የጋዜጠኛው ምልከታ፤ ከጣና እስከ ላልይበላ::

407
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) አወጣጣችን ከወትሮው ይለያል፡፡ አርምሞን በሚያሳብቅ የአዕዋፋት ዝማሬ፣ ለዓለሙ ሁሉ መዳን በጸሎት በሚተጉ የቤተ አምልኮ ድምፆች፣ ውፍረትን ለመቀነስ በሚተጉ የጤና ስፖርተኞች የማለዳ ሩጫ እና ኑሮን ለማሸነፍ ቀድመው ተነስተው በሚታትሩ ባተሌዎች መካከል በጠዋት የተጀመረ ጉዞ አይደለም፤ የዛሬው ጉዟችን፡፡
 
ይልቁንስ የረፋዷ ፀሐይ በባሕር ዳር ሰማይ ስር የበላይነትን ወስዳለች፡፡ ወበቅ በጀመረው የረፋድ ላይ ሙቀት በመኪና መስኮት የሚገባው ቅዝቃዜን እ…እ…ፍ…ፍ… እያደረገ የሚረጨው አየር ሌላ የሕይወት እስትንፋስ ይዘራል፡፡ ከወደ ጣና ሐይቅ የሚመጣው ነፋስ ደግሞ የባሕር ዳርን የበረሃ ገነትነት ለመመስከር የሚጣድፍ ይመስላል፡፡ የመንገድ ዳር ዘንባባዎቿ ጎንበስ ቀና ሲሉ እንግዳን ለመቀበል የተዘጋጁ ይመስላሉ፤ እንደኔ ዓይነት ተጓዥ መንገደኞችን በትህትና መልካም ጉዞ የሚሉ ይመስላሉ፡፡
 
ባሕር ዳርን ከወደ ኋላችን እየተውን ጣናን በቅርብ ርቀት ቀስ በቀስ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ እየተመለከትን ተሸኛኘን፡፡ ገና ከተማዋን ለቅቀን እንደወጣን የፀደይ ወቅት ፀጋ የተቀዳጀው እና አረንጓዴ የአርሶ አደር ማሳን እየማተርን ዘንዘልማ፣ ሐሙሲት፣ ጉማራ፣ ወረታ …እያልን ቀጠልን፤ የደራ እና ፎገራ ኩታ ገጠም መሬቶች በበቆሎ እና ሩዝ ማሳ አሸብርቀው ልቦናን ይሰርቃሉ፤ በተስፋም ያጠግባሉ፡፡ የክልሉ ደረቅ ወደብ ወደ ሆነችው ወረታ ከተማ ገብተናል፡፡
‹‹ደረቅ ወደብ›› ስል የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት ድርጅት እያስገነባው ያለው ስምንተኛው የወረታ ደረቅ ወደብ ግንባታ ትዝ አለኝ፡፡ ግንባታው ሲጀመር እና አጋማሹ ላይ ሲጎበኝ በሥራ ምክንያት ተገኝቼ ነበር፡፡ ከወረታ-ጎንደር በሚወስደው መስመር ትንሽ እንደተጓዝን ወደ ቀኝ በኩል ወደ ደብረ ታቦር-ወልድያ የሚያቀናውን መገንጠያ ይዘን ትንሽ እንደተጓዝን ‹‹የወረታ ደረቅ ወደብ›› ግንባታን መንገዳችን ዳር አገኘነው፡፡ በ20 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የወደቡ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በ90 ሚሊዮን ብር ወጪ በግንባታ ላይ ነው፤ አልተጠናቀቀም፡፡ የአስተዳደር ቢሮ፣ የጥበቃ ቤት፣ አጥር እና መደበኛ ግንባታዎቹ አሁንም በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ምን ላይ እንደደረሰ በቅርቡ እንጠይቃለን፤ ለማንኛውም አሁንም ሠራተኞች በሥራ ላይ መሆናቸውን ተመልክተን ወደፊት ጉዟችንን ቀጥለናል፡፡
 
አውራ አምባን በቀኝ አሻግረን እያየን ትንሽ ስለአኗኗር ፍልስፍናቸው አሰብን መሰል መኪናችን ውስጥ ያለነው ተጓዦች ዝም ብለናል፡፡ በነገራችን ላይ የአውራ አምባ ማኅበረሰብ አባላት ሥራን ባለመምረጥ፣ በፆታ እኩልነት፣ ልዩ በሆነ የአረጋውያን እንክብካቤ ባሕላቸውና በጠንካራ አብሮነታቸው ዓለም ያወቃቸው ናቸው፡፡ የአውራ አምባ ማኅበረሰብን ልዩ ባሕል ለዓለም ያደረሰው የአማራ ቴሌቪዥን በ1990ዎቹ አጋማሽ ነበር፤ የማኅበረሰቡ ምሥረታ ደግሞ በ1960ዎቹ አጋማሽ ተጠንስሶ በ1980ዎቹ እውን መሆኑ ይታወቃል፡፡
 
ስለአውራ አምባ ማኅበረሰብ እንዲህ እያሰላሰልኩ መኪናችን እየከነፈ ዓለም በር ደርሷል፤ አሁንም ጉዟችን ቀጠለና የዓለም ሳጋን ደን እየማተርን በዝንጆሮዎቹ እና በጦጣዎቹ የመንገድ ዳር ትይንት ፈገግ እያልን ደብረ ታቦር ገባን፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ርዕሰ ከተማ ደብረ ታቦር ከሀገራችን የጥንት ከተሞች አንዷ ብትሆንም የዕድሜዋን ያክል ያላደገች፤ በጤና ቋንቋ የቀነጨረች ከተማ ሆና ቆይታለች፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር በዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የተጀመረባት (ጋፋት) ደብረ ታቦር ለዘመናት ዕድገቷ አዝጋሚ ነበር፡፡ የጉና ጥብቅ ደን በቅርብ ርቀት፣ በሐገራችን የመጀመሪያው የኢንዳስትሪ መንደር ‹‹ጋፋት›› ከጥጓ፣ ታሪካዊው የተክሌ የአቋቋም ትምህርት ቤትና ዕድሜ ጠገቡ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በራስጌዋ እንዲሁም የዓፄ ቴዎድሮስ እና የሌሎች ነገሥታት መኖሪያ ፍርስራሽ ‹‹ሰመርንሃ›› በግርጌዋ አቅፋ ብትይዝም የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኝ እምብዛም አይታይባትም፡፡ በነገራችን ላይ ንግሥተ ነገሥታት ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ክርስትና የተነሱት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ነበር፤ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን ለጋብቻ ደብረ መዊዕ (ጎንጅ ቆለላ ወረዳ) ላይ አጭተው የሄዱም ደብረ ታቦር ላይ ከዓፄ ዮሐንስ ጋር ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሸዋ ሲመለሱ ነበር፡፡ ለማንኛውም ደብረ ታቦር አሁን እንደ ወጣት የተነቃቃች መስላለች፤ ይህንን እየታዘብን ጉዟችን ወደ ፊት ቀጥሏል፡፡
 
ከጉና እስከ ጋሸና እየተዘናፈለ የወጣ የገብስ እና የስንዴ እሸት በነፋሱ ሲቅለሰለስ እያዬን፤ በባቄላው አበባ የሚፍለቀለቁ ዓይኖችን እያስታወስን፣ በአተሩ እሸት ሽታ እየታወድን ከኅሩይ አባ አረጋይ እስከ ጋሳይ፤ ከክምር ድንጋይ አስከ ጥጥራ፤ ከሳሊ እስከ ጎብጎብ ተፈጥሮን እያደነቅን ተጓዝን፡፡ አሁን ወደ ራስ ጋይንቶች መናገሻ ነፋስ መውጫ ልንደርስ ነው፡፡ በመንገዳችን አሻጋሪ ከነፋስ መውጫ ጥግ ስር የዙር አባ ፀርሀ አርያም ቤተ ክርስቲያን ትታያለች፡፡ ስለዚች ታሪካዊ ገዳም አንድ ወቅት ላይ ‹‹ገሊላ ላይ ነኝ›› በሚል ርዕስ በሁለት ክፍል እንዳስነበብኳችሁ አስታውሳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ራስ ጋይንት›› ስለሚባለው የአራቱ ወረዳዎች ታሪክ አንድ ቀን አወጋችኋለሁ፤ አሁን ነፋስ መውጫ ላይ ነን፡፡ ያልተለመደችው ፀሐይ ብልጭ ያለችባት የነፋስ መውጫ ከተማ በነዋሪዎቿ ዘንድ ብርቅ የሆነች ትመስላለች፤ ብዙ ሰው የፀሐይን ሙቀት ውጪ ላይ ሲያጣጥም እያስተዋልን እንደሌሎች ከተሞች ነፋስ መውጫን በጨረፍታ አስተውለናት አለፍን፡፡
 
‹‹በቅሎ አግት›› ስንደርስ መኪናችን አቁመናል፡፡ ጨጭሆ መድኃኒያለም ካቴደራል ላይ ወርደን ስላለፈው ልናመሠግን ስለመጪው በጎ ፈቃዱን ልንጠይቅ ነው አወራረዳችን፡፡ ለማንኛውም ነፋስም አግኝተን እግራችንም አፍታትተን ጸሎታችንን አድርሰን ከጎንደር ወደ ወሎ ምድር ገባን፤ የአስቴር አወቀ ‹‹ጨጨሆ›› ዘፈኗ ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ድንገት ትዝ አለኝ፡፡ የኪነ ጥበብ ተጽእኖ ይኼኔ ነው ከልቤ የገባው፤ አሁን ቤተ ክርስቲያን ላይ ሙዚቃ ትዝ ይላል?
‹‹በእናቱ ከወሎ፣ ባባቱ ከጎንደር
ተወለደ ሸጋ ከጨጨሆ መንደር›› ስትል በእዝነ ኅሊናዬ ውልብ አለብኝ፤ ቆይ ግን አስቴር ምን ለማለት ፈልጋ ነው?
 
አዝመራው ደርሷል፡፡ ከአረንጓዴ በላይ ሽበት የደረበ ገብስና ስንዴ ‹‹ደረስኩ ደረስኩ›› እያለ ይመስላል፡፡ ጠመዝማዛው መንገድ ለሹፌሩ እንጃ እንጂ ለእኛ ተመችቶናል፡፡ እጥፍ እጥፍ እያልን ሲያሻን በግራችን ሲያሻን በቀኛችን እስከ ከዓድማስ እስከ ዓድማስ ተራራና ሸለቆ፣ ሸንተረርና ሸጥ፣ ሜዳና ገድል እያየን ሐሴት እያደረግን ጋሸና ገብተናል፡፡
 
ስለጋሸና ትንሽ የምነግራችሁ አለኝ፡፡ ጋሸና አራት ዓይና ከተማ፤ መስቀለኛ ‹‹ቀበሌ›› ናት፡፡ ቀበሌ ያልኳችሁ ያለነገር አይደለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ጋሸና በክልላችን ከሚገኙ በርካታ ከተማ አስተዳደሮች ያልተናነሰ ከተሜ ቀመስ አቅም አላት፤ ግን ደግሞ አንድ የገጠር ቀበሌ ናት፡፡ ከደሴ-ኮን-ጋሸና-ላሊበላ፣ ከሰቆጣ-ላሊበላ-ጋሸና፣ ከወልዲያ-ጋሸና-ጋይንት-ደብረ ታቦር የሚደረግ ጉዞ ጋሸናን ሳይነካ አያልፍም፡፡ በኢንቨስትመንት ዘርፍም መነቃቃት ላይ ብትሆንም የምትመራው ግን እንደ አንድ የገጠር ቀበሌ መዋቅር ነው፡፡ ባንኮችን ጨምሮ አነስተኛ እና መካከለኛ ፋብሪካዎች የሚጠበቁት ከሦስት ባልበለጡ ፖሊሶች እና በከተማዋ ሕዝብ የነገ የከተሜነት ተስፋ ነው፡፡ ነዋሪዎቿ ቅሬታ አላቸው፡፡ እስከ ክልል ድረስ ሄደው ከተማ አስተዳደር እንድትሆን እየጠየቁ እንደነበርም አውቃለሁ፤ ምላሹ ምን እንደሆነ ለጊዜው ባላውቅም፡፡ ለማንኛውም አንድ ቀን ስለጋሸና እንጠይቃለን፡፡
 
ከጋሸና ወደቀኝ ታጠፍን፡፡ ድምፅ ሳታሰማ፣ ሳታቃስት እና ሳትንገራገጭ እረግታ ስትሄድ የነበረችው መኪና አዲስ አመል አመጣች፡፡ እየየዋ ለጉድ ሆነ፤ ከላይ አንስታ ወደ ታች ከግራ መልሳ ቀደ ቀኝ ትንጠን ገባች፤ እርጎ ብንጠጣ ኖሮ ቅቤ የሚወጣን ይመስለኛል፡፡ ጪስ ያላየንባት መኪና አቧራ ትነፋብን ጀመረች፡፡ እምንሄደው እኮ ወደ ታላቁ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የማንነት አሻራ ዘመን ወደ ተሸጋገረበት የላልይበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት መከተሚያ፣ ደብረ ሮሃ፣ ላስታ ላልይበላ ነበር፡፡ እንደ ኔትወርክ የሚቆራረጥ አስፓልት 64 ኪሎ ሜትሩን 640 የራቀ ያክል አስመሰለብን፤ ግን ምሥጋና ለሾፌራችን ትኩረታችንን ከተፈጥሮ ሊነጥል የሚታገለውን መንገድ ቀስ እያለ ወደ ተመስጧችን እየመለሰን ነው፡፡ ተፈጥሮ በዚህም ውብ ናት፤ ማራኪ መልክአ ምድር፣ ውብ ማዕዛ እና ገራገር ፊት በየመንገዶቻችን እናስተውላለን፡፡
 
ላስታ ላልይበላ ቀይ መሬት፣ ታሪክ ያቀለመው ታላቅ ማንነት፣ እምነትና መንግሥት አንድ የሆኑበትን ዘመን የሚያስታውስ አሻራ ከይምርሃነ ክርስቶስ እስከ ብልብላ ጊዮርጊስ፣ ከአሸተን ማሪያም እስከ ናኩቶ ለአብ በነዚህ አድባራት ስር የቆየ፣ የነበረና የሚኖር ጥበብ አለ፡፡ ላልይበላ ገብተናል፤ በዚሁም ቆይታ የምናደርግ ይመስለናል፡፡ በቆይታችን የምንዳስሰውንና የምናየውን ሁሉ በጨረፍታ እንነግራችኋለን፡፡ እስከዚያው ግን ሠላም ሁኑ ብለናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- ከድረገጽ
Previous articleበደም ልገሳው የታየውን መተባበር የክልሉን ሠላም እና ልማት በሚያጠናክሩ ተግባራት መድገም እንደሚገባ ርዕሰ መሥተዳድሩ ጠየቁ።
Next article‹‹የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መላ፤ ጎንደር የመጣ ተማሪ አንድም ዕውቀት ሌላም እናት›› የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት