
ጥር 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በምሥራቅ አማራ ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አጎራባች አካባቢዎች የፀጥታ ችግር አጋጥሞ ቆይቷል። ይህን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሽጥላ በደረሰው የፀጥታ መደፍረስ ችግር የፀጥታ ኀይሎችና ንፁሃን ዜጎች መስዋእትነት ከፍለዋል ብለዋል።
አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት በየደረጃው ካለው የፀጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት በመሥራት አካባቢውን ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ድረስ ተቋርጦ የነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ኀይሎች በዋናነት ደግሞ ሸኔ የተሰኘው የሽብር ቡድን ቀጣናውን ለማተራመስ ወቅት እየጠበቀ የሚያደርሰውን ጥፋት እልባት መስጠት የሚያስችል ኦፕሬሽን በተቀናጀ መንገድ ከሕዝቡ ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።
“የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት በመንሳት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መቼም ሊሳካ አይችልም” ያሉት አቶ ግርማ በደረሰው የሰው ህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማው ገልጸዋል።
በጽንፈኝነት መሳሪያ ተጠቅመው የሕዝብ እልቂት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችን ህልማቸውን ለማክሰም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ብዝሐነት የሚገለፅበት ቀጣና የምሥራቅ አማራ ክፍልን እሳት በመለኮስ ችግር ለመፍጠር ሀገር አፍራሾች እየሠሩ መሆናቸውን እንረዳለን ነው ያሉት።
አካባቢውን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስም ከሁለቱ ዞኖች ከተወጣጡ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር ጋር በአጣዬ ከተማ ውይይት ስለማድረጋቸውም ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ በቀጣይ መሠራት ስላለባቸውና በየጊዜው ሕዝቡን ረፍት በመንሳት ርካሽ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱትን ጽንፈኛ ኀይሎች እልባት ለመስጠት በሚቻልበት ሁኔታ መክረናል ብለዋል።
“ከምንም በላይ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲመጣ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ሥራ እየሠራ ነው” ያሉት አቶ ግርማ የደረሰው ጥፋት ከፍተኛ ቢሆንም አጥፊዎችን በሕግ አግባብ ለመጠየቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የጥፋት ኀይሎች ተመጋጋቢ ሥራዎችን በመስራት አካባቢውን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ ሌት ከቀን እየሠሩ ስለመሆኑ እንገነዘባለን ያሉት አቶ ግርማ ይህንን በውሉ በመረዳት የክልሉ መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እየሠራ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የቀጣናው የጸጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ለማድረግም ክልሉ ማድረግ ያለበትን ሁሉ ይሠራል ብለዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ተረጋግቶ በቀጣናው ለተሰማራው የፀጥታ ኀይል አጋዥ ተግባር እንዲፈፅምም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:–ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!