
አዲስ አበባ: የካቲት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በጉባኤዉ ከ53 አባል ሀገራት 353 ዲፕሎማቶች ተሳታፊ እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
36ተኛው የአፍሪካ ኅብረት ስኬታማ በኾነ እና አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነትን ባፀና መልኩ መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም ተናግረዋል።
ይህ ጉባኤ በተሳትፎ፣ በአጀንዳ እና በኹኔታ ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጋር የሚመሳሰል መኾኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። በዚህ ጉባኤ በማዕቀብ ውስጥ ካሉት በስተቀር 53 የአባል ሀገራቱ አባላት ተሳትፈዋል፡፡ የ22 ሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ 6 አባል ያልኾኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና 2 ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ 358 ዲፕሎማቶች እና 297 ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
ጉባኤው በ1 ሺህ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሽፋን አግኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች 332 ናቸው። ለጉባኤው ከተደረጉ መደበኛ በረራዎች ውጪ 43 ቻርተር በረራዎች ወደ አዲስ አበባ ተደርገዋል። 3 የጎንዮሽ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተከናውነዋል፡፡
በ36ተኛው የኅብረቱ ጉባኤ 47 አጀንዳዎች የነበሩ ሲኾን ኢትዮጵያ በ20ዎቹ ላይ ተሳትፋ ሀገራዊ ጥቅሞቿን አስከብራለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ.ር) ከ20 ሀገራት መሪዎች እና የድርጅት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል። በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ከ20 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ዲፕሎማቶች ጋር ውይይት አድርገዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮዮጵያ በሰላም ያዘጋጀችው ጉባኤ ከተመድ ጉባኤ ጋር ሊስተካከል የሚችል ተሳትፎ ተደርጎበት መጠናቀቁም ተገልጿል። ለዚህም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ አካላትን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ አመስግኗል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!