” የሊቃውንቱ እጅ መንሻ፣ የደቀመዛሙርቱ መዳረሻ”

196
አስተሪዮን በመርጡለ ማርያም!
ባሕር ዳር፡ ጥር 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሪት መስዋዕት የቀረበብሽ፣ አበው ያከበሩሽ፣ ነገሥታቱ የሰገዱልሽ፣ የጦር አበጋዞች ጎራዴያቸውን እያስቀመጡ የተማፀኑብሽ፣ መኳንንት እና መሳፍንት ደጅ የጠኑብሽ፣ የተጨነቁት መረጋጋትን ያገኙበሽ፣ መድረሻ ያጡት የተጠለሉብሽ ፣ያለቀሱት እንባቸውን ያበሱብሽ፣ የተቅበዘበዙት ያረፉብሽ፣ የደከሙት ብርታትን ያገኙብሽ ርዕሰ ርዑሳን ኾይ ትውልድ ሁሉ ስምሽን ያነሳል፣ ትውልድ ሁሉ ክብርሽን ይናገራል፣ ስለ ኀያልነትሽ ይመሰክራል።
የበዛ ታሪክ የከበበሽ፣ ለጌታ የቀረበው መስዋዕት ያረገብሽ፣ በአፀድሽ ሥር ቅዱሳን የሚረማመዱብሽ፣ ስለ ምድር ሰላም እና በረከት የሚለምኑብሽ፣ በረከትና ረድኤት የሚቀበሉብሽ፣ ስምሽን እየጠሩ በደስታ የሚኖሩብሽ፣ በዙሪያ ገባው ኾነው የሚያመሰግኑሽ መርጡለ ማርያም ኾይ በማይጠፋ ቀለም ተፅፈሻል፣ በማያረጅና በማይቀደድ መዝገብ ላይ ተቀርፀሻል፣ በሰዎች ልብ ታትመሻል፣ ከፍ ከፍ ብለሽ ተቀምጠሻል።
በአሻገር ስምሽን የሰሙ ደቀመዛሙርት ወደ አፀድሽ የሚጓዙብሽ፣ አውራ ጎዳናዎችን አቆራርጠው በአፀድሽ ሥር የሚፀልሉብሽ፣ ፊደል ቆጥረው፣ ዳዊት ደግመው ሚስጢር የሚያመሰጥሩብሽ፣ ሊቃውንት ጥበብን የሚገልጡብሽ፣ እውቀትን ለትውልድ የሚነግሩብሽ፣ ሃይማኖት የሚያፀኑብሽ፣ ታሪክ የሚያስተምሩብሽ፣ እሴት በትውልድ መካከል ይሸጋገር ዘንድ የሚያደርጉብሽ፣ ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠው የከበረ ሃይማኖት፣ የረቀቀ ታሪክ የጻፉብሽ ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ኾይ ሁልጊዜም ትከበሪያለሽ፡፡
ለጌታ የሚገባው መስዋዕት ቀርቦባታል፣ የጌታ ስም እየተነሳ ተመስግኖባታል፣ አነሆ ዛሬም ይመሰገንባታል፣ ነገሥታቱ አውራጃዎችን እያቆራረጡ መጥተው እጅ ነስተውባታል፣ ለክብሯ የእጅ መንሻ አቅርበውላታል፣ በመቅደሷ እየሰገዱ ተማፅነውባታል፣ አምላክ ሕዝብ የመምራት ጥበቡን፣ መከራ የማለፍ ፅናቱን፣ ድል የማድረግ ጀግንነቱንና ብልሃቱን ይሰጣቸው ዘንድ ለምነውባታል፡፡
በንፁሕ ልብ ተማጽነው የልባቸውን መሻት አግኝተውባታል፣ ሕዝብ የሚመሩበትን ጥበብ ተቀብለውባታል፣ ድል የሚያደርጉበትን ድልና ብልሃት ተችረውበታል፣ ጸጋውና ረድዔቱን አግኝተውባታል፡፡
ዘለግ ያለውን ታሪክ ይዛለች፣ የበዙ ነገሥታትን አይታለች፣ ከበዙ ነገሥታት እጅ የእጅ መንሻ ተቀብላለች፣ በበዙ ሊቃውንት ተከባ ኖራለች፣ እየኖረችም ነው፣ ወደፊትም ትኖራለች መርጡለ ማርያም ገዳም፡፡
ሕገ ኦሪት ከመምጣቱ አስቀድሞ በሕገ ልቡና አምላክ ይታሰብባት ነበር፡፡ መርጡለማርያም ገዳም በዘመነ አበው በሕገ ልቡና የአምላክ ስም ተመስግኖባታል፣ ተጠርቶባታል፤ በዘመነ ኦሪትም የአርዓያም ማደሪያ እየተባለች በሕገ ኦሪትም የኦሪት መስዋዕት ይሰዋባት ነበር፣ ለጌታ የተገባው መስዋዕት ይቀርብባት ነበር፡፡
አበው በዚያች ምድር ስሟ ኀይል የኾነች ገዳም እንደምትገደም አስቀድመው ይናገሩ ነበር ይባላል፡፡ በጥንታዊት ገዳም በአብርሃ ወ አጽብሃ ዘመን የተገነባ፣ በጳጳሱ አቡነ ሰላማ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረ ቤተ መቅደስ አላት፡፡ ይህም ቤተ መቅደስ በቅድስና የተሠራ፣ እጅግ ያማረና የተዋበ የጥበብ አሻራ ነው፡፡ በዚያች ጥንታዊት ገዳም ያለ ምክንያትና ያለ መልእክት የተሠራ የለም፡፡ ሁሉም በምክንያት እና በምልክት ተሠራ እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ያለው የረቀቀ ምስጢር በቤተ መቅደሱ ተቀርጿል፣ ድንቅ ኾኖ ተሰርቷል፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ በራዕይ የተሠራ ነው ይላሉ አበው፡፡ ነገሥታቱ፣ ጳጳሱና ሊቀ ካህናቱ ሱባዔ ገቡ፡፡ ሱባዔ በገቡም ጊዜ የረቀቀ ራዕይ አዩ፡፡
ይህም ራዕይ አንድ አምደ ብርሃን ተተክሎ አሥራ ሁለት ክፍል ኾኖ ታያቸው፡፡ ይህን ባዩ ጊዜ ያጌጠ ቤተመቅደስ አሠሩ ይባላል፡፡ መርጡለማርያም ገዳም እጅግ የረቀቁ ቅርሶች ያሉባት፣ የረዘመ ታሪክ የሚገለጥባት፣ የታሪክ ማስረጃዎች የሚገኙባት ታላቅና ጥንታዊት ገዳም ናት፡፡ ከቤተክርስቲያን ላይ እጃቸውን ባነሱ አካላት ያማረው ቤተ መቅደስ የመፍረስ አደጋ ገጥሞትም ነበር፣ ዳሩ ታሪኩን እና ረቂቅነቱን ዛሬም ይመሰክራል፤ የቀደመውን ጥበብ ይናገራል፡፡
በወርቅ እና በእንቁ የተንቆጠቆጡ የነገሥታቱ ካባዎች፣ የራስ ዘውዶች፣ በትረ መንግሥቶች፣ እጅግ የከበሩ ታሪክ ነጋሪ ቅርሶች፣ እጹብ የሚያሰኙ ንዋየ ቅድሳት ይገኙበታል መርጡለማርያም፡፡ ለማርያም ማደሪያ የተመረጠች፣ ለሕዝብ መሰባሰቢያ የተመረጠች፣ አስቀድማ የታዬች፣ ሊቃውንት ያፈራች፣ እያፈራች ያለች ታላቅ ገዳም፡፡
የርዕሰ አድባራት ወገዳማት መርጡለ ማርያም ገዳም አስተዳደሪ ርዕሰ ርዑሳን ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ አበበ መርጡለ ማርያም የበዛ ታሪክ ያላት ናት ይሏታል፡፡ የዓባይን ወንዝ ተከትለው የመጡ ነገዶች ገና አስቀድሞ በዘመነ አበው በሕገ ልቡና አምላክን ያስቡባት የነበረች፣ የሰላም ሀገር፣ ሀገረ እግዚአብሔር እያሉ ይጠሯት እንደነበር ነግረውኛል፡፡
በዘመነ ኦሪትም አበው የኦሪት መስዋዕት ያቀርቡባት የነበረች፣ እጅግ የከበረችና የተቀደሰች ገዳም ናት ይሏታል፡፡ በዘመነ ኦሪት የአርዓያም አዳራሽ እየተባለች የተጠራች፣ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀች፣ የበረከት ማደሪያ የኾነች፣ የከበሩ ጥበብቾችን የያዘች ጥንታዊት ናት፡፡
በሐዲስ ኪዳን በአብርሃ ወ አጽብሃ ዘመነ መንግሥት የተሠራው ቤተ መቅደስ በወርቅና በብር የተለበጠና የረቀቀ እንደኾነም ነግረውኛል፡፡ መርጡለ ማርያም ታሪክና ሃይማኖትን፣ እሴትና ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ላይ የያዘች፣ ዘመናትን በክብርና በሞገስ የኖረች ታላቅ ገዳም ናት፡፡
በዓለ አስተርዮ ደርሷል፡፡ የመርጡለ ማርያም አጸድ ሥር በሊቃውንት ትመላለች፣ እጅግ የሚያምሩት፣ ያማረውን ልብሰ ተክህኖ የደረቡት፣ ትሕትናን ከአበው የወረሱት ሊቃውንት ይሰባሰቡባታል፣ ያማረውን ዝማሬ ያቀርቡባታል፣ ጳጳሳት ይጓዙባታል፣ ሕዝቡን እየባረኩ በቤተመቅደሷ ምስጋና እና ውዳሴ ለአምላክ ያቀርቡባታል፤ ደናግላን መነኮሳት ምስጋና ያቀርቡባታል፣ ዲያቆናት፣ አንባቢያን እና መዘምራን እንደ ክብራቸው እና ማዕረጋቸው ይሰባሰቡባታል።
ምድራዊ የማይመስለው ዝማሬ ይቀርብባታል፣ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን በአጸዱ ሥር ይሰባሰባሉ ፣በእጃቸው ያጨበጭባሉ፣ በአንደበታቸው እልል ይላሉ፣ ለጌታ የተገባውን ምስጋና ያቀርባሉ ፣በረከትና ረድዔትን ይቀበላሉ፡፡ ዝናሽ ከዳር ዳር የሚነገርልሽ፣ በታሪክ የከበርሽ፣ መንፈስ ቅዱስ የመላብሽ፣ የሊቃውንት ምንጭ የኾንሽ መርጡለ ማርያም ኾይ ሕዝብ ሁሉ ያይሽ ዘንድ ወደ አንች ይጓዛል፤ ስምሽን እየጠራ ወደ አለሽበት ይገሰግሳል፤ በአጸድሽ በደረሰም ጊዜ ሀሴትን ያደርጋል፣ ለአምላክም ምስጋና ያቀርባል፡፡
ዙሪያ ገባሽ በቃል ኪዳኑ ሠንደቅ ይዋባል፣ ዝማሬው ያስተጋባል፣ ምስጋናው በማዕልትና በሌሊት ይቀርባል፡፡ ሁሉም ያማረና የተዋበ ይኾናል፡፡ ከሕገ ልቦና እስከ ሐዲስ ኪዳን ድረስ አምላክ የታሰበብሽ፣ ስሙ ከፍ ከፍ ብሎ የተጠራብሽ፣ ለኢትዮጵያ ሰላምና በረከት የተጸለየብሽ መርጡለማርያም ኾይ ትወደጃለች፣ ትከበሪያለሽ፣ ታሪክሽና ገናንነትሽ በልብ ውስጥ እንዳበራ ትኖሪያለሽ፡፡
ሂዱ መርጡለ ማርያምን ተመልከቷት፣ ሂዱ የረቀቀችውን ገዳም እዩዋት፣ ደስታና ሀሴትን አገኙባት፣ እሴትና ታሪክን ተማሩባት፣ ቀደምትነቷን መስክሩባት፣ ኢትዮጵያን እዩባት፡፡
መልካም የአስተሪዮ በዓል!
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት በመንሳት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መቼም ሊሳካ አይችልም” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሽጥላ
Next articleአማራ ባንክ በሀገር አቀፍ ፈተና ከ600 በላይ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ወጭ እንደሚሸፍን አስታወቀ።