
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቁሮችን በነጻነት ወለደቻቸው፣ ከጨለማው ዘመን ወደ ብርሃን መራቻቸው፣ የተበተኑትን ሰበሰበቻቸው፣ ተስፋ ያጡትን ተስፋ ኾነቻቸው፣ ጥቁር ሁሉ ኃያል እንደኾነ አሳየቻቸው፡፡ ጥቁሮች ሁሉ እናታችን ይሏታል፣ ከዓለም ፊት በኩራት ይራመዱባታል፡፡ ስሟን እያነሱ ይመኩባታል፣ የነጻነት አርማችን፣ የአሸናፊነት ምልክታችን ናት ይሏታል፡፡
አፍሪካውያንን ቅኝ ገዢዎች ሲበታትኗቸው፣ ኢትዮጵያ ሰበሰበቻቸው፣ በአንድ ጥላ ሥር ሰብስባ ስለ ራሳቸው፣ በራሳቸው እንዲመክሩ እንዲዘክሩ አደረገቻቸው፡፡
ኢትዮጵያ ተስፋ ያጡት ተስፋ ያደርጉባታል፣ የተቸገሩት ይጠጉባታል፣ መድረሻ ያጡት ይጠለሉባታል፣ ድል አድራጊነትን ያዩባታል፣ የሀገር ፍቅርን፣ የሠንደቅ ክብርን ይመለከቱባታል፡፡ የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት፣ አንድነት፣ እምቢ ባይነትን ያዩ ሁሉ ከባርነት ለመውጣት ተነሱ፡፡ ጊዜ የሰጣቸው ቀኝ ገዢዎች ከወሰናቸው እያለፉ አፍሪካን ተቀራመቷት፣ ነጻነቷን እየገፈፉ በባርነት ሠንሰለት ውስጥ አሠሯት፣ የራሷን ባሕልና ሥርዓት እያጠፉ የእነርሱን ባሕልና ወግ ሰጧት፡፡ አፍሪካውያን የሚግባቡበትን ቋንቋቸውን፣ የሚያጌጡበትን ባሕላቸውን፣ ለዘመናት የሠሩባቸውን ታሪካቸውን አጠፉባቸው፡፡ በእርስታቸው ባይታዋር አደረጓቸው፣ በሕይወታቸው ሳይቀር አዘዙባቸው፡፡
የነጻነት ጀምበር በአፍሪካውያን ሰማይ ሥር ልትጠፋ ተቃርባለች፡፡ አፍሪካ ተስፈዋን እየፈጸመች ያለች ትመስላለች፡፡ በጥቅጥቅ ጨለማ ተጠቅልላ ጊዜው ለማይታወቅ ዘመን ልትታሰር የደረሰችም መስላለች፡፡ በምሥራቅ ፀሐይ ወጣ እንዳለ በአፍሪካ ሠማይ ሥር በምሥራቅ ንፍቅ በምትገኝ አንዲት ሀገር ብቻ ጀንበር ከፍ ብላ ታበራለች፡፡ ያቺንም ጀንበር አፍሪካውያን የመጨረሻ ተስፋቸው፣ ከባርነት መውጫ ብርሃናቸው፣ ከሰንሰለት መፈቻ ቁልፋቸው አድርገዋታል፡፡
በምሥራቅ ንፍቅ የምታበራው ጀንበር ከጠፋች ግን አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ በባርነት ጨለማ ውስጥ ትገባለች፣ ተስፋ የምታደርገው፣ በአሻገር የምታየው ምልክት ታጣለች፡፡ ያቺ ምሥራቃዊት ሀገር ጀንበሯን እንዳበራች ከኖረች፣ ነጻነቷን ከጠበቀች አፍሪካውያንንም ከመከራ ታወጣቸዋለች፣ አደራዋን ትወጣለች፣ ተስፋ ላደረጓት ትደርሳለች፡፡ ኃላፊነቷ እጥፍ ድርብ የሆነው ሀገር ነጻነቷን አስጠብቃ ለአፍሪካውያንም ተስፋ ለመሆን በጽናት ቆመች ታላቋ ኢትዮጵያ፡፡
የዓለም ማዕከላዊነት አውሮፓ ነው ያሉት አውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ወሰናቸውን እያሰፉ አፍሪካን መከራዋን አበዙባት፣ በጭንቅ ውስጥ አሰቃዩዋት፡፡ በምሥራቅ ንፍቅ የነጻነት ጀንበሯን እያበራች፣ በጽናት የኖረችውን ኢትዮጵያንም ለመያዝ ቋመጡባት፡፡
ዘመናዊ ሠራዊት የያዙት እና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁት አውሮፓውያን በአፍሪካ ሠማይ ሥር የሚያስቆማቸው አንዳችም ነገር እንደማይኖር ተማምነዋል፡፡ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛታቸው አካል ያደርጓት ዘንድ ቀረቧት፡፡ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሥር የማድረግ ዓላማው የነበራት ደግሞ ኢጣሊያ ነበረች፡፡ የሮም አደባባዮች በኩራት በሚራመዱ ወታደሮች፣ የነገሥታቶቻቸውን ስም እየጠሩ በሚያጋሱ ነዋሪዎች ተሞልተው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሥር የማድረጉ ዘመቻ ተጀመረ፡፡ ኢጣሊያ በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያን በጦር ድል መትታ ለማስገበር ያደረገቻቸው ሙከራዎች ሁሉንም በሽንፈት ስላፈረች ሌላ እድል ለመሞከር ነበር የተነሳችው፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ግዛቱን አስፍቶ የነበረው የሮማው አውግስቶስ ቄሳር ኢትዮጵያንም የግዛቱ አንድ አካል ያደርግ ዘንድ አይሎስ ጋሎስ በሚባል የጦር መሪ ሠራዊት አዝምቶ ነበር፡፡ በዘመኑ ኃያል የነበረው የአውግስቶስ ቄሳር ሠራዊት በኢትዮጵያዊያን ድል ተመትቶ ተመለሰ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም በሮም የነገሠው ኔሮ የአባቶቹን ሽንፈት ይክስ ዘንድ ካምቤይስ በሚባል የጦር መሪ አዝማችነት ሌላ ጦርነት ሞከሩ እንዳልነበር ኾነው ተመለሱ፡፡
ከዘመናት በኋላ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ዘመን ሲፋፋም ኢጣሊያ በተደጋጋሚ ሞክራ ያልተሳካላትን ኢትዮጵያን ለመያዝ ዳግም ጦርነት ከፈተች፡፡ በዘመኑ የነገሡት አባዳኛው ምኒልክ ጀግና ኢትዮጵያዊያንን እየመሩ ዘምተውና አዝምተው በዓድዋ ተራራ እንዳልነበር አደረጓት፡፡ ኢትዮጵያ የማትደፈር ሀገር መሆኗን አሳዩዋት፡፡ እንደ ቀደሙት ሁሉ አሳፍረው መለሷት፡፡ በጥቁሮች ምድር ይሄን ያክል ጀግና ሠራዊት አይኖርም ብለው አስበው የነበሩት አውሮፓውያን ደነገጡ፡፡ ኢትዮጵያን ተስፋ አድርገው የነበሩ አፍሪካውያንም ተስፋቸው የበለጠ ፈካ፡፡
ኢጣሊያ አርፋ አልተቀመጠችም፡፡ አርባ ዓመታትን ጠብቃ ለዳግም ወረራ በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ተነሳች፡፡ ዓመታትን በፈጀው ጦርነት ዳግም ተሸንፋ ተመለሰች፡፡ ኢትዮጵያም በነጻነት ምልክቷ ጸናች፡፡ አፍሪካውያንንም በተደጋጋሚ አኮራች፡፡ የጠላት ክንድ የማይደፍራት፣ የወራሪ ሠራዊት የማይኖርባት፣ ማንም የማያሸንፋት ሀገር መሆኗን በተደጋጋሚ አስመሰከረች፡፡ እርሷን ያዩ አፍሪካውያንም በክንዳቸው ነጻነታቸውን ማስመለስ ጀመሩ፡፡ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ያለማንም ከልካይነት ስታበራ የነበረችው ጀንበር አፍሪካን አዳረሰች፡፡ በጨለማው ሀገር ብርሃኗን ፈነጠቀች፡፡
ኢትዮጵያ የነጻነት ምልክት ኾና አፍሪካውያንን ከማኩራቷ አልፋ አፍሪካውያን አንድ የሚሆኑበትን ተቋም በመመሥረትም ቀዳሚዋ ሀገር ኾነች፡፡ አፍሪካውያን ስለራሳቸው የሚመክሩበትና አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ተመሠረተ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ ለዚህ ተቋም መመሠረት ድርሻቸው ላቅ ያለ ነበር፡፡ ቅኝ ገዢዎች በታትነዋቸው የነበሩ አፍሪካውያን በፈተናም ውስጥ ኾነው በአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና በነጻነት ምልክቷ ኢትዮጵያ እየተገናኙ እየመከሩና አንድነታቸውን እያጠናከሩ ዓመታትን አልፈው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት በአዲስ አበባ ለተሰበሰቡ የአፍሪካ መሪዎች ʺበአፍሪካዊነታችን ያለን ኩራት የሚገጥሙንን ችግሮች ሁሉ ለማስወገድ ትልቁ መሣሪያችን ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ አፍሪካ ከብዙ ጨለማ ከሆነ ዘመን ወጥታለች፡፡ ክፉው ጊዜ አልፏል፡፡ አፍሪካውያን ነጻ ኾነን እንደገና ተወልደናል፡፡ በእያንዳንዳችን ትግልና ድካም አፍሪካ እንደገና ነጻ ለመሆን ችላለች” ብለው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፊታውራሪነት በልጆቿ ጥረት ነጻ የወጣችው አፍሪካ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አቅሟን እያዳበረች ከትናንት ዛሬ የተሻለች እየሆነች ቀጥላለች፡፡
ኢትዮጵያ ያሰባሰበቻቸው አፍሪካውያን መሪዎች እንደ አባቶቻቸው ሁሉ ስለ አፍሪካ፣ በአፍሪካ ለመምከር ኢትዮጵያ ላይ ተሰባስበዋል፡፡ በአንድ ጥላ ሥር ተገናኝተዋል፡፡ የጥቁሮች ምልክትና ኩራት ኢትዮጵያም እንግዶቿን እያስተናገደች ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመሪዎች መዳረሻ፣ የዲፖሎማት መሰባሰቢያ መሆኗን እያሳየች ቀጥላለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ስለ ኢትዮጵያና ስለ መላው አፍሪካ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በተናጠል እና በጋራ እየመከረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለአንድነት ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየችና ለመሪዎቹ እየገለጸች ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!