
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ወሎ ዞን በአፋርና አማራ ክልሎች አጎራባች ቀበሌዎች ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የአንበጣ መንጋውን በሙሉ አቅም ለመከላከል እንዳስቸገራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
የበረሃ አንበጣው በተከሰተባቸው የሀብሩ እና ራያ ቆቦ ወረዳዎች ላይ በእንስሳት መኖ እና በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ መነሻውን ከየመን እንዳደረገ የሚነገረው የበረሃ አንበጣ መንጋ ካለፈው ሰኔ ጀምሮ በአካባቢው መከሰቱን የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ በቂ የቅድመ መከላከል ሥራ ባለመሠራቱ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑንም ነው በሀብሩ ወረዳ ድሬ ሮቃ ቀበሌ አብመድ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ያመለከቱት፡፡
በአማራ እና አፋር ክልሎች ባሉ አጎራባች የአፋር ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋው ኩብኩባ በሚባለው የዕድገት ደረጃ ላይ እያለ አርሶ አደሮቹ ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተፈለገው መጠን የአንበጣ መንጋውን ማጥፋት አለመቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ የበረሃ አንበጣው ክንፍ አውጥቶ መብረር በመጀመሩ የጉዳት መጠኑን እንደጨመረውም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው የተሰማራ ቢሆንም ስምሪቱ በተወሰኑ አካባቢዎች የተወሰነ በመሆኑ የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮቹ ለመከላከል እንደተቸገሩም ነው አስተያዬት የሰጡት፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን የአንበጣውን መንጋ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመከላከል ሥራው አርሶ አደሮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ እና አፋር አጎራባች ቀበሌዎች የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የአንበጣ መንጋውን ከጅምሩ ለመከላከል እንዳላስቻለ ያስታወቁት ዋና አስተዳዳሪው በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ይሠራል ብለዋል፡፡ ግጭት በተነሳባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማካተት የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም ወልዲያ ላይ የምክክር መድረክ በማካሄድ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት አለማድረሱንና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን አፋር ክልል አጎራባች ወረዳዎች የተከሰተው ችግር ደግሞ አሁንም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ክፍሉ ሞገስ