“አዝማሪነት ነቃሽነት እና የወደፊቱን ጠቋሚነት ነው” የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ

169

ጎንደር፡ ጥር 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጥምቀት በዓል ዋዜማ ምክንያት በማድረግ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በርካታ ኹነቶች እየተካሄዱ ነው። በአጼ ቴወድሮስ ሐውልት ስር በተካሄደው የአዝማሪ ምሽት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ “አዝማሪነት ነቃሽነት እና የወደፊቱን ጠቋሚነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ጎንደር ስትጠራ አዝማሪነት እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ፊታውራሪነት አብሮ ይታወሳል። አዝማሪ ሙያው የረቀቀ፣ ጥበብን በመያዝ የሚያዝናና እና የክፋ ቀን መውጫ የጀግንነት ወኔን የሚቀሰቅስም ነው ሲሉ ከንቲባው ገልጸዋል።

አዝማሪዎች በንጉሡ ዘመናት በማዕረግ እና በሊቀመኳስነት ክብር ሕዝብን ከማዝናናት ባሻገር ማኅበራዊ ችግርንም እየነቀሱ በግጥም በመሸንቆጥ እንዲስተካከል ያደርጉ ነበር። ለዚህም የአዝማሪዎች መፍለቂያ የኾነችው የብርቧክስ መንደር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገች ገልጸዋል።

አቶ ዘውዱ አዝማሪዎች በጎንደር ከተማ በደማቁ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ውበቶች ስለመኾናቸውም ገልጸዋል። አዝማሪነት ትልቅ ሙያ በመኾኑ ከዘመን ዘመን እየተሻሻለ እና እያደገ እንዲመጣ አዝማሪዎች እና ሌሎች የሥነ ጥበብ ሰዎች የበኩላቸውን ማበርከት እንዳለባቸውም አቶ ዘውዱ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥር 08/2015 ዓ.ም ዕትም