
ደብረታቦር: ጥር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 204ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ እና የፊታውራሪ ገብርየ ፋውንዴሽን ምስረታ በአጼ መስክ ጋይንት ላይ እየተካሄደ ነው።
በዘመነ መሳፍንት ተወልደው የዘመነ መሳፍንት ፈውስ ተደርገው ይወሰዳሉ። የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ጠንሳሽ እና የጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት መሥራች እንደኾኑም ይነገርላቸዋል፤ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ።
የሀገራቸውን ችግር ጠንቅቆ የማወቅ እድል የነበራቸው ንጉሰ ነገስቱ ቴዎድሮስ ሀገራቸውን ከነበረችበት የመበታተን እና የመፍረስ አደጋ ለመታደግ እና የኢትዮጵያን አንድነት ለማጽናት በወሰዷቸው እርምጃዎች በበርካቶች ዘንድ ከዘመናቸው ቀድመው የተወለዱ ይሏቸዋል።
በንግሥና ዘመናቸው ከጦር እረፍት ሲያገኙ ሀገራቸውን እንደ ሌሎቹ ሀገራት በቴክኖሎጂ ለማዘመን የነበራቸውን ጥረት እና ፍላጎትም በጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር አሳይተዋል። ቴዎድሮስ ንጉስ ብቻ ሳይኾን የሀገር መሀንዲስ፤ ጦረኛ ብቻ ሳይሆኑ አንጥረኛም፣ መሪም እንኾኑ ይነገርላቸዋል።
ለእናታቸው አንድ የነበሩት ንጉሱ ለሀገራቸውም አንድ ኾነው በዘመናቸው ማምሻ ላይ ብቻቸውን ሲቆሙ ከጎናቸው የነበረው ታማኝ ባለሟላቸውና “የቴዎድሮስ ቀኝ እጅ” የተባለለት ፊታውራሪ ገብርየ ነበር። ፊታውራሪ ገብርየ የጦር መሪ እና የንጉሰ ነገስቱ አማካሪ እንደነበር ይነገራል።
ጠላት በርትቶባቸው፣ ወገን እየከዳቸው እና የውጭ ወራሪ አሰፍስፎባቸው በንግሥና ዘመናቸው ማብቂያ ከእንግሊዞች ጋር ጦር የገጠሙት አጼ ቴዎድሮስ ከመቅደላ አምባ ቅርብ እርቀት ላይ የጦር መሪያቸውን በእለተ ስቅለት ማለፍ የሰሙት ንጉሱ፦
“ገብርየ ገብርየ የጦር መኮነኔ፣
አሽከሬም አይደለህ ወንድሜ ነህ ለኔ” በማለት አልቅሰው እንደሸኙት ታሪክ ይነግረናል።
የንጉሰ ነገስቱ 204ኛ ዓመት የልደት በዓልም ከነፋስ መውጫ በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘው እና አጼው በእረፍት ላይ ሳሉ ለጋይንቶች “የራስነት” ማዕረግ በሰጡበት አጼ መስክ ላይ እየተዘከረ ነው። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር
በተገኙበት እየተከበረም ይገኛል። የፊታውራሪ ገብርየ ፋውንዴሽን፣ መታሰቢያ ሃውልት፣ የባሕል ማእከል እና ቤተ መጻሕፍት ይመሰረታልም ተብሏል።
በዝግጅቱ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች እና እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!