
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሞጃና ወደራ ወረዳ የስንዴ ሰብል ኩታ ገጠምን ጎበኙ፡፡
በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ባለፈው ዓመት የተጀመረው ስንዴን በኩታ ገጠም የማምረት አሠራር ውጤታማ እንደሆነላቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው 4 ሺህ 881 ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል፡፡ የሰብሉ ቁመና የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝላቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ አንፃር ከአንድ ሄክታር እስከ 42 ኩንታል ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በሞጃና ወደራ ወረዳ በዘር ከተሸፈነው 19 ሺህ ሄክታር መሬት 600 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን 88 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በተለያዩ ሰብሎች ተሸፈኗል፡፡ በዞኑ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል፤ ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነውን በኩታ ገጠም ከተዘሩ የስንዴ፣ የሽንብራ፣ የገብስ፣ የጤፍ፣ የማሽላ እና የማሾ ሰብሎች የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
በሞጃና ወደራ ወረዳ የኩታ ገጠም የስንዴ ማሳዎችን የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየጎበኙ ነው፤ በአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ደግሞ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጤፍ ኩታ ገጠም ማሳዎች ላይ ጉብኝት እያካሄደ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ይርጉ ፋንታ- ከሞጃና ወደራ ወረዳ