ʺ ሠጋሪ ፈረሶች፣ ሰባሪ ጀግኖች”

205
ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖቹ ፈረሶቻቸውን ሸልመው፣ በአማረው ጌጥ አስጊጠው፣ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው፣በቁጣ ፈረሶቻቸውን ይኮለኩላሉ፣ጋሻቸውን አስተካክለው፣ጎራዴያቸውን ስለው በግርማ ይታያሉ፣ጠላት ወደ በዛበት፣ ምሽግ ወደ ሚሰበርበት ያለ ፍርሃት ይፋጠናሉ፣ ፈረሶቹ ሽምጥ ይሰግራሉ፣ ጌቶቻቸውን ከፈለጉበት ሥፍራ ለማድረስ በእልህ ይበራሉ፣ ወደ ጠላት ቀጣና ገስግሰው ይገባሉ፤ ፈረሶች ለማድረስ፣ ጀግኖቹ ለመድረስ ትንቅንቅ ይኾናል፡፡ ያን ጊዜ ምድር ትጨነቃለች፣ የጠላት ልብ በፍርሃት ትርዳለች፣ ጉልበቱ ብርክ ብርክ ትላለች፣ ፈረሱ እያሽካካ፣ ጀግናው እየፎከረ በገሰገሱ ጊዜ ጠላት ይደናበራል፣ የት በገባው የትስ በሄድኩ ይላል፡፡
ፈረሱ ገስግሶ ሲደርስ፣ጀግናው ጦሩን ከሰገባው ያወጣል፣ ጠላቱን እየነጠለ ይጥላል፣ ጋሻውን አስቀድሞ በጠላት መካከል ይረማመዳል፣ በቀኝ በግራው፣ በፊት በኋላው የተሰለፈውን ጣላቱን በጦሩ እየወጋ፣ በጎራዴው ስለት እየመታ፣ በፈረሱ እየረገጠ ያልፋል፣ ደማቅ ታሪክም ይጽፋል፡፡
ሠጋሪ ፈረሶች ጀግኖችን ያደርሳሉ፣ ሰባሪ ጀግኖች በሀገርና በሠንደቅ ላይ የተነሳውን ይሰብራሉ፣ እንዳልነበር አድርገው ይመልሳሉ፣ በጠላት ሠፈር ድል ነስተው ሠንደቃቸውን በኩራት ይሰቅላሉ፣ በፈረሶቻቸው ላይ ተቀምጠው በኩራት ይመላለሳሉ፡፡ የሀገራቸውን ስም በተደጋጋሚ እየጠሩ በአሸናፊነት ግርማ ይታያሉ፣ ጠላቶቻቸውን ከእግራቸው ጫማ ሥር ጥለው ቁልቁል ይመለከታሉ፣ አሸናፊነታቸውን ያስመሰክራሉ፡፡ ሀገር ለመውረር፣ ክብርን ለመድፈር የመጣውን አንገቱን አስደፍተው ይመልሳሉ፣ በጎራዴያቸው ሸልተው፣ በጦራቸው ወግተው እንዳልነበር ያደርጋሉ፡፡
የበረቱ ፈረሶች ከጠላት ሠፈር ቀድመው እየደረሱ ጌቶቻቸውን ድል አቀዳጅተዋል፣ በጦር ሜዳ ሽምጥ ጋልበዋል፣ ጋልበው ጌታቸው ድል ይነሳ ዘንድ ታላቁን ስጦታ ሰጥተዋል፡፡ ሰጋሪ ፈረሶች እሾህና አሜካላ በበዛበት፣ ጠላት በቀኝና በግራ በተደረደረበት፣ ጦርና ሾተል ባለበት፣ የጠላት መንጋ በሚግተለተልበት፣ ሞትና መቁሰል በበረከተበት በታማኝነት እና በፍጥነት ጀግኖችን ይዘው ይገሰግሳሉ፣ ሰባሪ ጀግኖችን ይዘው፣ ጭራቸውን እየነሰነሱ በሞት መካከል ድል ያቀዳጃሉ፡፡
ሠጋሪ ፈረሶች እና ሠባሪ ጀግኖች ሀገር ከፍ ከፍ አድርገዋል፣ ሠንደቅን በኩራት አውለብልበዋል፣ ነጻ በኾነች ሀገር በደም ጠብታ ነጻ ኾነው ኖረዋል፣ ነጻ የኾነች ሀገር፣ ነጻ የሆነ ትውልድ አፍርተዋል፡፡ ብዙዎች ባፈሩበት ዘመን እነርሱ ኮርተዋል፣ ብዙዎች በወደቁበት ዘመን እነርሱ በጀግንነት ተረማምደዋል፣ ብዙዎች በተሸነፉበት ዘመን እነርሱ በድል አድራጊነት ገስግሰዋል፡፡ ሰባሪ ጀግኖች፣ በሰጋሪ ፈረሶቻቸው ላይ ተቀምጠው የነጻነት ብርሃንን አውጥተዋል፣ ለተጨነቁት ደርሰዋል፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩትን በጀግንነት መርተው ወደ ብርሃን አድርሰዋል፡፡
በገናናው የኢትዮጵያ ታሪክ ሠጋሪ ፈረሶች እና ሰባሪ ጅገኖች ተነጥለው አይታዩም፤ ሰባሪ ጀግኖች ጋር ሰጋሪ ፈረሶች አሉ፡፡ ፈረሶች ያደርሳሉ፣ ጀግኖቹ ጠላትን ሰብረው ድል ያደርጋሉ፣ ለኢትዮጵያ ክብር ተዋድቀው፣ ደማቅ ታሪክ ይጽፋሉ፡፡
ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ በተደጋጋሚ የውጭ ጦር መጥቷል፡፡ ነገር ግን አንዱም አልተሳካለትም፡፡ ሁሉም እየተመታና እየወደቀ ተመለሰ እንጂ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው ʺኢትዮጵያውያን ባላቸው ኃይል የማይበገሩ ኾነው የሚመጣውን የውጭ ጦር ሁሉ መልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የማይለቁና የሌላ ሀገር የማይፈልጉ በመኾናቸው እንጂ እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች መስካሪነት ከኾነ አውሮፓን ኾነ ኢሲያን እያለፉ የሚይዙበት ብዙ ሁኔታ ነበር፡፡ ” በማለት አስፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የረቀቁ ፈረሰኞች፣ ጠላትን ድል የሚያደርጉ ጀግኖች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፈው ሳይሰጧት፣ በአሸናፊነት ግርማ እንዳስከበሯትና እንዳኮሯት ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ዛሬም እየጠበቋት ነው፣ ነገም ይጠብቋታል፡፡ ለምን ከተባለ ሀገር የመጠበቅ ቃል ኪዳን ተሰጥተዋልና፡፡
ጳውሎስ የባሕር ላይ ተጓዡ ማርኮ ፓውሎ ስለ ኢትዮጵያውያን የመሰከረውን ሲጽፉʺ ልታውቁት የሚገባ ነገር አለ በሀበሻ ምድር ምርጥ የኾኑ ወታደሮች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ወታደሮች ፈረሰኞች ናቸው፡፡ ፈረስም በብዛት አላቸው፡፡ በዚሕ ምክንያት ተዋጊዎች እና ኃይለኞች ናቸው፡፡ በሕንድ ሀገር ስላሉትና ከምናደንቃቸው እውቅ የሕንድ ወታደሮችም የሚበልጡ ናቸው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ፈረሰኞች እና ምሽግ ሰባሪዎች ናቸው፡፡ ጀግንነታቸው በየጦር ሜዳ ታይቷል፤ በታሪክ ተወድሷል፣ ተሞግሷል፡፡ ቀደም ባለው ዘመን የጀግንነት መለኪያው፣ የባላባትነት መገለጫው ፈረስ ግልቢያ ማወቅ፣ በተሸለመ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ነበር፡፡ የነገሥታቱ ልጆች በቤተ መንግሥት ዙሪያ ፈረስ ጉግስ ይጫወታሉ፣ ፈረስ ግልቢያ ይማራሉ፣ በፈረስ ላይ ኾነው የጦር ውርወራ ያውቃሉ፡፡ ፈረስ ተራራ መውጫ፣ ለሜዳ መሮጫ፣ ለባላባትነት መገለጫ ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባሕል ጥናት ዳይሬክተርና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ፤ በቀደመው ዘመን የሚጋልበው፣ ጭኖት የሚወጣው ፈረስ አለው ወይ ተብሎ የሚጠየቅ የሃብት መገለጫ ነው ይሉታል፡፡ ፈረስ የክብርና የሃብት መገለጫና ክብር ነውም ይላሉ፡፡
ፈረስ ከሰማዕታትና ከጀግኖች ጋር ይገናኛል፡፡ የአንድ ሰው ጀግንነት የሚመሰከረው በፈረስ ጋላቢነቱ፣ በፈረስ ጋልቦ በጦር ተዋጊነቱ ነው፡፡ ፈረስ የክብር መገለጫ ከመኾን ባሻገር ታዛዥ፣ ታማኝ እና ፈጣን ነውም ይላሉ መምህሩ፡፡ ፈረሶች ታምነው ወደጦር ሜዳ ይገሰግሳሉ፣ በጠላት መካከል ገብተው ጌታቸው ድል እንዲቀዳጅ ያመቻቻሉ፣ ጠላቱን ወግቶ ፈጥኖ እንዲወጣም በታማኝነት ይታዘዛሉ፡፡
ፈረስ እርሻ በማረስ የነዋሪዎችን ገቢ ያሳድጋል፣ እንግዳን በአጀብ መቀበያ፣ ዓመታዊ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ በዓላት መድመቂያ፣ ሰርግና ለቅሶ መከወኛም ነው ይሉታል መምህሩ፡፡ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ታንክ፣ መድፍ፣ እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ባልነበሩበት ዘመን ከጠላት ጋር ይደረጉ የነበሩ ውጊያዎች የሚከወኑት በጦር፣ በጋሻ እና በጎራዴ ነበር፡፡ የሚደረጉት የጨበጣ ውጊያዎችን በድል ለማጠናቀቅ ፈረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። አንድም ፈጥኖ ወደ ጠላት ገብቶ ለመደምሰስ፤ ሁለትም ደግሞ በፍጥነት ከጠላት ለመትረፍ ትልቅ ሚና ነበረው።
በኢትዮጵያ የተካሄዱ የውስጥ እና የውጭ ጦርነቶች በተነሱ ቁጥር ፈረሶች እና ፈረሰኞች ይነሳሉ፡፡ ነገሥታቱ በፈረሶች ተቀምጠው በክብር ይጓዙባቸዋል፣ ስንቅና ትጥቅ ይጫንባቸል፣ ተዋጊ ጀግኖች በክብር ይመላለሱባቸዋል፣ ወደ ጦር ሜዳ ተጉዘው ድል ያደርጉባቸዋል፡፡ ሰጋሪ ፈረሶች መጓጓዣዎች ብቻ ሳይኾኑ ታሪክ ሰሪዎችም ናቸው፡፡
ፈረስ ያልተዘመረለት ያልተነገረለት ባለ ታሪክ ነው ይሉታል መምህሩ፡፡ አበው በፈረሱ ይዝናኑበታል፣ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ሀገር ያጸኑበታል፣ በክብር ተቀምጠው ይታዩበታል፣ ከፍ ከፍም ይሉበታል፣ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ያዩበታል፤ ጦር ሜዳ ተጉዘውም ድል ይቀዳጁበታል፡፡
ፈረሶች ከፈረሰኞቹ ጀግንነት እና ባሕሪ ጋር የተስማማ ስም ይወጣላቸው እንደነበርም መምህሩ ነግረውኛል፡፡ 👉የቴዎድሮስ ፈረስ አባ ታጠቅ፣
👉የአጼ ዮሐንስ – አባ በዝብዝ፣
👉የአጼ ምኒልክ – አባ ዳኛው፣
👉የሳሕለ ስላሴ – አባ ዲና፣
✍️የንጉሥ ሚካኤል – አባ ሻንቆ፣
👉የልጅ ኢያሱ – አባ ጤና፣
👉የንጉሥ ሚካኤል – አባ ጠና እየተባሉ የነገሥታቱ ፈረሶች ስም ይሰጣቸው ነበር፡፡ የነገሥታቱ ብቻ ሳይኾን የጦር አበጋዞች ሁሉ የፈረሶቻቸው ስም ነበራቸው፡፡
በባዝራው እየሰገሩ፣ በድንጉላው እየገሰገሱ አያሌ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ እነኾ ወርኃ ጥር ላይ ነን፤ ሰባሪ ጀግኖች የሚታወሱበት፣ ሰጋሪ ፈረሶች የሚሰግሩበት፣ የትናንቱን ዛሬ ላይ የሚያሳዩበት፣ ታሪክ የሚዘክሩበት፣ የአበውን ጀግንነት የሚመሰክሩበት፡፡ ሰጋሪ ፈረሶችን እየተመለከቱ ታሪክ ይማሩ፣ ጀግንነትን ይመስክሩ፣ በሰጋሪ ፈረሶች ደስታን ያግኙ፡፡ በዓላቱ በፈረሶች ይደምቃሉ፣ ሜዳዎች በፈረሰኞች ይጨነቃሉ፣ በፈረስ ጋላቢዎች ደስታን ይገበያሉ፣ ሰዎች ሁሉ በዙሪያ ገባው ተሰባስበው መልካሙን ነገር ያያሉ፡፡ ሰጋሪ ፈረሶችን እና ሰባሪ ጀግኖችን በአንድ ላይ ይመለከታሉ፡፡ ይህ ህያው ቅርስ ጥር 23 በአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል በእንጅባራ ፤ ጥር 25 በቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል በደብረ ታቦርና እስቴ – መካነ ኢየሱስ በድምቀት ይከወናል። መልካም በዓል!
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo Amajjii 15/2015
Next article“የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት በመንሳት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መቼም ሊሳካ አይችልም” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሽጥላ