
ባሕር ዳር: ጥር 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ በበርካታ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይታጀባል። ከእነዚህ መካከል የሴቶች የጸጉር አሰራር አንዱ ነው፡፡
የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ሴቶች እንደየፍላጎታቸው ዘመናዊ ወይም ባሕላዊ የጸጉር አሰራር ን በመምረጥ ይዋባሉ፡፡
በዘመናዊ መንገድ መዋብ የሚፈልጉ በፓይስትራ ወይም በካውያ፤ ሳብሳብ፣ፍሪዝ፣ከርል እና በመሳሰሉት ይዋባሉ፡፡ በባሕላዊ መንገድ መዋብ የሚፈልጉ ደግሞ የተለያዩ ሹሩባዎችን ይሰራሉ፡፡ ሹሩባ ፤ ስንቅር፣ አልባሶ፣አሣ ቅርጽ፣ሰርዴታ ፣አጼ ቴዎድሮስ፣ገብስ ሥራ ፣አከንባሎ እና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
አሚኮም በባሕር ዳር ከተማ በመዟዟር ለበዓሉ ድምቀት ሴቶች እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት ቃኝቷል። በየውበት መጠበቂያ ሳሎኖች በርካታ ሴቶች ወረፋቸውን እየጠበቁ ነበር ያገኘናቸው።
በውበት ሳሎን ሥራ የምትተዳደረው ዋጋዬ መስፍን በተለይ በጥምቀት በዓል በየዓመቱ ከሌሎች የሥራ አጋሮቿ ጋር በመሆን፤ በቀንና በሌሊት ከ200 በላይ ሴቶችን ጸጉር እንደምታሳምር ነው የተናገረችው።
ሴቶች ባሕላቸውን ጠብቀው በቡድን ፀጉራቸውን እየተሠሩ መኾኑን ተናግራለች። ባለሙያዋ ሴቶች ፀጉራቸውን ተሠርተው፤ የባሕል ልብስ ለብሰው፤ በዓሉን ማክበራቸው የሚያስደስት ነው ብላለች።
“ሴቶች የፀጉራቸውን ውበት በመጠበቅ ለጥምቀት በዓል አምረው እንዲያጌጡ ቀን ከሌሊት እየሠራን ነው” ያለችው ደግሞ ሌላዋ በውበት መጠበቂያ ሳሎን የሥራ ዘርፍ የምትዳደረው መሰረት መንግሥት ነች። ባለሙያዋ እንዳለችው የጥምቀት በዓልን ታሳቢ በማድረግ የሴቶች ፀጉርን ባሕላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እየሠራች ትገኛለች።
ለበዓሉ ድምቀት ፀጉሯን ስትሠራ ያገኘናት ወጣት ራሔል ወርቁ በዓሉን በደመቀ መልኩ ለማክበር ማቀዷን ተናግራለች። ጥምቀትን የሚመጥን ባሕላዊ ልብስ በመልበስ በዓሉን ለማክበር ዝግጅቷን እያጠናቀቀች መኾኑን ነግራናለች። የጥምቀትን በዓል በየዓመቱ በድምቀት ስታከብር እንደነበረም ወጣቷ አስታውሳለች።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!