
ባሕር ዳር :ጥር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኀያላን ነገሥታት ዙፋናቸውን አስቀምጠውበታል፣ በሕዝብ ተከበው፣ በጠንካራ ጦረኞች ታጅበው፣ መኳንንቱን በግራና በቀኝ አሰልፈው ተቀምጠውበታል፣ የተስማማውን፣ እውነት የኾነውን ፍርድ ፈርደውበታል፣ ሀገር የሚያጸና፣ ሕዝብ የሚያኮራ ምክር መክረውበታል፣ ሊቃውንቱ ተሰባስበውበታል፣ ምስጢር እያመሴጠሩ እውነትን አውጥተውበታል፣ ጥበብን ገልጠውበታል፡፡
ጃን ተከል ዛፍ ብቻ አይደለም አዕዋፋት የሚኖሩበት፣ በማለዳና በምሽት የሚዘምሩበት፣ ጃንተከል ጥላ ብቻ አይደለም የደከማቸው የሚያርፉበት፣ ላባቸውን የሚጠርጉበት፣ ጃንተከል ዛፍ ብቻ አይደለም በተመቸ ጊዜ የሚቆርጡት፣ ከሥሩ ነቅለው የሚጥሉት፡፡
ጃንተከል ታሪክ ነው ነገሥታቱ ዙፋናቸውን አስቀምጠው በክብር የታዩበት፣ ጃንተከል የታላቅነት መገለጫ ነው ታላላቆቹ ታላቅ ነገርን ያስተማሩበት፣ ጃንተከል የፍትሕ ማረፊያ ነው መልካሙ ፍርድ የተፈረደበት፣ ጃንተከል የሊቃውንት መዳረሻ ነው፣ ጥበብ እንደ ዥረት የፈሰሰበት፣ ጃንተከል የጥበብ መገኛ ነው አበው በጥበብ ምስጢር ያሜሰጠሩበት፡፡ ጃን ተከል ግርማ ነው የጦር አበጋዞች በግርማና በኩራት የታዩበት፣ ጃንተከል የአንድነት ጥላ ነው በአንድነት የተሰባሰቡበት፣ ጃንተከል የፍቅርና የስልጣኔ መገለጫ ነው የሀገር ጥያቄዎች በውይይት የተፈቱበት፡፡
ነገሥታቱ በታላቁ ቤተ መንግሥት በክብር እና በአጀብ ይወጣሉ፣ በእልልታና በአጀብም ይከበባሉ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት በግርማ ይታያሉ፣ ሕዝቡም በእልልታና በሞገስ ያጅባቸዋል፣ ይከባቸዋል፣ ያከብራቸዋል፣ መልካሙን ምኞት ይመኝላቸዋል፣ ሺህ ዓመት ንገሡ ይላቸዋል፡፡ ጃንተከል ሕዝብና ንጉሥ፣ መኳንንትና መሳፍንት፣ ሊቃውንት፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ አዝማሪዎች፣ ነጋዴዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት፣ ፍትሕና ፍርድ የሚያዩበት ታላቅ ሥፍራ ነው፡፡
በታላቁ ቤተ መንግሥት ከአስራ ሁለት በሮች መካከል በፊት በር ሲወጡ ቀድመው የሚያዩት፣ በግርማ የሚመለከቱት ታላቁን ዋርካ ጃን ተከልን እና አደባባይ ኢየሱስን ነው፡፡ ጃንተከል ግርማን ተላብሶ፣ ትናንትና ዛሬን እያስተሳሰረ ዘመናትን የተሻገረ ታላቅ ዋርካ ነው፡፡
ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በሚለው መጽሐፋቸው በጎንደር ከተማ በጽሑፍ የሠፈረ ነገር ባላገኝም በአፈታሪክ የሚነገሩ አርባ አራት ምንጮች፣ አርባ አራት ዋርካዎች አሉ ይባላል በማለት ጽፈዋል፡፡ እሳቸው እንኳን ባደረጉት ጥረት ሃያ አራት ታላላቅ ዋርካዎችን ማግኘታቸውን ከትበዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ እውነት የኾኑት የቀደሙት አርባ አራት ታቦታት (አሁን ቁጥራቸው የበረከተው) በጎንደር ከተማ ይገኙበታል፡፡ ጎንደር በምስጢርና በጥበብ የተከበበች ከተማ ናት፡፡
ከአንደኛው ጎዳና ወደ ሌላኛው ጎዳና በተንቀሳቀሱ ቁጥር ግሩም ታሪክ፣ ግሩም ጥበብ፣ ግሩም ተፈጥሮ፣ ግሩም ቅርስ ይገኝባታል፡፡ ታምራት ወርቁ ከታላላቆቹ ዋርካዎች መካከል ስሙ ስለ ገነነው ጃን ተከል ዋርካ ሲጽፉ “ጃን” ትልቅ ሰው የተከለው ማለት ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ጃንተከል ታላቅ ያረፈበት፣ ታላቅ የኖረበት፣ ታላቅ የተመላለሰበት ነው፡፡ ጃንተከል ታላላቅ ማዕረጎች የተሰጡት ታላቅ ዋርካ እንደኾነም ይነገርለታል፡፡
ʺጃንተከል ዋርካው ሥር እትብቴ ተቀብሮ
ልቤ ጎንደር ይላል የትም የትም ዞሮ” እንዳለች ዘፋኟ ጃንተከል በትዝታው የሚያብከነክን፣ በውበቱና በግርማው የሚጠራ፣ ጎንደርን ያዬ ሁሉ ሲያስታውሰው የሚኖር፣ ጎንደርን ለማዬት ያሰበ ሁሉ ያዬው ዘንድ የሚመኝው ዋርካ ነው፡፡ ከዚያ ዋርካ ስር ያረፈ ሁሉ ፍቅርንና ትዝታን ይዞ ይነሳል፡፡
ጃንተከል አዋጅ የሚነገርበት፣ ገበያተኛ የሚገበያይበት፣ ሹም ሽር የሚፈጸምበት፣ ወንጀለኞች የሚቀጡበት፣ ሊቃውንት ጉባዔ የሚያደርጉበት፣ ለነገሥታት እጅ የሚነሱበት፣ ነገሥታቱ የጦር አበጋዞችን የሚመለምሉበት፣ ሹመት ሽልማት የሚሰጡበት፣ ባላባቶች የሚመክሩበት፣ የተጋጩ ሰዎች የሚታረቁበት፣ ፍቅረኛሞች የሚገናኙበት ሥፍራ ነው ይሉታል ታምራት ወርቁ፡፡
ከጎንደር አብያተ መንግሥታት አሥራ ሁለት በሮች መካከል በፊት በር የሚወጡት ንጉሡ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙት በጃንተከል ሥር ነው፡፡ የጎንደር ከተማ የግል አስጎብኚዎች ማኅበር ሊቀመንበር ፋንታሁን ያለው እንደነገሩን ፊት በር ለንጉሡ መተላለፊያ ይሆን ዘንድ ደርብና ምድር የነበረው፣ የንጉሡ ዋና ውጫና መግቢያ በር የነበረ ነው፡፡ በጎንደር አብያተ መንግሥታት ዙሪያ ያሉት በሮች የተለያዬ ስያሜ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ ስያሜያቸው ሁሉ እንደ ስልጣን ደረጃቸው የሚወጣባቸውና የሚገባባቸው በሮች ናቸው፡፡ ንጉሡ፣ የጦር አዛዦች እና ሌሎችም የሚወጡበትና የሚገቡበት እንደ ማዕረግና እንደ ክብራቸው ይለያያል፡፡
ጎንደር በግዙፍ ዋርካዎች ትታወቃለች፡፡ ከሁሉም ዋርካዎች መካከል ስሙ የናኘው ጃን ተከል ነው፡፡ ጃን ማለት አባት፣ ንጉሥ፣ ታላቅ መሪ እንደማለት ነው ይሉታል፡፡ ጃን አንድም ታላቅ ግርማ ያለው የተከለው ነው ሲባል፣ ሁለትም ንጉሡ ድንኳን የተከሉበት ነው ይባላል፡፡
ጃንተከል ዋርካ የነጋዴ ቅፍለቶች ማረፊያ ፣ማኅበራዊ ግጭት ሲፈጠር ለመወያያ፣ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በመተላለፊያ ድልድዩ ተጉዘው፣ በክብር ዙፋናቸው አርፈው የሊቃውንቱን ክርክር የሚያዩበትና የሚዳኙበት ነበርም፡፡ ያ ሥፍራ ሰፊ አደባባይ የነበረበት ታላቅ ዋርካ ነው ይላል የግል አስጎብኚዎች ማኅበር ሊቀመንበሩ ፋንታሁን፡፡
ጃንተከል ፍቅር የተገበያዪት፣ ከሥሩ ተቀምጠው የአበውን ታሪክ የሚያስታውሱበት፣ ታሪክ የሚማሩበት፣ ታሪክ የሚነግሩበት፣ ታላቅነትን የሚመሰክሩበት ነው፡፡
ይሂዱ ከጥላው አርፈው፤ የታላላቆቹን ታሪክ ይወቁበት፣ የኀያላኑን ዘመን ያስታውሱበት፣ አብሮ የሚኖር መልካሙን ትዝታ ይገብዩበት፣ ፍቅርና አንድነትን ይማሩበት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!