
አዲስ አበባ፡ ጥር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የስነ ምግባር ደንብና ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከሙያ ማኅበራት ጋር እየመከረ ነው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሀብታሙ ሴኤታ እንዳሉት የወጪ ሀገራት በኮንስትራክሽን ኢንዳስትሪው ዘርፍ ውጤታማ የኾኑት ከሙያ ማኅበራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠራቸው ነው። ኢትዮጵያም ዘርፉን ለማሳደግ የሙያ ማኅበራትን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባታል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ማነቆ ያሏቸውን ችግሮች ያሏቸውን ጉዳዮችም ኢንጅነር ሀብታሙ አንስተዋል:-
👉ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ የምህንድስና ተመራቂዎች በተግባር የተፈተነ ክህሎት አለመኖር
👉ከ 60 እስከ 70 በመቶ የሚኾኑ ኮንትራክተሮች የዉጪ ሀገራት መኾናቸው
👉የኮንትራክተሮች የግንባታ መዘግየት፣ የግንባታ ጥራት ማነስ፣ ግንባራ ጀምሮ አለመጨረስ
👉በርካታ የግንባታ ግብዓቶች ከውጪ የሚገቡ መኾናቸው
👉በዩኒቨርሲቲዎች እና ሌላ ምርምር ተቋማት የሚሠሩ ጥናቶች በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሚስተዋለውን ችግር በተጨባጭ የማያሳዩ እና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የማይተገበሩ መኾኑ
👉ፕሮጀክቶችን የመምራትና የመከታተል አቅም ዝቅተኛ መኾን
👉ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መኾን
ስለኾነም ከላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚመራበት ፖሊሲ እየተዘጋጀ እንደኾነም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!