ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ለተሾሙት 14 ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮችና 7 አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ሰጡ።

198

ባሕር ዳር :ጥር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሹመት ደብዳቤ የመስጠት መርሀ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል።
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያን ማገልገል ትልቅ እድል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ተሿሚ አምባሳደሮች እምነትንና ሰርቶ ማሳመንን መርህ አድርገው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ስክነት እና ጠንካራነትን በመላበስ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር ረገድ ከተሿሚ አምባሳደሮች በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቁም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁለት የፈተና ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ ወደ ተስፋ እየተመለሰች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ይህ ቀጣይነት እንዲኖረው አምባሳደሮች ጥረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፥ ሀገር ስትፈተን አብሮ የተጎዳው ዲፕሎማሲ አሁን ላይ እየተነቃቃ እና ግንኙነቶች እየተሻሻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ችግሮች አልፈው ሰላምን የማፅናት፣ የተጎዱ አካባቢዎችና ተቋማትን የመገንባት እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ሀገርን የመጠበቅ ስራ ችግሮች ሲፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው፤ ከተሿሚ አምባሳደሮች ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
ተደማጭና ተመራጭ፣ ብሄራዊ ጥቅሟ የተረጋገጠ ሀገር እንድትኖረን ተሿሚ አምባሳደሮች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ተሿሚ አምባሳደሮችም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት የኢትየጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ በመንግሥታት መካከል ግንኙነቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትጋት እንደሚሰሩ ቃለ መሃላ ፈፅመዋል። ዘገባው የኢቢሲ ነወ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል አከባበርን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረስብከት መግለጫ ሰጠ።
Next articleጥምቀትን በጎንደር ለሚያከብሩ እንግዶች የተሳለጠ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት ተዘጋጅቷል።