
ባሕርዳር: የካቲት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተሳሳተ ዘመን የተወለድከው ትክክለኛው ሠው እያለ ታሪክ የሚያወሳህ፣ ትውልድ የሚኮራብህ፣ በልቡ ላይ አስቀምጦ ያኖረህ፣ ቃልህን እየደጋገመ የሚያነሳልህ ኃያሉ ንጉሥ ኾይ ኢትዮጵያን እንደምን አድርገህ ወደድካት? የተበተነ የመሰለውን የሰበሰብከው፣ አስፈሪውን ዙፋን የመለስከው፣ የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና ከፍ ከፍ ያደረከው፣ ኢትዮጵያን በጠላቶቿ ፊት ግርማ ያላበስካት፣ ዋስና ጠበቃ የሆንካት፣ ከነብስህ በላይ የወደድካት፣ ምቾትህን ትተህ የተንከራተትክላት፣ ሞት በበዛባቸው ጎዳናዎች ሁሉ የተመላለስክላት ንጉሥ ኾይ የሀገር መውደድ ልኩ እስከምን ድረስ ነው?
በልጅነት ያሰብካት፣ በወጣትነት ዘመን የጠበካት፣ በጉልምስና ዘመን ያከበርካት፣ ያስከበርካት ታላቁ ንጉሥ ኾይ ኢትዮጵያ በልብህ ውስጥ እንዴት ነበረች? እንዴት ብላስ ተቀምጣ ኖረች? እንከፋፍልሽ ያሉትን ቀጣኻቸው፣ በክብሯ የመጡትን ገሰጽካቸው። ኢትዮጵያ የማትደፈር እና የማትነካ መኾኗን አሳየኻቸው፡፡
ጠጅና ወይኑ ሳይነጥፍብህ፣ ጮማው በአዳራሹ ሳይጠፋብህ፣ ለጉሮሮህ የሚጣፍጥ ሳይታጣ ስለ ፍቅሯ ባሩድ የጠጣህላት፣ የሽጉጥ እርሳስ የተጎነጨህላት ንጉሥ ኾይ ሀገርህን እንዴት አድርገህ ብትወዳት ነው? በፍስሃ ዘመን የወደድካት፣ በመከራ ዘመንም ያፈቀርካት፣ ለፍቅሯ ስትል ራስህን ለመስዋዕትነት ያቀረብክላት፤ አባ ታጠቅ ኢትዮጵያን እንዴት ትገልጻት ነበር?
የአባቶቹ የእነ ፋሲል ቤተመንግሥት እያለለት፣ ያማረው የዙፋን ቤት አስቀድሞ ተሰርቶለት፣ ሠገነቱ ተስተካክሎለት፣ የግብር ማብያው አምሮ ተውቦለት፣ ያየውን ሁሉ የሚያሳሳ መናገሻ ሳይቸግረው እርሱ ግን እንደመንገደኛ በድንኳን ተቀመጠ፡፡ በዙፋኑ ተቀምጦ፣ በዘውዱ አጊጦ፣ በትረ መንግሥቱን ጨብጦ፣ በግራና በቀኝ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ፣ በጦር አበጋዞቹና በሊቃውንቱ ተከቦ መኖር ሲችል እርሱ ግን በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ያለ ዕረፍት ተመላለሰ፡፡
ለእማማ ኢትዮጵያ የፍቅሩን ልክ ሊያሳያት፣ የክብሯን ደረጃ ሊገልጥላት ስለ ወደደ ዘመኑን ሙሉ ለእርሷ ሠጣት፤ አብዝቶ ወደዳት፣ ለእርሷ የተመቸውንና የተገባውን ራዕይ ዕውን ያደርግ ዘንድ ደከመላት ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ፡፡
ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር ከመኾን አልፋ የቆዬን ስልጣኔ ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር አጣምራ የያዘች ሀገር ትኾን ዘንድ የበዛ ጥረት አድርጓል፡፡ ጠላት የሚበረክትባት፣ አቅም አለኝ ብሎ ያሰበ ሁሉ ነፍጥ የሚያነሳባት ኢትዮጵያ ሀገሩ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁና ዘመኑን የዋጀ ስልጠና የወሰዱ ወታደሮች ይኖሯት ዘንድ ጥሯል፡፡ ግንባራቸው የማይታጠፍ ጀግና ልጆች ያሏት ኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቀች ጊዜ ማንም እንደማይደፍራት ያውቃልና፡፡
ይህን ሕልሙን እውን ያደርግባት፣ ራዕዩን ይኖርባት ዘንድ የወደዳትና የመረጣት ከተማ ደግሞ ደብረ ታቦር ነበረች፡፡ ደብረ ታቦር የቴዎድሮስ ራዕይ የፈነጠቀባት፣ ያልተቋጨው ራዕዩ የተቀመጠባት፣ ዘመናዊነት ከፍ ብሎ የታየባት፣ የቴዎድሮስ ተስፋ እውን መኾን የጀመረባት ታላቅ ከተማ ናት፡፡
በዚህች ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ጋፋት በዘመኑ ግሩም ያስባለ ጥበብ ታየባት፣ ቴዎድሮስ ያዘዛቸው፣ ሕልሙን ዕውን ያደርጉለት ዘንድ ያሰማራቸው ጥበበኞች ኖሩባት፣ የተስፋ ብርሃንም አበሩባት፡፡ ጋፋት የንጉሡን የዘመናዊነት ተሞክሮ እና ሕልም የሚያመላክት ታሪካዊ ስፍራ ናት ይሏታል፡፡ ጋፋት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መሠረት የተጣለባት፣ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ጨረር የተወረወረባት ሥፍራ ናት ይሏታል፡፡
ቴዎድሮስ የውጭ ቴክኖሎጂን፣ አዳዲስ ሃሳቦችን እና የፈጠራ ሥራዎችን የመቀበል ጉጉት የነበረው ኃያል መሪ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ እንደ አካሉ ሁሉ ጠንካራ የአዕምሮ ኃይል የነበረው በዘመኑ ከፍተኛ ዕውቅት የኾነውን የሀገሩን ዕውቀት በጥልቀት የተማረ ታላቅ መሪ ነበር፡፡
አቤ ጉበኛ በእርሱ ዘመን የነበረውን ቆንስል ፕላውዴንን ጠቅሰው ቴዎድሮስን ሲገልጿቸውʺ የአዕምሮና የአካል ጥንካሬያቸው ድካም አይሰማቸውም፡፡ የመንፈሳቸው እና የአካላቸው ድፍረት ወሰን የለውም፡፡ ሠርተው አይታክታቸውም፡፡ ቀን ይሁን ሌሊት የሚያርፉት በትንሹ ነው፡፡ ሐሳባቸውና የቋንቋ አገላለጻቸው የተጣሩና በአጭሩ ለመረዳት የሚችሉ ናቸው፡፡ ማመንታት በእርሳቸው ዘንድ አይታወቅም፡፡ “ብለዋል፡፡ ቴዎድሮስ ፍርሃትና ማመንታት ብሎ ነገር አያውቅም፡፡ ያመነበትን ያደርጋል፤ የፈለገውን ይፈጽም ዘንድ ያለ መሰልቸት ይሠራል፡፡ ለዚያም ነው በዚያ ዘመን የማይሞከር የሚመስለውን የሞከረው፡፡
ቴዎድሮስ የሀገሩን ክብርና ዕውቀት በደንብ የተረዳ፣ የውጭውን ዓለም ስልጣኔ የተገነዘበ ነበር፡፡ በተለይም የአውሮፓውያንን ስልጣኔ ብቻ ሳይኾን የክፋት አካሄዳቸውንም በሚገባ ያወቀ ብልህም ነበር፡፡
“የአውሮፓን መንግሥታት የተንኮል ብልሐት አውቀዋለሁ፡፡ የምሥራቃዊውን ዓለም አንድ ክፍለ ሀገር ለመያዝ በሚፈልጉ ጊዜ መጀመሪያ ሚሲዮናውያንን ይልካሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሚሲዮናውያንን የሚያጠናክሩ ቆንስሎች ይልካሉ፡፡ በመጨረሻም የጦር ወታደሮችን ይልካሉ፡፡ እኔ በዚህ የምታለል የሂንዱስታን ራጂ አይደለሁም፡፡ ከሁሉ አስቀድመው ወታደሮች መጥተው እነርሱን መግጠም እመርጣለሁ፡፡ ” ይልም ነበር፡፡ ለዚህም ነው እርሱ የዘመነ ወታደር ይኖረው ዘንድ የበረታው፡፡
ቴዎድሮስ ራዕዩን ባስቀመጠባት ደብረታቦር ከተማ የተመሠረተው የደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የቴዎድሮስን ራዕይ ለማስቀጠል እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዉ ሴባስቶፖል የተሠራባትን ከተማ ስልጣኔን ለማስቀጠል ሮኬት ሞክሮባታል፡፡ ዘመኑን የዋጀ መሳሪያ በኢትዮጵያ ይኖር ዘንድ እየሠራባት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በጋፋት ስም ማዕከል ከፍቶ የቀደመውን ስልጣኔ ለማስቀጠል እየሠራ ነው፡፡
በደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የጋፋት የህዋ ምህንድስና ልማት ማዕከል አስተባባሪ በለጠ ጌታቸው ጋፋት የሚለውን ስም ስንሰማ በመጀመሪያ በአዕምሮአችን የሚመጣው የታታሪው ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ መድፍ ሥራ ነው ይላሉ፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ መድፍ መድፍ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በጋፋት ሥር የወጣች የጥቁር ሕዝብን ዓይን ልትገልጥ የሥልጣኔን ቀለም ልታሳየን ብልጭ ያለች ፀሐይ ናት እንጂ ነው የሚሉት።
መድፉ የራዕዩን ጨረር ወስዶ በጠላት ላይ ተፋው። የቴዎድሮስ መድፍ ከናሳ ሮኬቶች መቶ ዓመታትን ከሂትለር መድፎች አንድ ክፍለ ዘመንን ይቀድማልም ብለውኛል። መድፉ ከጦር መሳሪያነት ባሻገር ከበኋላው ብዙ የዕውቀት ብልጭታ ይዟል ነው ያሉት፡፡ በታሪክ አንደኛው ጅምሮ ተከታዩ እንደሚያስቀጥል ያነሱት አስተባበሪው ለአብነት የሩስያን ሕዝቦች ስልጣኔ መነሻ እና መድረሻ ማየት በቂ ነው ይላሉ፡፡ የሩሲያ ስልጣኔ በታላቁ ፒተር አንደኛ ተጀምሮ በፑቲን ቀጥሏል ነው የሚሉት። ታሪክ ቀለም ነው፤ አቧራው፣ ዝናቡ፣ ጠላትም ያደበዝዘዋል፤ ለዚህም የታሪክ ባለቤቶች ታሪካቸውን በየሰዓቱ ፣በየቀኑ መቀስቀስ እና ታሪክ እየሠሩ ታሪካቸውን እንዳይደበዝዝ መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቴዎድሮስን የስልጣኔ ጉዞና ሕልም እየቀሰቀሰ የተኛውን እያነቃ፣ ጉሙ እና አቧራውን እያጸዳ ኑ ወደ ፀሐያችን እንሂድ እያለ መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጀመረው እንቅስቃሴ የመንኮራኩር ድምፅ ማሰማቱንም አስታውሰዋል፡፡ ሰማያችን በልጆቻችን የእጅ ሥራ ልንለካ፣ ከዋክብትን በራሳችን ምሁራን ልንቆጥር፣ የአፄ ቴዎድሮስን መንፈስ እየቀሰቀሰን ህሊናችንን እና ክብራችን ከፍ አድርገን ለመስቀል ተነስተናልም ብለውኛል፡፡
ስልጡን ሕዝቦች ነን የሚሉት አስተባባሪው ስልጣኔውን ማስቀጠል የዚህ ዘመን ድርሻ እንደኾነም ያነሳሉ፡፡ ቴዎድሮስ አይሞከርም በተባለበት ዘመን ሞክሮ በጋፋት ሰማይ ሥር ድንቅ ነገርን እንዳሳዬ ሁሉ ዛሬም የእርሱ ልጆች ድንቅ ነገርን ከመሥራት የሚያቆማቸው የለም፡፡ ለምን የስልጡን ልጆች ናቸውና፡፡
“ቴዎድሮስ የዛሬውን እና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልድ በመንፈስ ይገዙታልʺ እንዳሉ አቤ ጉበኛ ቴዎድሮስ ዘመን የማይሽረው፣ ተራራ የማይጋርደው፣ ትውልድ የማይረሳው ራዕይ የታጠቀ ነበርና በራዕዩ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን ይገዛዋል፡፡ ለእርሱ የተገዛ ትውልድም ራዕዩን ያስቀጥላል፣ ቴዎድሮስ የወደዳትን፣ ያከበራትን፣ ከፍ ከፍ ያደረጋት ኢትዮጵያን ይወዳል፤ ለክብሯ ይኖራል፡፡
ሴባስቶፖል የተሠራባት ሮኬት የተሞከረባት ደብረታቦርም የተደበቀውን ራዕይ እያወጣች ዘመኑን እንደምትዋጅ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!