መንግሥት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት መሠረት የኾነውን የግሉን ዘርፍ በአግባቡ መደገፍ እንደሚገባው የአማራ ክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት  ጠየቀ።

154

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክርቤት “ኮርድ ኤይድ -ኢትዮጵያ” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የወጣቱን የሥራ እድል ፈጠራ አስመልክቶ በባሕር ዳር ከተማ  ወይይት አካሂዷል።

አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተገኝተዋል። በወይይቱም በክልሉ  የሥራ እድል ፈጠራ በኩል ምን እየተሠራ ነው? ምንስ ለመሥራት ታቅዷል? እያጋጠሙ ያሉና በቀጣይም ሊስተካከሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጹሑፎች ቀርበው ምክክር ተደርጓል።

የአማራ ክልል የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳን ሱሌይማን ኢብራሂም እንደተናገሩት እንደ ሀገርም የሥራ እድል በመፍጠርም ኾነ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበረከት በኩል የግሉ ዘርፍ  ሚናው የጎላ ነው።

መንግሥት የግሉን ዘርፍ በአግባቡ መደገፍ እንደሚገባውም ጠይቀዋል።

መንግሥት የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ፣ ባለሃብቱን በመደገፍ፣ በቅንጅት በመሥራት፣ የሚያጋጥሙ ችግር በአጽኖት አይቶ መፍትሔን በማስቀመጥ በኩል በኀላፊነት መሥራት ይገበዋል ነው ያሉት።

የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ በተቻለው መጠን ከአጋር አካላትና አጋዥ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ እሔነው ዓለሙ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለክልሉ ኢንቨስትመንት መነቃቃትን እድል እየፈጠረ ሥለመኾኑ ተናግረዋል።

ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ እንደኾነ የተናገሩት ኀላፊው የኃይል አቅርቦትና ሌሎችንም ችግሮችን ሁሉ እየታገሰ ኢንቨስት የሚያደርገው ቁጥር እየጨመረ እንደኾነ ነው ያስረዱት።
“ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገር አቀፍ ንቅናቄው የአምራቹን ችግርና ጥያቄ መፍትሔ ጭምር ይዞ የሚመጣ ነው ያሉት ኀላፊው፣ በቅርቡም በአማራ ክልል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

በግል ዘርፉ የተሰማሩ የመድረኩ ተሳታፊዎችም መንግሥት የመሠረተ ልማት እና ሌሎችም  ከመንግሥት የሚጠበቁ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።

በተለይም የኃይል አቅርቦት ችግር የግሉን አምራች ዘርፍ እየፈተነው እንደኾነ ነው ያነሱት።
የገበያና ግብይት ሥርዓቱ ጤናማ አለመኾን “ከማምረት ይልቅ መሸጥ” ከባድ ኾኗል የሚል ሃሳብ ያነሱት አምራቾቹ መንግሥት የገበያ ሥርዓቱን በሕግና ሥርዓት በልኩ ሊመራው ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ” የሕግ መሠረት በሌለው ወይም በልኩ ባልታወቀ ሁኔታ የፈረሱ ኢንተርፕራይዞች አሉ  መንግሥት ወደ ሥራቸው ይመልስ፣ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞችን የመሥሪያ ቦታ አለመሥጠት ችግርም ዘርፉን እየጎዳው ነው “የሚል ቅሬታም ተነስቷል።

መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር  ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ   የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቡድን መሪው በለጠ ገበየሁ ናቸው።

የሥራ እድል ፈጠራው በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ባለመኾኑ በሥራ እድል ፈጠራ እና በግሉ ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የሚሞሉ አሠራሮችና ስትራቴጂዎች ላይ ማሻሻያዎች እየተደረጉ እንደኾንም ነው አቶ በለጠ የተናገሩት።
መንግሥት በዘርፉ የሚስተዋሉ አሥተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ መመሪያዎች እንዳተዘጋጀ ተናግረዋል።

የገጠርና የከተማ ኢንተርፕራይዞች የመሬት አጠቃቀም ላይ፣ የግሉ ዘርፍ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም በትኩረት እየተሠራ ነው ተብሏል።

በቅሬታ ለተነሱት፣ በተለያዩ ምክንያቶች የፈረሱ ኢንተርፕራይዞች በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት መፍትሔ የሚሰጣቸው ይኾናል የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።

ለፈረሱ ኢንተርፕራይዞችን መፍትሔ ፍለጋ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሚመለከተው አካል ጋር አስፈላጊውን ንግግር እንደሚያድርግም ፕሬዝዳንቱ  ሱሌይማን ኢብራሔም ተናግረዋል።

በተያያዘም በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች የተመረቱና የወጣቱን የሥራ እድል ፈጠራ ለማስፋት የሚያግዙ ተሞክሮዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በባሕር ዳር ከተማ ተከፍቷል።

በባዛር እና ኤግዚቢሽኑም በክልሉ በኢንዱስትሪዎችም ኾነ በግለሰቦች የተመረቱ የፋብሪካ ውጤቶች ለእይታ ቀርበዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleʺቅኝ ገዢዎች ሲበታትኗቸው፣ ኢትዮጵያ ሰበሰበቻቸው”
Next article“ያን ጊዜ ከተማዋን ዋይታ ሞላት፣ የደም ጎርፍ አጥለቀለቃትʺ