱባቸው፣ ስብሐተ እግዚአብሔር እንዳደረሱባቸው፣ ምስጢር እንደገለጡባቸው፣ ከአምላካቸው ዘንድ ለምድር በረከትና ረድኤት እንደለመኑባቸው ይኖራሉ። እኒያ ሰማይ የተመረኮዙ የሚመስሉ ተራራዎች ግርማ አላብሰዋት፣ ጥላ ኾነዋት ይኖራሉ። የአምባሰል ተራራዎች እንደ ንጉሥ ጠባቂ ወታደሮች ለዘመናት ቆመው ያጅቧታል፣ ለዘመናት ጸንተው ግርማ ያላብሷታል፣ ሞገስ ይኾኗታል። እርሷ ወደ ላይ እያየቻቸው፣ እነርሱ ወደታች እያዩዋት ይኖራሉ። ከተራራዎች ግርጌ ትሁን እንጂ እንደተራራ የገዘፈ ታሪክ ይዛለች፣ በጉያዋ ታቅፋለች፣ ስሟን እንዳስጠራች ትኖራለች።

ይህች ሥፍራ በስሟ የሮምን ቤተመንግሥት አስጨንቃለች፣ የዓለም መንግሥታትን ቤት አንኳኩታለች፣ ኃያላን ነን የሚሉትን አስደንብራለች፣ የነጭን ያልተገራ መንገድ ዘግታለች፣ የማይጠግብ ከርስ አስርባለች፣ የጥቁርን ዘር ሁሉ አኩርታለች። የሮማ ጋዜጦች ጽፍውላታል፣ ኃያላኑ ስሟን እያነሱ መክረውባታል፣ ዘክረውባታል። ምን ብናደርግ ይሻላል ሲሉ ተጨንቀው ተጠበውባታል። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣ መኳንንት፣ መሣፍንት፣ የጦር መሪዎች፣ ጦረኞች፣ ጥበበኞች በአንድነት መክረውባታል ታሪካዊቷ ምድር ውጫሌ ይስማ ንጉሥ። ይህች ስም በታሪክ ገናና ናት። የኢትዮጵያ ታሪክ በተዘከረ፣ የዓድዋ ነገር በተነገረ ቁጥር ትነሳለች። ትታወሳለች።

ውጫሌ አስቀድመው ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ ተማከሩባት፣ ውልም አሠሩባት። በኋላም ተጋጩባት። ግጭታቸውንም ሽምግሌ የሚፈታው፣ አንተም አንተም ተው የሚል ገላጋይ የሚያስቆመው አልነበረም። ጠባቸውስ ጥይት የሚያታኩስ፣ ደም የሚያፋስስ፣ አጥንት የሚያስከሰክስ ሕይወት የሚያስገብር፣ ጀብዱ የሚታይበት፣ ጉልበተኛ የሚመረጥበት፣ ልበ ብርቱ የሚፈተንበት ነበር እንጂ።

በዘመነ ምኒልክ ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ በውጫሌ ተዋዋሉ። ውሉም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሀገራቱን በጋራ የሚጠቅም ይሆናል ተብሎ ታስቦበት ነበር። ዳሩ ያ አልነበረም። ከውጫሌ ውል መካከል 17ኛው አንቀጽ በኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ መካከል ከፍተኛ ጠብ ውስጥ አስገባ።” ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” የሚል ኾኖ ሳለ ኢጣሊያ ሌላ ጉዳይ አመጣች። በአማርኛው እና በኢጣልኛው ቋንቋ የተለያየ ትርጉም ያለው ውል አደረገች።

“ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጠባቂነት ውስጥ ነች። ንጉሠ ነገሥቱም በኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ካልሆነ በቀር ከማንም የመንግሥት መሪ ጋር ሊጽፉም፣ ሊዋዋሉም አይችሉም” የሚል አሳሪ የሆነ ነገር ይዛ መጣች። በጦር ሜዳ የማትበገረውን፣ ለነፃነቷ በማንም የማትደፈውን ሀገር በውል ልታስራት ሞከረች። ኢጣሊያ በውጫሌ የተፈራረመችውን ውል በየሀገራቱ ለሚገኙ አምባሳደሮቿ ላከች። ለሚኖሩበት ሀገር መንግሥትም እንዲያሳውቁ አዘዘች። እነርሱም የተባሉትን አደረጉ። የኢጣሊያ መንፈስም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጠባቂነት ሥር ለመሆን ፈቅዳለችና ለወደፊቱ ከእርሷ ጋር ሌሎች መንግሥታት የሚያይርጉት ማናቸውም ግንኙነት ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት እየተላለፈ መፈቀድ አለበት የሚል ነበር። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የማይሆን ነገር ነው። ኢትዮጵያዊ ሀገሩን በውል አሳልፎ አይሰጥምና። ኢትዮጵያዊ ሀገሩንና ነጻነቱን በደምና በአጥንቱ፣ በማትተካ ሕይወቱ ያጸናል እንጂ ለማንም አሳልፎ አይሰጥም።

ንገሠ ነገሥት ምኒልክ በዚያ ዘመን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ለተለያዩ ሀገራት ደብዳቤ ፃፉ። ተክለፃድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መፅሐፋቸው እንደአሰፈሩት የአፄ ምኒልክ ደብዳቤ ሥስት ዋና ዋና ጉዳዮችን የያዘ ነበር። በአፄ ዮሐንስ ፈንታ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን መንግሥታት እንዲያውቁላቸው፣ የሀገራቸውን ፀጥታ ለመጠበቅ እንዲመቻቸው፣ በቤልጄዬም የተደረገው የጦር መሣሪያ እገዳ እንዲነሳላቸው እና በኃያላኑ መንግሥታት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የወዳጅነት እና የንግድ ሥራ እንዲስፋፋ የሚል ነበር።

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለፃፉት ደብዳቤ የተመለሰላቸው መልስ ግን የጠበቁት አልነበረም። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በሥሯ እንዳደረገቻት አድርጋ ተናግራ ነበርና ለክብራቸው የሚመጥን መልስ አልተመለሰላቸውም። ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ክብር የማይመጥን መልስ ንጉሡን አበሳጫቸው። ተበሳጭተውም ዝም አላሉም። በውጫሌ ውል የተፈረመው ውል የአተረጓጎም ሥሕተት እንዳለበት የሚያሳውቅ ደብዳቤ ፃፉ።

“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መሆኔን ለወዳጆቼ ለውጭ መንግሥታት አስተላልፌው ስለነበረው የመጣልኝ መልስ አዋራጅ ነገር ይገኝበታል። ሰበቡም 17ኛው አንቀጽ ነው። ይኸም አንቀጽ የኢጣልያንኛው አባባል ከአማርኛው የተለየ ነው። ያንንም ውል ሳደርግ በአውሮፓ ምስጢሩ የጠበቀ እንዲሆንና እንዲቃና ስል አደረግሁት እንጂ ምንም የሚያስገድደኝ ነገር የለም። አንድ ነፃ የሆነ ሀገር በወዳጅነት ካልሆነ በቀር ምንም የሚያስገድደው እንደሌለ ግርማዊነትዎ ያውቀዋል። ስለዚህ ስለወዳጅዎ ክብር ሲሉ ይህ አንቀጽ እንዲታረምና ለአስተላለፉላቸው የወዳጅ ሀገሮች ይኸንኑ ስሕተት ገልጸው እንዲጽፉላቸው ተስፋ አለኝ” የሚል ደብዳቤ ፃፉ።

ኢጣሊያ አንድ ጊዜ ለመንግሥታት አሳውቄያለሁና ለክብሬ አይመጥንም ስትል አልሰርዝም አለች። ኢትዮጵያም ማንም ሀገር የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት ሊገፋ አይቻለውም አለች። ይባስ ብለው የኢጣሊያ ጋዜጦች “ምኒልክ ውል የማያከብሩ ሀገሪቱ ሥርዓት የማታውቅ ሕዝቡ ገና ካረመኔነት ያልተላቀቀ ሽፍታና የባርያ ንግድ የሚያዘወትር ነውና ልናሰለጥነው ይገባል” እያሉ ይጽፉ ጀመር። ይህ ለአንድ እንደምኒልክ ላለ ስልጡን እና ኩሩ መሪ የሚያበሳጭና የሚያሳምም ነበር።

ውሉ መካረርን፣ መካረሩ ጦርነትን ወለደ። የሮም አደባባዮች በሚያጋሱ ጦረኞች ተመሉ። መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ንጉሣቸውን አጅበው በግርማ ታዩ። ጦሩ ታዘዘ። በድል እንደሚመለስም ተማመኑ። እምነታቸው ጥርጥር አልነበረውም። ኢትዮጵያ የኢጣልያን ክንድ ትመክታለች ብለው አላሰቡምና። ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱ ሠራዊቱን አሞገሱ፣ አወደሱ። ኢትዮጵያን ድል አድርጎ የኢጣሊያን ክብር ከፍ ከፍ እንዲያደርግ፣ ስሟን በዓለም እንዲያናኝ ተመኙለት። ሠራዊቱ ባሕር ሠንጥቆ የብስ አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ገሰገሰ።

በአስፈሪው ዙፋን ላይ የተቀመጡት እምዬ ምኒልክ፣ ከባለቤታቸው ከእቴጌ ጣይቱ፣ ከመኳንንቶታቸቸው፣ ከመሣፍንቶቻቸውና ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር ተመካክረው ለጦርነቱ ተዘጋጁ። በአንዲት አዋጅ ሕዝባቸውን ከዳር ዳር አሰባሰቡ። የኢጣልያን ወደ ኢትዮጵያ መዝመት ያዩና የሰሙ ኃያላን ሀገራት ወዮላት ለዚያች ደኃ ሀገር፣ የኢጣልያ ክንድ አደቀቃት፣ የኢጣልያ አፈሙዝ በላት አሉ።

የኢጣልያ መንግሥት ምኒልክን አሸንፎ ኢትዮጵያን አስገብሮ፣ በሮም ሥር እንድትተዳደር አድርጎ አዋጅ የሚያስነግርበትን ቀን በጉጉት ጠበቁ። ዳሩ በጉጉት የጠበቁት ቀርቶ አንገታቸውን የደፉበት ዜና ከወደ ኢትዮጵያ ሰሙ።

በምኒልክ አዋጅ የተሰባበሰው የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት አቧራውን እያጨሰ፣ እንደ ነበር ተቆጥቶ፣ እንደ አምበሳ አግሥቶ ኢጣልያ አለች ወደ ተባለበት ሥፍራ ገሰገሰ። የውጫሌ ውል ያመጣው ጣጣ ነፃነቴን አላስደፍርም ባለ ሕዝብና ከእኔ በላይ ጉልበተኛ በሚል መንግሥት መካከል ጦርነት አስነሳ። የኢትዮጵያ ጦር በቁጣ ገሰገሰ። ኢጣልያንም አገኛት፣ እንዳልነበር አደረጋት። እየደመሰሳት ወደፊት በግርማ ተጓዘ። የኢትዮጵያ ክብርና ልእልና ከፍ ወደ አለበት ተራራ ተጠጋ። ኃያሉ ጦርነት ተካሄደ። ኢትዮጵያ ኢጣልያን አንበረከከች፣ በሮም አደባባይ ያገሱት ወታደሮች በኢትዮጵያ ጀግኖች ጎራዴ ተቀንጥሰው፣ በጦራቸው ተወግተው ዳግም ላይነሱ ወደቁ፣ ከጎራዴ ፍላፃ የተረፉት እጃቸውን ሰጡ። የኢትዮጵያ ጀግኖች በድል አድራጊነት ተመላለሱ፣ ፎከሩ ሸለሉ፣ ሠንደቃቸውን ከከበረው ተራራ አናት ላይ ከፍ አድርገው አውለበለቡ።

በዚህ ድል ሮም ደነገጠች፣ በጨለማ ተዋጠች፣ በፍርሃት ችንካር ተቸነከረች፣ የዓለም መንግሥታት ያልጠበቁት ኾነባቸው። ኢትዮጵያ እኩልነትን በክንዷ አወጀች፣ የነጭ የበላይነትን ገረሰሰች። ምኒልክ እና እቴጌ ደስታቸው ከፍ አለ። አምላካቸውንም አመሰገኑ። ሀገር በአንድነት መርተው የዓድዋን ድል ያስገኙት እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከፍ ከፍ እያሉ ተከበሩ። ለታላቅ ሥራቸው፣ ጥበብ ለበዛበት አበርክቷቸው ትውልድ አሁን ድረስ እናቴ አባቴ እያለ ያወድሳቸዋል። በመንፈሳቸው ይገዛላቸዋል። ድል ያመጡበትን ቀንም እያሰበ የዓድዋን የድል በዓል ያከብራል። ይዘክራል።

ብዙ ሀገራት ነፃ የወጡበትን ቀን ያከብራሉ ኢትዮጵያ ግን ነፃነቷን ያላሳድፈረችበትን የድል በዓል ታከብራለች ትዘክራለች፣ ሌሎች ሀገራት ከነፃነት ወዲያ፣ ነፃነት አጥተን በነበርነበት፣ በባርነት የቆየንበት፣ ከነፃነት ወዲህ እያሉ ያወራሉ፣ ታሪክም ይጽፋሉ። ኢትዮጵያ ግን ለዘመናት የነፃነት ታሪኳን ትዘክራለች። የእርሷን ነፃነት የደፈረ፣ እደፍራለሁ ብሎም የኖረ የለምና። ኢትዮጵያ የድል ሀገር፣ ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ምድር፣ ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ፊት ግርማን የተላበሰች፣ ኢትዮጵያ ክብሯን ሳታስደፍር የኖረች፣ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ሁሉ የቀጣች፣ ኢትዮጵያ ለተጨቆኑት የደረሰች፣ ተስፋ ላጡት ተስፋ የሆነች፣ ኢትዮጵያ እኩልነትን ያመጣች፣ ኢትዮጵያ ነጭን አሳምራ የገረፈች፣ ወደ ልኩ ያስገባች ድንቅና ብርቅ ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ በዓለሙ ሁሉ ደምቃ የታየችበትን በዓል ዓድዋን ትዘክራለች፣ ታከብራለች። ዓድዋ ዝም ብሎ በዓል አይደለም። ዓድዋ የኢትዮጵያ ጀግኖች ገድል የታየበት፣ የእምዬ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ የመምራት ጥበብ የተመሠከረበት፣ የነጭ የበላይነት እና የአልጠግብ ባይነት ግስጋሴ የተሰባበረበት፣ የኢትዮጵያ ክብርና ልእልና በዓለሙ ሁሉ የናኘበት፣ ተሰፋ ያጣው ተስፋ ያገኘበት፣ ነጭ ያፈረበት፣ ጥቁር የኮራበት፣ ዓለም አዲስ ነገር ያየበት በዓል ነው። ዓድዋ የገዘፈ ታሪክ ያለው፣ የኢትዮጵያን አስፈሪነት በየጠላቶቿ ልብ ሁሉ የፃፈ፣ ያፃፈ ኃይል የድል በዓል ነው።

ይህ የድል በዓል በተገኘበት፣ የኢጣሊያ ሠራዊት በዓድዋ ተራራ ላይ እንደ ዱቄት በተበተነበት፣ የኢትዮጵያ አናብስት ድል አድርገው በአገሱበት፣ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከፍ ብላ በተውለበለበችበት፣ ኢትዮጵያ በኩራት ከፍ ከፍ ባለችበት፣ ኢጣሊያ በሃፍረት ዝቅ ዝቅ ባለችበት ቀን በየካቲት 23 ይከበራል። በጥበብ መርተው፣ በሞገስ ዘምተውና አዝምተው ድሉን ያመጡት፣ ኢትዮጵያዊነትን ያጸኑት እምዬና እቴጌ በአምባሰል ሰማይ ሥር ተከብረዋል። በአምባሰል ሰማይ ሥር በግርማ ተቀምጠዋል። ከዓመታት በፊት በተቀመጡባት፣ የውጫሌ ውልን በመከሩባት ሥፍራ በይስማ ንጉሥ ከፍ ከፍ ብለዋል። እንደ አምባሰል ተራራዎች የገዘፈ ታሪክ የሠሩት፣ በዓድዋ ተራራ ላይ ሌላ ተራራ የኾነ ታሪክ ያስቀመጡት እምዬና እቴጌ ስለ ክብራቸው ሐውልት ተቀምጦላቸዋል።

ትውልድ በውጫሌ ሰማይ ሥር የከበሩትን፣ በክብር የተቀመጡትን ንጉሥና ንግሥቷን እያዬ ታሪካቸውን ይማራል፣ በክብራቸው ይከበራል፣ በሥራቸው ሲኮራ ይኖራል። የእነርሱን ስምና ዝና እያነሳ የራሱን ታሪክ ይሠራል። የእነርሱን ታሪክም ይጠብቃል። እነኾ ንጉሡና ንግሥቱ እንደተራራ የገዘፈ ታሪክ ታቅፈው በአምባሰል ተራራዎች ግርጌ ተቀምጠዋል።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ የካቲት 20/2015 ዓ.ም ዕትም
Next article“ከፍ ያለው የዓድዋ ዘመን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ዛሬም መደገም አለበት፡፡” የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙሉዓዳም ታምሩ