
ጎንደር፡ ጥር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶች ወደ ጎንደር ከተማ በመግባት ላይ ይገኛሉ። ይኽንን ተከትሎ በከተማው ውስጥ ለመዘዋወር የመጓጓዣ አገልግሎቱ እንዳይጨናነቅ ከማድረግ አኳያ የከተማ አሥተዳደሩ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ቅድመ ዝግጅት እና የተቀናጀ ስምሪት እያደረገ ይገኛል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለልኝ አየነው የጥምቀት በዓል ሲከበር የትራንስፖርት ዘርፉን የሚያሳልጥ ኮሚቴ ተቋቁሞ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ኮሚቴው የተሽከርካሪ ባለቤቶች፣ ማኅበራት እና ወጣቶችን ያካተተ ሲኾን ባለፉት ዓመታት ይገጥም የነበረውን የትራንስፓርት ችግር ለመቅረፍ ያለመ ነው ብለዋል።
ኮሚቴው ከጥምቀት በዓል ዋዜማ ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚኾኑ እና እንደአማራጭ የሚያገለግሉ መንገዶችን ለይቶ እንደሚሠራም ተገልጿል። በንግድ ሸቀጣሸቀጥ የተዘጋጉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ነጻ ኾነው ለእንግዶች መጓጓዣነት እንዲያገለግሉም ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በከተማው ውስጥ የሚገኙ ኹሉም አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች ያለምንም የታሪፍ ጭማሪ እንግዶችን ከቦታ ቦታ እንዲያንቀሳቅሱ ይደረጋልም ብለዋል። የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ማዕከላቸውን በከንቲባ ጽሕፈት ቤት አድርገው እንግዶችን ወደሚፈልጉት ቦታ ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ አለልኝ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!