ʺየድንቅ ምድር ድንቅ በር- አሚኮ”

177

ባሕር ዳር: ጥር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ተራራዎቹ በታሪክ ተሞልተዋል፣ በሃይማኖት ከብረዋል፣ በቅዱስ መንፈስ ጸንተዋል። ሸለቆዎቹ በቅርስ ተከበዋል፣ ሜዳው በባሕል ተውቧል፣ በታሪክ አምሯል፣ በእሴት ደምቋል፣ በጀግኖች አሸብርቋል፣ በሐይቆቹ ቅዱስ መንፈስ ሞልቷል፣ ዙሪያ ገባቸው በመልካም ማዕዛ ታውዷል፤ በሐይቆቹ ገዳማትና አድባራት ይገኛሉ፣ በገዳማቱና በአድባራቱ ቅዱሳን ይኖራሉ፣ ያለ ማቋረጥ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ይጸልያሉ፣ የፈጣሪን ስም እየጠሩ ምስጋና ያቀርባሉ፣ አምላክ ምድርን በበረከት ይዋጃት ዘንድ ይማጸናሉ፡፡

የረቀቁ አብያተ ክርስቲያናት፣ የተዋቡ አብያተ መንግሥታት፣ እጹብ የሚያሰኙ ገዳማት፣ ታይተው የማይጠገቡ መስጅዶች፣ ታሪክ የሚጠራቸው ድንቅ ሥፍራዎች፣ አምላክ አሳምሮ የሠራቸው ተራራዎች፣ ሸለቆዎች፣ ኮረብታዎች ይገኙበታል፡፡ አምላክ አሳምሮ በሠራቸው ተራራዎች ብርቅዬ እንስሳት ይመላለሱበታል፣ ምድሩን መርጠው ይኖሩበታል፡፡

ገነትን የሚያጠጣው ታላቁ ወንዝ ግዮን ይፈልቅበታል፣ ምስጢራዊ ሐይቅ ጣና በምስጢር ይኖርበታል፣ ሰማይ ጠቀሶቹ የሰሜን ተራራዎች ይገኙበታል፡፡ የአሠራር ጥበባቸውን ዓለም ያልደረሰባቸው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ የአፍሪካ መናገሻ የኾኑት የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ጥበብን፣ ሃይማኖትን፣ ታሪክን፣ እሴትን፣ ምስጢርን የታቀፉት የጣና ገዳማት፣ በመስለቀኛ ተራራ ላይ ያረፈችው የግሸኗ ንግሥት፣ የአንኮበር ቤተ መንግሥት፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ፣ የዘንገና ሐይቅ፣ የጎዜ መስጂድ፣ የሾንኬ መንደር መገኛ ነው፡፡

ደብረ ታቦር በደብረ ታቦር የሚከበርበት፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል የሚያሸበርቅበት፣ የሶለል፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና የእንገጫ ነቀላ የልጃገረዶች ጨዋታ የሚከወንበት፣ ከእነ ክብሩ የሚከበርበት፣ ድንቅ ምድር ነው፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ከእነ ክብራቸው ዘመናትን የተሻገሩ ቱባ ባሕሎች መገኛ ነው የአማራ ክልል፡፡

ጀግኖች ተወልደውበታል፣ ታሪክ ሠርተውበታል፣ ጥበብ እንደ ምንጭ ይፈልቅበታል፣ ዕውቀት ይገበይበታል፣ እሴትና ባሕል ይጸናበታል፣ ኢትዮጵያዊነት ይጠብቅበታል፣ከፍ ከፍም ይልበታል፡፡ ኢትዮጵያ የምትደምቅባቸው፣ ከፍ ከፍ የምትልባቸው፣ እልፍ አዕላፍ ጎብኚዎችን የምትስብባቸው ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኙት፣ የኢትዮጵያን የቀደምት ስልጣኔና ኀያልነት የሚመሰክሩት በዚሁ ድንቅ ምድር ይገኛሉ፡፡

ልደት በታላቅ ክብር የሚከበርበት፣ ጥምቀት የሚያሸበርቅበት፣ ግሸን ደብረ ከርቤ እጹብ የምታሰኝበት፣ የበዙ ባሕላዊና ታሪካዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት ነው የአማራ ክልል፡፡ ሙቀት ከሚበዛባቸው ከመተማ፣ ከቋራ፣ ከሁመራ እና በረዶ ከሚጋገርባቸው እስከ ሰሜን ተራራዎች የሚገኘው በዚሁ ክልል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዘብ እንደኾነ የሚነገርለት የአልጣሽ፣ የቃብቲያ ሑመራ፣ የጎደቤ፣ ቦረና ሳይንት እና ሌሎች የበዙ ፓርኮች፣ የውኃ ማማዎቹ የጮቄና የጉና ተራራዎች የሚገኙት በዚሁ ድንቅ ምድር ነው፡፡

የአማራ ክልል ታይተው የማይጠገቡ፣ በምስጢር የተጠበቁ፣ በጥበብ የረቀቁ መስህቦች መገኛና መፍለቂያ ነው፡፡ ታዲያ ሕዝብ ሁሉ ሊያዬው የሚጓጓለትን ድንቅ ምድር በዓለሙ ሁሉ የሚያሳይ ድንቅ መግቢያ በር አለ፡፡ ይህ ድንቅ በር የሕዝብን ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ታሪክና እሴት የሚያጎለብቱ ሥራዎችን ይሠራል። የሕዝብ መገለጫዎችን ለዓለም ያሳያል፡፡ በሕዝብ ዘንድ የሚከበሩትን፣ የሚወደዱትና የሚናፈቁ የረቀቁ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና ተፍጥሯዊ መዳረሻዎችን በትኩረት ያስተዋውቃል፣ ያሳያል፤ ታላላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች፣ የሚናፈቁ ታሪካዊ በዓሎች በዚህ ድንቅ ተቋም ይዘገባሉ፣ በቀጥታ ስርጭት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ይደርሳሉ፡፡ ይሄን ሁሉ የሚያደርገው በድንቁ ምድር የተገኘው፣ ድንቁ በር አሚኮ ነው፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአማራ ክልል ባሕል እንዲያድግ፣ የቱሪዝም ሃብት ከፍ እንዲል፣ እሴት እንዲጎለብት ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ወደ ድንቁ ምድር የሚያስገባ ድንቅ በር ኾኖም እያገለገለ ነው፡፡ በባሕልና ቱሪዝም ሀብት ላይ በጥራት እና በብቃት የሚሠራ ታላቅ ተቋም ነው አሚኮ፡፡ ታላላቅ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ በዓላትን በዘጋቢ ፊልም፣ በዜናና በቀጥታ ስርጭት በመሥራት ቀዳሚና ተመራጭ ኾኖም እየሠራ ነው፡፡ የመስህብ ሃብቶቹ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾኑ በጥራት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሥራውም በብዙዎች ተወድዷል፡፡ ብዙዎች ይከታተሉታል፡፡ ብዙዎች ያደንቁታል፡፡ ብዙዎችም ያመሰግኑታል፡፡ አሚኮ በክልሉ በባሕልና ቱሪዝም ልማት ላበረከተው አስተዋጽዖ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ አሚኮ በአማራ ክልል የሚገኙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶችን በተከታታይነት ያስተዋውቃል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአማራ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች ብቻ ሳይኾን በመላው ኢትዮጵያ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ተመራጭ ሚዲያ ነው፡፡ አሚኮ በአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ሃብት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው፡፡

ለአስተዋጽዖውም ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ ዕውቅና የተሰጠው ʺበመጀመሪያው የድንቅ ምድር አማራ የቱሪዝም ዕውቅና እና የሽልማት መርሐ-ግብር” ላይ ነው፡፡ በባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ ልማት ድንቅ ባለ ድርሻና አጋር አካል ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽዖ ነው ምስጋና እና ዕውቅና የተቸረው፡፡

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ድንቅ ምድር አማራ የቱሪዝምና ዕውቅና የሽልማት መርሐ-ግብርን ትናንት በጎንደር ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ ባደረገው መርሐ-ግብርም በልዩ ልዩ ዘርፎች አስተዋጽዖ ያበረከቱ ተቋማትንና ግለሰቦችን ሸልሟል፡፡ በክብር ከሸለማቸው ተቋማት መካከልም አሚኮ አንደኛው ነው፡፡ አሚኮ በድንቁ ምድር የሚገኙ ድንቅ ሃብቶችን ለዓለሙ ሁሉ እያስተዋወቀ፣ እየጠበቀና እያስጠበቀ ይቀጥላል፡፡ እግሮች ሁሉ ወደ ድንቁ ምድር እየመጡ እንዲጎበኙ፣ መምጣት ያልቻሉትም ድንቁን ምድር ባሉበት ኾነው እንዲመለከቱ እያደረገ ይገኛል፡፡

የድንቅ ምድር ድንቅ በር፣ የድንቅ ምድር ድንቅ አምባሳደር፣ የድንቅ ምድር በሩ ሠራተኛ፣ የድንቆች ድንቅ አገልጋይ ነው–አሚኮ፡፡ ድንቆች የሚመኩባቸውን፣ የሚከበሩባቸውን፣ ከፍ ከፍ የሚሉባቸውን እያከበረና እያስከበረ ለሕዝብ ሁሉ ያሳያል–አሚኮ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል” የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo Mudde 30/2015