
ባሕርዳር: ጥር 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ሩሲያ እንደትላንቱ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደምትሻ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ገለፁ።
የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂንን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም፤ በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን አዎንታዊ ትብብሮች አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።

በተለይም፣ የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በሩሲያ የላይኛው ምክር ቤት ማለትም የፌዴሬሸን ካውንስል መካከል ያለውን መልካም ትብብር ወደላቀ ደረጃ መሸጋገር እንዳለበት ተስማምተዋል።
ለዚህም ትብብር መጠንከር ይረዳ ዘንድ በቅርቡ በሞስኮ በሚካሄደው የሩሲያና አፍሪካ ምክር ቤቶች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የተላከውን የጥሪ ደብዳቤ ለአፈጉባኤው አስረክበዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ፤ በኢትዮጵያ ማንኛውንም መሬት ላይ ያለ ጥያቄ በሕግ አግባብ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ፅኑ እምነትና ፍላጐት እንዳላት ጠቅሰዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከቃላት ባለፈ ለሰላማዊ ግጭት አፈታት ተግባራዊነት እየሠራች የቆየችና አሁንም በትጋት እየሠራች መሆኑን ገልፀው፤ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ተከስቶ በሠላም የተቋጨውም ግጭት የዚህ ተግባራዊነት ማሳያ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በሌሎቹም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታዩ የሠላም መጓደሎች በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲፈታ የመንግስት እጆች መዘርጋታቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትም ትርጉም ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑን አንሰተው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁናቴም መረጋጋት እየታየበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ግጭት በሠላማዊ መንገድ በመፈታቱ የኢትዮጵያ መንግስትንና ሕዝብን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሩሲያ እንደትላንቱ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጡኑ አጠናክራ መቀጠል እንደምትሻ መናገራቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!