
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ ገዳ እያሱ ቀበሌ የጤፍ ሰብልን እየጎበኙ ነው፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን በጤፍ ምርት ከሀገር 10 በመቶ ከአማራ ክልል ደግሞ 26 ከመቶ ይሸፍናል፡፡ በዞኑ 639 ሺህ ሄክታር መሬት ተሸፍኗል፤ ከዚህ ውስጥ 190 ሺህ ያህሉ የጤፍ ሰብል ሲሆን 150 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም የተዘራ ነው፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮም የሰብሉ የፍሬ አያያዝ የታቀደውን ምርት ማግኘት እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡
በአማራ ክልል በ2011/12 የምርት ዘመን 120 ሚሊዮን 739 ሺህ 607 ኩንታል የሰብል ምርት ማግኘት እንደሚቻል በተደረገው የቁም ሰብል ግምገማ መረጋገጡን ግብርና ቢሮው አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰሎሞን አሰፋ (ዶክተር) በዚህ ወቅት በክልሉ አጠቃላይ የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ዝናብ በማያስፈልግባቸው አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ ሰብልን በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በ2010/2011 የመኸር ምርት ዘመን የተገኘው 102 ሚሊዮን 952 ሺህ 970 ኩንታል ነበር፡፡ ለ2011/12 የምርት ዘመን ደግሞ 120 ሚሊዮን 739 ሺህ 607 ኩንታል የሰብል ምርት ማግኘት ተተንብይዋል፡፡
ምርቱ የሚሰበሰበውም በሰብል ከተሸፈነው 4 ሚሊዮን 435 ሺህ 717 ሄክታር መሬት ነው፡፡
መረጃውን ያደረሰን ጋሻዬ ጌታሁን ነው፡፡