
ደብረ ታቦር:ጥር 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ”አንድ ተማሪ ውጤታማ ሊኾን የሚችለው ለትምህርት ትኩረት በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲኖር ነው” ብሏል ተማሪ ታዳኤል።
ተማሪ ታዳኤል ሐይለመለኮት በ2014 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በአማራ ክልል ሁለተኛ ደረጃ የሆነውን 658 ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ተማሪ ታዳኤል ሐይለመለኮት የከፍተኛና መሰናዶ ትምህርቱን የተከታተለው በደብረታቦር ከተማ በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
ተማሪ ታዳኤል እንደሚለው በወላጆቹ እንቅስቃሴ ምክንያት በአንድ አካባቢና ትምህርት ቤት ረግቶ የመማር ዕድል ባያጋጥመውም ውጤታማ ከመኾን ግን አላደናቀፈውም፡፡
”ዓላማ ሲኖርህ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን መቋቋም ተገቢ ስለኾነ የቤተሰቤን በአንድ ቦታ ተረጋግተው አለመቀመጥ ወሳኝ ችግር ሳይኾንብኝ ትኩረቴን ለትምህርቴ በማድረጌ ተጽዕኖው አልታወቀኝም፡፡” ሲል ገልጿል፡፡
ተማሪ ታዳኤል ባገኘው ውጤት መደሰቱን፤ ብዙ ሰዎችም እየደወሉ በውጤቱ መደሰታቸውን እየነገሩትና ለወደፊትም ጠንክሮ እንዲሠራ እያበረታቱት መኾኑን ተናግሯል። በውጤቱም ቤተሰቡን፣ መምህራኖቹን እና ርዕሰ መምህራኖቹን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና ፈጣሪውን አመስግኗል፡፡
ለአንድ ተማሪ የትምህርት ውጤት የወላጅ እና የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ያለው ተማሪ ታዳኤል፤ ቤተሰቦቼ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሰጡ ዕድለኛ ነኝ ፤ የትምህርት ቁሳቁሶችን በመሟላት፣ ከመምህሮቼ ጋር በቅርበት በመወያየት፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖቼን ለይተው በመምከርና ሳጠፋ በማረም በጥሩ ሥነ ምግባር ቀርጸውኛል ብሏል ተማሪ ታዳኤል፡፡
ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ችግሮች በመረዳት፣ ራዕይ ኖሯቸውና ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው በመሥራት ለፍላጎቶቻቸው መሳካት በርትተው ሊሰሩ ይገባል ያለው ተማሪ ታዳኤል እሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ራዕይ ሰንቆ በመማር ለጥሩ ውጤት እንደበቃ ተናግሯል፡፡
ለአንድ ተማሪ ውጤታማነት የሚያጠናበት ቦታ፣ ጊዜ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ አቅርቦት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ለፊዚክስ፣ ለሒሳብና ለኮምፒዩተር ትምህርት ጥልቅ ፍቅር እንዳለው የገለጸው ተማሪ ታዳኤል ወደፊት ፊዚክስ ማጥናት እንደሚፈልግ ገልጿል።ፊዚክስ፣ ኮምፒዩተር ሣይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለኢትዮጵያም ለቀጣዩ ትውልድም አስፈላጊ ናቸው ብሎ ስለሚያስብ በዘርፉ ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ማራመድ እፈልጋለሁ ብሏል።
ዘጋቢ፡-ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!