በአማራ ክልል 960 የተማሩ ወጣቶች ወደ መሥኖ ልማት ሊገቡ ነው፡፡

409

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የተማሩ ወጣቶችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የመስኖ ኮሚሽን በመስኖ ሥራ ለሚሰማሩ ወጣቶቹ ለ10 ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በባሕር ዳር እየሰጠ ነው፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ድኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶክተር) እንደገለጹት በዓመቱ በኢትዮጵያ 12 ሺህ የተማሩ ወጣቶችን በመስኖ ልማት አሰማርቶ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም 50 ሺህ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል ብለዋል። ወጣቶቹ ወደ ሥራ የሚገቡት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተገንብተው በተጠናቀቁ የመንግሥት የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሆነም አስረድተዋል።

በአማራ ክልልም የጣና በለስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ተጠቅመው ማልማት ይችላሉ ያላቸውን 960 የተማሩ ወጣቶች ወደ ሥራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አመላክቷል። በ80 ማኅበራት ለተደራጁ የተማሩ ወጣቶች 4 ሺህ ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር መዘጋጀቱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ለእያንዳንዳቸው ወጣቶችም 4 ሄክታር መሬት እንደሚሰጥና የጣና በለስ የመስኖ ፕሮጀክትን ተጠቅመው በዘመናዊ መልኩ ለገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለጸው፡፡

ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም ለወጣቶቹ በባሕር ዳር ከተማ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው። ሰልጣኞቹ በሀይድሮሊክስ፣ በአካውንቲንግ፣ በጅኦሎጅና በሌሎች የግብርና የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። ለተከታታይ 10 ቀናትም በሥራ ፈጠራ፣ በሜካናይዝድ የመስኖ ልማትና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ወደ ሥራ ሲገቡም እያንዳንዳቸው ከመቶ ላላነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከቦታ ዝግጅት፣ ከብድር አቅርቦትና ከገበያ ትስስር ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳይገጥሟቸው ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከልማት ባንክና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን የመስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ወጣቶቹም እየተፈጠረላቸው ያለውን መልካም ዕድል ተጠቅመው በ”ሜካናይዝድ” የአስተራረስ ዘዴ ለገበያ ተፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር ሌሎችን ለመጥቀም ዝግጁ መሆናቸውን ለአብመድ ጠቁመዋል።

በትምህርት ዘመናቸው ያካበቱትን ዕውቀት ለሌሎች አርሶ አደሮች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በኦሮሚያ፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ የተማሩ ወጣቶች ተመሳሳይ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ የሚችል 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማለ። ሀገሪቱ ካላት የመልማት አቅም አንፃር ሲታይ አሁን እየለማ ያለው 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ

Previous articleበሞጃና ወደራ ወረዳ በዘር ከተሸፈነው 19 ሺህ ሄክታር መሬት 600 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Next articleትኩረት የተነፈገው የባሕል ስፖርት በሚፈለገው ልክ አላበበም።