የባሕርዳር ወጣቶች በዓል የሚከበርባቸውን አካባቢዎች እያጸዱ ነው፡፡

58
ባሕር ዳር: ጥር 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ይታደሙበታል፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳዳር በጎፈቃደኛ ወጣቶች እንደተናገሩት የታቦታት ማለፊያ መንገዶችን እና የታቦተ ሕጉ ማረፊያ አካባቢዎችን እና መንገዶችን እያጸዳን ነው ብለዋል። በዓሉን ለማክበር የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በተመለከቱት ነገር ተደስተው እንዲመለሱ ለማድርግ የማጽዳት ሥራ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሠጪ ወጣቶች ሰብሳቢ አስቻለው ሲሳይ በባሕር ዳር ከተማ የመጀመሪያው የጽዳት ፕሮግራም መካሄዱን ተናግሯል፡፡ ወጣት አስቻለው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በኹሉም ክፍለ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች በጉዳዩ ላይ መወያታቸውን ተናግሯል፡፡
ሁለተኛው ዙር ጽዳት በዋዜማው እየተካሄደ መኾኑን ነው የነገረን። በዓሉ ሀገራዊ በዓል በመኾኑ እናቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና የእስልምና እምነት ተከታዮች በጽዳት ሥራው ላይ ተሳትፈዋል ብሏል ወጣት አስቻለው፡፡
ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባባር የጸጥታ ሥራውንም እንደሚሠሩ ተናግሯል፡፡ ኹሉም ታቦተ ሕጉን አጅቦ የሚመጣ ወጣት፤ ለአካባቢው ደኅንነት የሚጨነቅ እና የባሕር ዳርን ከተማ ሥም በከንቱ እንዳይጠራ የሚያደርግ መኾን አለበት ብሏል፡፡
“በዓሉ የአደባባይ በዓል በመኾኑ በርካታ ሰዎች በቦታው ይታደማሉ፤ ይኽን ተባብረን እና ተከባብረን በጋራ ኀላፊነታችንን እንወጣለን”ብሏል፡፡
እናቶችን እና አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባሻገር በዓሉ በሰላም እንዲከናወን በትኩረት ይሠራል፡፡ በሥራውም በረከት እናገኝበታለን ብለን እናምናለን ብሎናል፡፡
ማኅበረሰቡ ለበዓል ብቻ ሳይኾን በማንኛውም ሠዓት አካባቢውን ቢያጸዳ፣ ለአገልግሎቱ ተብለው በተጸዱ አካባቢዎች ቆሻሻ ከመጣል ቢቆጠብ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዋዜማ ሁሉም የአስፓልት መንገዶች ይታጠባሉ፡፡ በየዓመቱ ጥርን በባሕር ዳር የተሰኘው ፕሮግራም ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የተሻለ አድርጎታል ያለው ወጣት አስቻለው እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውንም ነግሮናል፡፡ ወጣት አስቻለው እንዳለው የጽዳት ሥራውን በበጎ ፈቃድ እንደሚሠሩት እና ኹሉም ይኽን ተግባር እንዲደግፍ ጥሪ አስተላልፏል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጥምቀትና መተጫጨት”
Next articleየደሴት ላይ ጥምቀት!