ጎንደር – ጥንትም የሲራራ ንግድ ኹነኛ መስመር፤ አሁንም የዘመናዊ ንግድ ማዕከል።

193

ጎንደር :ጥር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር ከአጼ ፋሲል ዘመን ጀምሮ ከቀይ ባሕር እስከ አውሮፓ የሚዘልቀው የሲራራ ንግድ ዋነኛ መስመር ነበረች። አኹንም ቢኾን በዘመናዊ ንግዱ የተሰማሩ ኹሉ የሚያተርፉባት ከተማ ኾና ቀጥላለች።

በጎንደር በተለይም በቅባት እህሎች እና በቅመማ ቅመም ሙሉ ናት። የሁመራ ሰሊጥ እና የቆላድባ ጥቁር አዝሙድ ለጎንደር ገበያ ሲሳዮች ከኾኑት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በጎንደር ገበያው ጥጋብ ነው። የእንግዳ ጌታ ስለኾነች ገዥ አጥታ አታውቅም።

የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ በምድርም በሰማይም በርካታ እንግዶች ወደ ጎንደር እየተመሙ ነው። ጥምቀትን በጎንደር የንግድ ትርዒትና ባዛር አንዱ የጎንደር ድምቀት ኾኗታል። ባዛሩ ጥር 6/2015 የጀመረ ሲኾን እስከ ጥር 15/2015 ዓ.ም ይቆያል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሀይ ጎንደር ከተማ ከብዙ አመታት በፊት የሲራራ ንግድን በመጀመር ለብዙ ሀገሮች የንግድ ሥርዓት ተምሳሌት ናት ብለዋል።

ጥምቀትን በጎንደር ከተማ ለማክበር በርካታ እንግዶች ወደ ከተማው እየገቡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ እየተካሄደ ያለው የንግድ ትርዒት እና ባዛር የበዓሉ አንዱ ድምቀት ስለመኾኑም ተናግረዋል። ባዛሩ አምራች እና ሸማቾችን በአንድ ማዕከል አገናኝቶ በተመጣጠነ ዋጋ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለማቅረብ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከተማ አሥተዳደሩ ለነጋዴዎች የመሸጫ ምቹ ቦታ እና አስፈላጊውን ኹሉ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ምርቶቻቸውን ይዘው ወደ ጎንደር ከተማ የመጡ ነጋዴዎች የጎንደር ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹ መኾኗን አይተው በተለያዩ ተጨማሪ ልማቶች ላይ እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሱሌማን ኢብራሂም ይኽ የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ እንግዶች ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት የራሳቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያለመ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል። ከኢኮኖሚው መነቃቃት በተጨማሪ አካባቢው ሰላሙን ጠብቆ የልማት ኮሪደር እንዲኾን እየተሠራ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አቶ ሱሌማን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ለዘርፍ ምክር ቤት ማኅበራት ቦታ በመስጠት ለንግዱ ዘርፍ መነቃቃት ላሳየው እንቅስቃሴም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ