ትኩረት የተነፈገው የባሕል ስፖርት በሚፈለገው ልክ አላበበም።

340

የአማራ ክልል “የባህል ስፖርት አባት” እየተባለ ይጠራል። በተደጋጋሚ በሚደረጉ ሀገር አቀፍ የባሕል ስፖርት ውድድሮች በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅም ይስተዋላል። ለአብነት ያህልም በ2011ዓ.ም ኦሮሚያ ክልል አምቦ፣ በትግራይ ክልል-መቀሌ እና በሶማሌ ክልል- ጅግጅጋ በተደረጉ ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርት ውድሮች በሦስቱም የቀዳሚነቱን ደረጃ ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን ከተከታዮቹ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ያለው የነጥብ ልዩነትም ሰፊ ነበር። ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ የባሕል ስፖርት እንቅስቀሴ ቢኖረውም ባለው ሀብትና አቅም ልክ ግን ባሕሉን ማሳደግ አልቻለም።

የአማራ ክልል 4ኛው የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን አጠቃላይ ጉባዔ በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ተካሂዷል። በጉባዔው የክልሉ የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዓለም ሁነኛውን ጨምሮ የየዞኖችና የብሔረሰብ አስተዳድሮች የባሕል ስፖርት መምሪያ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የክልሉ የባሕል ስፖርት በሀገሪቱ የተሻለ አፈፃፀም ቢኖረውም በሚፈለገው ልክ እንዳላደገ በጉባዔው ተመክሮበታል። ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠት ደግሞ ዋናው ምክንያት ነው ተብሏል ። ለዘመናዊ ስፖርት ትኩረት መስጠትና “ባህሉን እናውቀዋለን” የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ባህሉ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ አድርጎታል ነው የተባለው።

በጉባኤው የተሳተፉት ለአብመድ እንደተናገሩትም ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው አካል ለሕህል ስፖርቱ ትኩረት አለመስጠት፣ የበጀት እጥረትና የማዘውተሪያ ቦታ አለመኖር ዘርፉን አዳክሞታል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግርም ለስፖርቱ መቀዛቀዝ ድርሻ አለው ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ ለባሕል ስፖርቱ የገንዘብ ድጋፍ አለማድረጉም ከተጽዕኖዎቹ መካከል ሆኗል። በመሆኑም የኅብረተሰቡ መገለጫ፣ መዝናኛ እና የእርስ በርስ መገናኛ ሆኖ ለዘመናት የዘለቀው የባሕል ስፖርት አሁን ላይ በዘመን ጣልቃ ገብነት እየደበዘዘ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል።

ባሕሉ በሚከወንባቸው ውድድሮች ተገቢውን አልባሳት አለመጠቀምም በጉባዔው የተነሳ የባሕል ጠንቅ ነው። በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጠው ሽፋን አነስተኛ መሆንም ባሕልን ለማስተዋዎቅ እንዳላስቻለ ነው የተጠቀሰው።

የአማራ ክልል ባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዓለም ሁነኛው የዳኞች፣ የሰልጣኞችና የባለሙያዎች ቁጥር መጨመሩ ስፖርቱን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል። በባሕል ስፖርቱ 11 የሚደርሱ የስፖርት ዓይነቶች እንዳሉ የገለፁት አቶ ዓለም ከዘመናዊው እኩል እይታ እንዲሰጠው መስራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

በጀት ተመድቦለት የገፅታ መገንቢያ ሆኖ እንዲቀጥልም እንሰራለን ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። በቀጣይም የታቀዱ ስልጠናዎችንና ውድድሮችን በማካሄድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለን የመሪነት ደረጃ አስጠብቀን፣ ባሕሉንም ጠብቀን ለመሄድ እንሰራለን ብለዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

Previous articleበአማራ ክልል 960 የተማሩ ወጣቶች ወደ መሥኖ ልማት ሊገቡ ነው፡፡
Next articleመንግሥት ሕግና ሥርዓትን ማስፈን ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን አውቆ፣ በሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተሳተፉትን ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ የአማራ ምሁራን መማክርት በአፅንዖት አሳሰበ።