መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ማስፈን ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን አውቆ፣ በሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተሳተፉትን ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ የአማራ ምሁራን መማክርት በአፅንዖት አሳሰበ።

220

የአማራ ምሁራን መማክርት በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል፤ ሙሉ መልዕክቱ ቀጥሎ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ገናና ታሪኮችን የሠሩ፣ ጠንካራ ስርዓተ መንግሥት የመሠረቱ፤ ለዘመናት በመልካም እሴቶቻቸው ተከባብረውና ተቻችለው፤ ሀዘንና ደስታን፤ ክፉና ደጉን አብሮ መኖር የቻሉ ሕዝቦች ሀገር ናት። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ከሦስት አስርት ዓመታት ወዲህ ግን አኩሪ ባህሎቻችንን እና ታሪኮቻችንን የማይመጥኑ፣ በረጅም ዘመናት የገነባናቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶቻችንንና ትስስሮቻችንን የሚንዱ ፈተናዎች ተጋርጠውብን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንገኛለን። በቅርቡ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ፣ በድሬዳዋ፣ በዶዶላ፣ባሌ ሮቤ፣ ደብረ ዘይት፣ ናዝሬት፣ ዱከም፣ አምቦ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው ማንነትንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገው የብዙ ንጹሃን ዜጎቻችንን ህይወት የቀጠፈው፣ አካል ያጎደለው፤ ዜጎች በላባቸው ያፈሩትን ሀብት እና ጥሪት አውድሞ ያለመጠለያ ያስቀረው የኃይል ጥቃት የዚህ ፈተና አንዱ መገለጫ ነው።

በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተነሳ ህይወታቸውን ላጡ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ሀብት ንብረታቸው ወድሞ ያለመጠለያ ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል።

በተጨማሪም ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የንጹሃንን ህይወትና ንብረት ለማትረፍ ሲረባረቡ ለነበሩ የየአከባቢው ነዋሪዎችና የጸጥታ አካላት ለሙያቸውና ለሕዝብ በመታመን ለፈፀሙት አርዓያነት ያለው ተግባር ምስጋናችንን እያቀረብን ፤ ለሙያቸውና ለሕዝባቸው ታማኝ ያልሆኑ የጸጥታ አካላት ደግሞ የገቡትን ቃል ልብ እንዲሉ እናሳስባለን።

ሕግና ስርዓት ባልተከበረበት ሁኔታ የዜጎችን ደኅንነት እና ሰላምን ማረጋገጥም ሆነ ሀገርን ማስቀጠል አይቻልም። ስለሆነም መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ማስፈን ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን አውቆ ፣ በዚህ አሳዛኝ ክስተት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተሳተፉትን ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ በአፅንዖት እናሳስባለን።

ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ከቀጠለች ሁላችንም ሁለመናችንን ወደምናጣበት ደረጃ ስለምንደርስ እኛ ኢትዮጵያውያን ይህን በመረዳት ከዚህ አስከፊ ሁኔታ እንድንወጣ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ጥሪ እያቀረብን ለዚህ አሳዛኝ ክስተት ምክንያት የሆኑትም ከሀገር አፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በአጽንዖት እንጠይቃለን።

በተጨማሪም በዚህ አሳዛኝ ክስተት ሰለባ ለሆኑ ዜጎቻችን በአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ባለሃብቶች እንዲሁም በጎ አድራጊ ግለሰቦች ተገቢውን ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን።

በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ፤ የሀገራችን ሕዝቦች፤ ከጉሮሯቸው ነጥቀው ፣ ፆም ውለውና ፆም አድረው ያስተማሩን ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እንድናፈላልግ፣ የተሻለች ሀገር እውን እንድትሆን በርትተን እና በቅንነት እንድንሠራ ነው። በመሆኑም ይህንኑ ሀቅ ተገንዝበን፣ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ዘብ እንድንቆምና የመፍትሔ መንገድ እንድንቀይስ ጥሪ እያቀረብን የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ለዚህ ዓላማ ከማንኛውም ወገን፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ አብሮ ለመሥራት ዝግጁነት ያለው መሆኑን እንገልጻለን።

Previous articleትኩረት የተነፈገው የባሕል ስፖርት በሚፈለገው ልክ አላበበም።
Next articleበኩር ጥቅምት 17-2012 ዓ/ም ዕትም