
ባሕር ዳር: የካቲት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ያን ጊዜ ከተማዋን ዋይታ ሞላት፣ የደም ጎርፍ አጥለቀለቃትʺ
ከተማዋ በዋይታ ተሞላች፣ በለቅሶ ተናጠች፣ በተኩስ ድምጽ ተጨነቀች፣ የደም ጎርፍ አጥለቀለቃት፣ የንፁሐን ሬሳ ከበባት፡፡ ጨካኝ እጆች ንፁሐንን ገደሏቸው፣ መከራውን አጸኑባቸው፤ እንደ ዱር እንስሳት እያደኑ ገደሏቸው፣ መጠጊያ እንዳይኖራቸው ቤታቸውን እያቃጠሉ አሰቃዩዋቸው፣ ከእሳት ለማምለጥ የሚጣደፉትን ከዳር ቆመው በጥይት አረር ቆሏቸው፡፡ ነብሳቸው አብዝታ ተቅበዘበዘች፣ መድረሻም አጣች፡፡
በከተማዋ የተገኙ ኢትዮጵያውያን የግፍ ጽዋ ተቀበሉ፣ በግፍ እየተገደሉ፣ በግፍ ተጣሉ፡፡ አዲስ አበባ ቤቶችን እያቃጠለ በሚነድድ እሳት፣ በጦር ተወግቶ፣ በጥይት ተመትቶ በሚየቃስት የሰው ድምጽ ተመላች፡፡ በቤት ውስጥ ያሉትን እሳት፣ ከቤት የወጡትን ጥይት በላቸው፡፡ የቃጠሎው ጭስ እያፈነ ከጠላት እጅ ላይ ጣላቸው፡፡
በአዲስ አበባ ሰማይ ሥር ጀንበር በእኩለ ቀን የጨለመች፣ ብርሃኗን አጥፍታ ወደ መስኮቷ የገባች መሰለች፡፡ ጎዳናዎችን የደም ጎርፍ አጥለቀለቃቸው፣ የንፁሐን ሬሳ ሞላቸው፣ ከተማዋን ጭስ አፈናት፣ ጥይትና ነዲድ በዛበት፡፡
ንጉሡ ተሰደው፣ የጦር አበጋዞች ገሚሶቹ ስለ ሀገራቸው ተሰውተው፣ ገሚሶቹ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ከጠላት ጋር እየተናነቁ ነበር፡፡ እምብኝ ለሀገሬ ያሉ ጀግኖች ልጆቻቸውን ትተው፣ የሞቀ ቤታቸውን ረስተው፣ ለአንዲት ሀገር ፍቅር፣ ለአንዲት ሠንደቅ ክብር ሲሉ ዱር ቤቴ ብለዋል፡፡ ኮቸሮ በልተው፣ የኮዳ ውኃ ተካፍለው ጠጥተው ውለው እያደሩ ከጠላት ጋር ትንቅንቅ ገጥመዋል፡፡
የሀገሬው ሰው ከመጠቃት መሞት ይሻላል፣ ተዋርዶ ከመኖር ተከብሮ መሞት ይልቃል እያለ ለእናት ሀገር ፍቅር ውድ ሕይወቱን እየሰጣት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች፣ ጋራና ሸንተረሮች፣ ዳገት ቁልቁለቶች የጠላት ሬሳ እየወደቀባቸው፣ ጀግኖች የጠላትን ግንባር እየመቱባቸው፣ የልባቸውን እየሠሩባቸው ውለው ያድራሉ፡፡
ወረኃ የካቲት ደርሷል፡፡ ቀኑ በክርስቲያኖች ዘንድ በዓለ ሚካኤል የሚታሰብበት ነበር–የካቲት 12፡፡ ለወትሮው በበዓለ ሚካኤል በየአድባራቱና በየገዳማት ማሕሌቱ ደምቆ ያድራል፣ ሊቃውንቱ ሲዘምሩ፣ አምላካቸውን ሲያመሰግኑ ያነጋሉ፡፡ በዚያ ዘመን ግን ጠላት መጥቷልና እንደቀደመው ሁሉ ማሕሌት መቆሙ ኪዳን ማድረሱ፣ ቅዳሴ መቀደሱ፣ ማስቀደሱ እንደቀደመው አልኾነም፡፡ ሀገር ሰላም ባልሆነችበት፣ ቤተክርስቲያን በጠላቶች ዓይነ ቁራኛ በገባችበት ጊዜ ስርዓቱ እንደቀደመው አይሆንም፡፡ ቀሳውስቱ ቢገኙ፣ ዲያቆናቱ ለአገልግሎት ቢፋጠኑ እንኳን ምዕመናኑ እንደ አሻቸው አይሄዱም፣ ከአምላካቸው ጋር በቤቱ አይገናኙም፡፡ ለምን በሀገር ላይ ጠላት ተነስቷል፣ ግፉ በዝቷልና፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ጠላት ደፍሮባቸው እንቅልፍ አልወስዳቸው፣ ምግብ አልበላቸው፣ ውኃ ከጉሮሮዓቸው አልወርድ ብሏቸዋል፡፡ እልህ እየተናነቃቸው፣ የሀገር ፍቅር እያነደዳቸው ነው፡፡ የኢጣሊያ ግፍ ሕዝቡን ቂም እንዲይዝ፣ ጨክኖም እንዲዋጋቸው አድርጓል፡፡
በዚያ ዘመን በኢጣሊያ ግፍ አብዝተው ከተንገበገቡት መካከል አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ነበሩ፡፡ አብርሃ ደቦጭና መገስ አስገዶም ስለ ኢጣሊያ ግፍ ማውጋት እና ማንሰላሰል ከጀመሩ ዋል እድር ብለዋል፡፡ ኢጣሊያኖችንም ለመበቀል ቆረጡ፡፡ ቃል ኪዳንም አሠሩ፡፡ ስለቦምብ አጣጣል ተማሩ፡፡ ተለማመዱ፡፡ ክንዳቸውን አጠነከሩ፡፡
ግራዚያኒ የኔፕልስ ልዕልት ወልዳለችና የደስታ መግለጫ አወጣለሁ ብሎ ሽርጉድ ላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ሀገራቸው በምጥ ተይዛባቸው ተጨንቀዋል፡፡ ኢጣሊያናውያን ደግሞ የኔፕልስ ልዕልት ወልዳላቸው በደስታ ተሞልተዋል፡፡ በአንዲት እናት ሀገር እና በአንዲት ልዕልት መካከል ያለው ልዩነት ያልገባው ግራዚያኒ ሀገራቸው ምጥ በተያዘችባቸው ኢትዮጵያውያን ምድር የደስታ መግለጫ ላውጣ አለ፡፡ ሀገር ተደፍራባቸው፣ ወገኖቻቸው በዱር በየገደሉ እየተንከራተቱባቸው፣ ንጉሡ ከዙፋኑ ተነስተውባቸው ካዘኑ ሰዎች ፊት የደስታ መግለጫ ላውጣ ብሎ ማሰቡ ሕመም ነበር፡፡ ግራዚያኒ ሰው በቤተ መንግሥት እንዲሰባሰብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የግራዚያኒን ትዕዛዝና የደስታ መግለጫ ቀን የሚሰጥበትን ደግሞ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ሰምተዋል፡፡ ያን የመሠለ ወርቃማ እድል ማሳለፍ አልፈለጉም፡፡ ስነ ስርዓቱ ከሚከወንበት ጊዜ ቀደም ብለው ወደ ቤተመንግሥት አቀኑ፡፡ ሁለቱም ቦምብ ይዘዋል፡፡ ግራዚያኒ በከፋውና ንዴት በአፈነው ሕዝብ ፊት ተኮፍሶ የደስታ መግለጫ ሊሰጥ ከመኳንንት እና ከትትልቅ ባለሰልጣናት ጋር በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ተቀምጧል፡፡ አብርሃ እና ሞገስ ሕልማቸውን እውን ሊያደርጉ፣ ግራዚያኒን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላት የሆኑ ሹማምንትን በኪሳቸው በያዟት ቦምብ እስከ ወዲያኛው ሊሸኙ ጊዜ እየጠበቁ ነው፡፡ አይደርስ የለም ጊዜው ደረሰ፡፡ ቦንቦችን ፈልቅቀው ወረወሯቸው፣ ነገሩ ሁሉ ተደበላለቀ፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ቦንቦቹን ጥለው ከቤተመንግሥት አመለጡ፡፡ ግራዚያኒ እና ሌሎች ቆሰሉ፡፡
ጨካኝ የላከው የጨካኝ መልእክተኛ ግራዚያኒ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የግፍ ትዕዛዝ አዘዘ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው በወቅቱ አዲስ አበባ የነበረውን ሐንጋሪያዊውን ሐኪም ዶክተር ላዲስላስ ላቫን ጠቅሰው ሲጽፉ ʺ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰላምና በፍቅር ከቤተ መንግሥት ግቢ ተሰባሰቡ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግራዚያኒ እና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ቦምቦች ተወረወሩ፡፡ ቦምቡ እንደተጣለ ግራዚያኒ በጠረጴዛው ሥር ተደበቀ፡፡ ሌሎች ኢጣሊያኖች ግን ከመሬት ተኙ፡፡ ቦምቡን የጣለው ከኢጣሊያኖች ዘንድ በአስተርጓሚነት የሚሠራ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ነውʺ ብለዋል፡፡ የቦምብ ውርወራው አቆመ፡፡ መሬት ላይ ተኝተው የነበሩ የኢጣሊያ ወታደሮች ተነሱ፡፡ ወዲያው ካርቴሲ ወደ ኢትዮጵያውያን መኳንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ ተኮሰ፡፡ ተከታዮችም ምሳሌውን ተከተሉ፡፡ በጥቂት ጊዜ በዚያ ግቢ ውስጥ ሬሳዎች ተከመሩ፡፡ ባለ ጥቁር ሸሚዞች፣ የኢጣሊያ ሹፌዎች እና የቅኝ ግዛት ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን ይፈጁት ጀመር፡፡ በምርኩዝ የሚሄዱ ደካሞች፣ በመሪ የሚጓዙ ዓይነ ሥውሮች፣ ሊወልዱ የደረሱ ነብሰ ጡሮች ሳይቀሩ በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡ ጳውሎስ ሐንጋሪያዊውን ዶክተር ማስታወሻ ሲጽፉ ʺባለ ጥቁር ሸሚዞዎች በግቢው እየተሯሯጡ በሕይወት ያለ ኢትዮጵያዊ ይፈልጉ ነበር፡፡ ከሬሳዎች መካከል የሚተነፍስ እንዳለ እያሉ እየመረመሩ ይገድሉ ነበር፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ባለ ጥቁር ሸሚዞች፣ ካራቤኔሪዎችና የጦር ወታደሮች በከተማው ውስጥ ይሯሯጡ ጀመር፡፡ ሱቆች ሁሉ እንዲዘጉ አደረጉ፡፡ የውጭ ሀገር ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዙ፡፡ በተለይ ፎቶ ግራፍ ማንሻ እየተፈተሸ ይወሰድ ጀመር፡፡ መንገዱ ሁሉ ጭር አለ፡፡ የፖስታና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ፡፡ በቤተ መንግሥቱና በአካባቢው ያሉት መንገዶች በሙሉ በሬሳ ተሸፈኑ፡፡ ምን አይነት አጨካከን ነው? ደም እንደ ውኃ ሲፈስስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው፡፡
የወንዶች፣ የሴቶች፣ የልጆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያውም ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት፡፡ የሕዝቡ ቤት ከተፈተሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሳት ይቃጠላል፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዝንና ዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል፡፡ ሌሊቱንም ሲገድሉና ሲያቃጥሉ አደሩ፡፡ የማረሳው ነገር በዚያ ሌሊት የኢጣሊያ መኮንኖች በሚያምር አውቶሞቢላቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው ብዙ ሬሳ ከተከመረበትና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ በሰው ደም ላይ እየቆሙ ያን እልቂት እየተመለከቱ ይስቁ የነበረበት ሁኔታ ነው፡፡ ግራዚያኒ ሆስፒታል ኾኖ የአዲስ አበባን መቃጠል በመስኮት እያዬ ይስቅ ነበር፡፡ በዓለም ጦር ጊዜ ቁስለኛ ለማንሳት ከግንባር ቀደሙ ጦር ጋር በአንቡላንስ ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ በሌላም ጦርነት ተካፋይ ሆኛለሁ፡፡ እንደ አዲስ አበባው ያለ እልቂት ግን አላየሁምʺ ብለዋል፡፡
ባለ ጥቁር ሸሚዞች የሠረቁትን ወርቅና ብር በኢጣሊያ ባንክ እየገቡ አስቀመጡ፡፡ ዘረፋው በቤት ውስጥ ብቻ አልነበረም፡፡ ከሚገድሏቸው ሰዎች አንገት፣ ጆሮ እና እጣት የሚገኘውን ወርቅና ብርም ይወስዱ ነበር እንጂ፡፡ አዲስ አበባ በጥይት እና በእሳት ጋየች፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን አለቁ፡፡ ብዙዎችን መከራ ወደበዛበት እሥር ቤት ወስደው አሠሯቸው፡፡ በእስር ቤትም አያሌ መከራ አደረሱባቸው፡፡ በረሃብና በተቅማጥ በሽታ ብዙዎች አለቁ፡፡
በእሥር ቤት እጃቸውን ወደኋላ እየታሠሩ ለቃናት ይንጠለጠሉ ነበር፡፡ ብዙዎችን በመርፌ እየወጉ ይገድሏቸዋል፡፡ መከራው የገዘፈና አስቸጋሪ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ የኢትዮጵያውያንን አንገት አላስደፋቸውም፡፡ አርበኞች በጀግንነት ተዋግተው፣ ጨካኞችን እንዳልነበር አድርገው ከሀገራቸው አጠፏቸው፡፡ ለተጨነቁትም ደረሱላቸው፡፡ በጀግንነታቸው ነጻነታቸውን አስከበሩ፣ ሀገራቸውን አኮሩ፤ ሠንደቃቸውን ከፍ አድርገው በአንድነት ዘመሩ፡፡
ኢትዮጵያ እኒያ ንፁሐን ያለቁበትን፣ መከራ የተቀበሉበትን የካቲት አሥራ ሁለትን ታስባታለች፡፡
ሰማዕተነታቸውን ታስታውሳለች፡፡ ስለ ኢትዮጵያ መከራን የተቀበላችሁ፣ የግፍ ጽዋን የተጎነጫችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋዋል፡፡ ትውልዱ ሁሉ በልቡ ብራና ላይ ጽፎ ይዘክራችኋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!