ቀሃ እንደ ዮርዳኖስ፤ ቀሳውስቱም እንደ ዮሃንስ!

123

ባሕር ዳር: ጥር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቀያሹ ገብረ ክርስቶስ፤ ጠበብቱ ወልደ ጊዮርጊስ የኾኑለት እና በ1632 ዓ.ም የተገነባው የፋሲል ግንብ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጉልላት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስድስት አብያተ መንግሥታት በአንድ ላይ፤ አርባ አራት አድባራት በአንድ ከተማ ላይ አስተባብራ ይዛለች ጎንደር ከተማ፡፡

ጎንደር የሚመጣ እንግዳ ባይተዋር ሳይኾን ባለሟል ኾኖ ይሰነባብታል፡፡ የጎንደር እንግዳ ጠዋት ጠዋት ከቤተ ክህነት በከበሮ፣ ቀን ቀን ከቤተ መንግሥት በነጋሪት፤ እና ማታ ማታ በአዝማሪዎች ማሲንቆ የተዋዛ ቀልድ ከቁም ነገር ጋር ይሸምታል፡፡ ጎንደርን የሚጎበኝ ታሪክና ባሕል፤ እምነትና ማንነት ድር እና ማግ ኾነው የሰሯት፤ ሐር እና ወርቅ ኾነው ያሳመሯትን የሀገር ጃኖ ተዘዋውሮ ይጎበኛል፡፡

ጎንደር ዘመን በስሟ የተሠየመላት፤ ሕንጻ ለክብሯ የቆመላት ጥንታዊት ከተማ ናት። “የጎንደሪያን ዘመን” የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ አውራ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ የአክሱም ሥልጣኔ ማደሻ፤ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መዳረሻ እና የመሃል ሀገር ዘመናዊ ፖለቲካ እርሾ ኾና ያገለገለች የሀገር ዋልታ እና ባለውለታ ናት፤ ጎንደር።

ጎንደር የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት መቀደሻ፣ የአያሌ አብያተ መንግሥታት መዳረሻ እና የብዙ ነገሥታት መናገሻ ነች፡፡ ጎንደር ከኢየሩሳሌም እስከ ሀረር በሃይማኖት፤ ከአስመራ እስከ ሰመራ በንግድ የተሳሰረች ጥንታዊት እና ታሪካዊት የሀገረ መንግሥት መዲና ኾና አገልግላለች፡፡ በተራሮች መካከል ታላቅ ክብር፤ በወንዞች መካከል ጥልቅ ፍቅር ጎንደር ውስጥ ሞልቶ ይፈስሳል፡፡ “አፈር ስኾን” ብሎ ማጉረስ፤ “አፈር ያርገኝ” ብሎ ማልቀስ አኹንም ድረስ የባለማተቦቹ መለያ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን እማማ ሲሉ የሚቀኙላት ጎንደር “የአፍሪካ ካሜሎት” የሚለው መጠሪያዋ በዘመኗ ሀገር የተሻገረ ገናና ስም እንደነበራት ማሳያ ነው።ጠምጣሚ ሊቃውንት እና አንጋች ሠራዊት ከአብራኳ የማይነጥፍባት ጎንደር “መታፈር በከንፈር” እንዲሉ ሕግ አርቃቂ፣ ንግግር አዋቂ እና በአጭር ታጣቂ ይበዛባታል፡፡

ጎንደር አብያተ ክርስቲያኖቿ የጸሎት፤ አብያተ መንግሥታቶቿ የችሎት ርትዕ ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል። ጎንደር እንኳን አብያተ መንግሥታቶቿ ዋርካዋ እንኳን የፍትሕ ችሎት አዳራሽ ነበር ይባላል። ጉናን በግርጌዋ፤ ራስ ደጀንን በራስጌዋ የተንተራሰችው የፋሲል መዲና፤ ከደንቀዝ እና አዘዞ በኋላ ለ250 ዓመታት ያክል ለዘለቀ መናገሻነቷ ፤ በዋናነት ሦስት ዓበይት ምክንያቶች ይነሳሉ ያሉን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ እና ተመራማሪው ዶክተር ሲሳይ ክፍሌ ናቸው፡፡

አጼ ፋሲል በ1624 ዓ.ም ከአጼ ሱስንዮስ ስልጣን ከተቀበሉ እና ዘውድ ከጫኑ በኋላ የአባታቸው መናገሻ እና የቤተ መንግስታቸው መዳረሻ ከነበረችው ጎርጎራ አሻጋሪ ደንቀዝ እና አዘዞን ለአራት ዓመታት መናገሻዎቻቸው አድርገው ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻ ግን ይላሉ ዶክተር ሲሳይ ለ250 ዓመታት በመናገሻነት ያገለገለችውን እና የአፍሪካ መዲና የተባለችውን ጎንደርን በ1628 ዓ.ም በመቀመጫነት መረጡ፡፡

እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ ለጎንደር በመዲናነት መመረጥ የብዙ ሕዝብ የጤና ሥጋት ከነበረው የወባ ወረርሽኝ ለመራቅ፣ በአንገረብና ቀሃ ወንዞች ለመጠመቅ እና በተራሮች ጋሻ ለመጠበቅ ሲባል ተመረጠች ይሉናል፡፡ ንግሥናን ከአባታቸው፤ ጥበብን ከፈጣሪያቸው የተቸሩት አጼ ፋሲል ጎንደር ታሪካዊ እና ጥንታዊ ከተማ ሆና ለመቆርቆሯ ባለውለታ ናቸው፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት አጼ ፋሲል በጎንደር ከተማ እምብርት ላይ የገነቡት የቤተ መንግሥት ማማ ከቀድሞው የአባታቸው ቤተ መንግሥት እስከ ጣና ሐይቅ ደሴት አሻግሮ እንዲያመላክት ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በፍሊጶስ እጅ ተጠምቆ ጥምቀትን ለኢትዮጵያ ምሳሌ እንደኾናት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል። የድኅነት ጥምቀትን ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ እጅ ተጠምቆ እንዳሳየው ኹሉ፤ ዛሬም “ቀሃ እንደ ዮርዳኖስ ቀሳውስቱም እንደ ዮሃንስ” ኾነው ጥምቀት በጎንደር በተለየ ድባብ ይታሰባል፡፡ ጥምቀትን በጎንደር መታደም ጎንደርን ከነታሪኳ፣ ወጓ፣ ባሕሏ እና ማንነቷ መመልከት ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቺርቤዋ ቴሳስ 30 ጌርክ 2015 ምሬት አሜታ
Next articleበኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ከሙያ ማኅበራት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።