
ባሕር ዳር: ጥር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የታደለች እናት አንድ ወልዳ እንደ ሺህ እናት ትጠራለች፣ የታደለች ማሕጸን አንድ አፍርታ ትመረቃለች፣ አንድ አፍርታ ትባረካለች፣ አንድ አፍርታ ከፍ ከፍ ትላለች፡፡ የታደለች እናት በአንድ ልጇ ለዘመናት ትጠራለች፣ እንኳን ጸነስሽ፣ እንኳን ወለድሽ፣ እንኳንም ዘር ሰጠች ትባላለች፡፡
የታደለችው እናት አንድ ወለደች፣ በአንድ ልጇ ተባረከች፣ የታደለችው እናት ለእናት ሀገር ታላቁን ስጦታ ሰጠች፡፡ ልጇ በተነሳ ቁጥር እርሷም ትነሳለች፣ ልጇ በተወሳ ቁጥር ትወሳለች፤ አንድያ ልጇ እልፍ ታሪኮችን ሰርቷል፣ በአባቶቹ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሀገር አጽንቷል፣ ትውልድ አኩርቷል፡፡
አንድ ወልዳ አብዝታ ተመርቃለች፣ አብዝታ ተባርካለችና በስብዕና ያሳደገችው ልጇ የደከመውን ዙፋን አበረታው፣ የተበታተነ የመሰለውን ሰበሰበው፣ በመንደር የሚቧደኑትን ቀጣቸው፣ በአንድ ሀገር ላይ መከፋፈል ያሰቡትን አስታገሳቸው፡፡ የመሳፍንት ዱላ ለበረታባቸው ደረሰላቸው፣ ኀያል ንጉሥ ለናፈቃቸው በአስፈሪ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አሳያቸው፣ ጌታ ኾይ ሀገር የሚፈራ ንጉሥ ስጠን ብለው ለተሳሉ የስለት ፍሬ ኾናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከጠላት ጠበቃት፣ ዙፋኗን ከፍ አድርጎ ራዕዩን አሰነቃት፣ ጀግንነቱን አስታጠቃት፣ እንደ ቀደሙት አባቶቹ ጠበቃት፣ ከእርሱም በኋላ ለሚመጡት ከእነ ክብሯ ጠበቃት፣ አስጠበቃት፡፡
ታላቅ ራዕይ የሰነቀ፣ ጀግንነት የታጠቀ፣ እምነት እና ቃል ኪዳን ያጠበቀ ኀያል ነው፡፡ ሀገሩን አብዝቶ የወደደ፣ ለኢትዮጵያ ፍቅርና ክብር ሲል በራሱ ሕይወት ላይ ሞትን የፈረደ ክንደ ብርቱ፤ ስመ ገናና ነው፡፡ ሀገርን እንደ እርሱ የወደደ ከዬት ይገኛል? ኢትዮጵያን እንደ እርሱ ያፈቀረ ከዬት ይመጣል? እርሱ ለክብሯ ጠላቶቿን ቀጥቶላት፣ አንድ አድርጓት አልበቃው ሲል፣ ስለ ፍቅሯ በስሟ ምሎ የራሱን ሕይወት የሰጣት የሀገር ፍቅሩ ልክ የሌለው ጀግና ነው፡፡
ልቡን ያመነ ጀግና፣ ለሀገሩ የታመነ ልበ ኩሩ ነው እርሱ፡፡ በዓለ ጥምቀት ሊከበር ሽርጉድ በዝቷል፣ ወይዛዝርቱ እንሶስላ መሞቁን፣ ሹርባ መሠራቱን፣ ወንዝ ወርደው ቀሚስና መቀነታቸውን ማጠቡን ተያይዘውታል፡፡ ጎበዛዝቱ ሱሪያቸውን እያሳመሩ፣ ጎፈሬያቸውን እየከመከሙ፣ ሽመላቸውን እየወላወሉ ነው፡፡ ብቻ በየቀዬው የጥምቀት ሽርጉዱ በዝቷል፡፡ ታዲያ ይህ በሚኾንበት ጊዜ እሜቴ አትጠገብም የመውለጃቸው ጊዜ ደርሶ ደካክሟቸዋል፤ እሳት አርግዘው ኖረዋልና ይደክማቸው ጀምሯል፡፡
መውለጃቸው ከወረኃ ጥር እንደማያልፍ እየታወቃቸው ነው፡፡ ጥምቅትን አሳልፌ ወይሰ ከዚያ በፊት እወልድ ይኾን እያሉ እያሰቡም ነበር፡፡
ታቦቱ ሊወጣ፣ ጥምቀት ሊከበር፣ ከተራው ሊከተር፣ ጎዳናው ሊደምቅ ቀናት ሲቀሩት እሜቴ አትጠገብ ምጥ ተያዙ፡፡ ወገን ዘመድ ተሰባሰበ፡፡ አርግዘውት የኖሩት እሳት ተወለደ፡፡ ወገን ዘመድ ደስ አለው፣ እልልታው ቀለጠ፣ ደስታም ኾነ፡፡ አበው እርሱ ሲወለድ ከሌሎች ልጆች የተለዬ ምልክት ታይቷል ይላሉ፡፡ ይህም ምልክት የወደፊት ታላቅነቱን የሚያሳይ ነበር ይባላል፡፡ ይህ ልጅ የተለወደው ጥር 6/1811 ዓ.ም ነበር፡፡
ይህን ልጅ እናቱና አባቱ ካሳ ሲሉ ስም አወጡለት፡፡ ያ ለታላቅ ነገር የታጨ ልጅ በጥበብ አደገ፡፡ በልጅነቱ ከጥበብ ጋር ተዋወቀ፡፡ ፊደል ቆጠረ ዳዊት ደገመ፡፡ ገና በልጅነቱ በሚያሳያቸው ነገሮች እረኞች አስቀድመው ተነበዩለት፣ በጋራና በጋራ ኾነው ኀያል ንጉሥ እንደሚኾን ተናሩለት፡፡ ሁልጊዜ ከፍታን የሚመኘው ብላቴና ገና በለጋ እድሜው ራዕይ ሰነቀ፡፡ በዘመኑ የነበረውን ሥርዓት ገርስሶ ኀያል ነገር መመስረትን አሰበ፡፡ ለዚህ የሚረዳውን ሁሉ አደረገ፡፡ የማይረታ ጀግና ጦረኛ፣ ሩቅ አሳቢ ጥበበኛ ነውና ሀገሩን ያስከብራት ዘንድ ወደደ፡፡ የወደደውን እና የተመረጠበትንም አደረገ፡፡
ካሳ ስመ ገናና ኾነ፣ የገጠሙትን ሁሉ አሸነፋቸው፣ የነኩትን ሁሉ ጣላቸው፣ መሳፍንቱን እየገረሰሰ ወደ ከፍታ ገሰገሰ፡፡ ዘመነ መሳፍንትንም ቋጭቶ በደረስጌ ማርያም ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ ነገሠ፡፡ በዘመኑ አያሌ ታሪኮችን ሠራ፡፡ አበው ቴዎድሮስን ለሀገሩ የተፈጠረ፣ ለሀገሩ የኖረ፣ ለሀገሩ ምቾቱንም ሕይወቱንም የሰጠ ነው ይሉታል፡፡ እርሱ ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ የጦር ስልቱና ብልሃቱ በጠላትም በወዳጅም የተመሠከረለት ኀያል ነው፡፡
ጳውሎስ ኞኞʺ ቴዎድሮስ በመሳፍንት ተከፋፍላ የወደቀችውን ሀገራቸውን ለማንሳት የተነሱ ታላቅ ሀገር ወዳድ ነበሩ፡፡ ቴዎድሮስ በብዙ ገዢዎች ተቆራርጣ የነበረችውን ኢትዮጵያን እንደነበረችው አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ድካም ደክመዋል፡፡ ያለ እረፍት ሠርተዋል፡፡ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከተለያዩ መኳንንት አገዛዝ አውጥተው፣ በአንድ መንግሥት ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ የጥርጊያውን መንገድ የከፈቱ ዋናው መሐንዲስ ናቸው፡፡ ለአጤ ዮሐንስና ለአጤ ምኒልክ መጓዣውን መንገድ በሕይወታቸው የከፈቱ ቴዎድሮስ ናቸው” በማለት ጽፈዋል፡፡
ቴዎድሮስ ሀገሩን አንድ አድርጎ በስልጣኔ ለማስቀመጥ ራዕይ ሠንቆ ያለ እረፍት የሠራ ንጉሥ ነው፡፡ እንደ አባቶቹ በአማሩት በጎንደር አብያተ መንግሥታት መቀመጥ ሳያምረው ከቦታ ቦታ እየተመላለሰ ለሀገሩ አንድነት እና ከፍታ የታተረ ኀያል፣ የሀገር ፍቅሩ ወሰን የለሽ ነው፡፡
ጠላት የሚበዛባት ኢትዮጵያ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እንድትጠበቅ፣ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች በመንገድ እንዲገናኙ፣ ወታደሩ በአንድ የጦር መሪ ሥር እንዲታዘዝና ሌሎች አያሌ ለውጦችን በሀገሩ ያስጀመረ፣ ሠርቶ የማይደክመው ነው ቴዎድሮስ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ሲሳይ ሳህሌ (ዶ.ር) አጼ ቴወድሮስ የጎደለን ነገር በደንብ ማዬትና ጎደሎውን መሙላት የሚችል ጠቢብ መሪ ነው ይሉታል፡፡ የኢትዮጵያን ችግር በብልሃት የተመለከተ፣ ችግሯንም በጀግንነት እና በልበ ሙሉነት ለመፍታት የተነሳ መሪ ነበር፡፡ አስፈሪ ሀገረ መንግሥት፣ ጠንካራ ሀገር እንዲኖር ያለ ድካም ታትሯል፡፡ ዘመነ መሳፍንት ቋጭቶ ለአንዲት ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ጥሏል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ እና መንገድ ጠራጊም ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከቴዎድሮስ ታሪክ በብዙው መማር እንደሚገባውም ዶክተሩ ያስገነዝባሉ፡፡ ለሥርዓት ተገዢ የኾነ ሕዝብ፣ ሥርዓት የሚያከብርና የሚያስከብር መንግሥትም ያስፈልጋል፡፡ ሥርዓት ያለው ሕዝብ ወደ ፊት ባይራመድ እንኳን ወደኋላ አይንሸራተትም፣ ክብሩን አስጠብቆ ይቆያል ነው የሚሉት፡፡
አቤ ጉበኛ ʺ የቴዎድሮስ ሙያና ውለታ እጅግ ልቆ ስለምናገኘው ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ መድረክ ላይ ጎልቶ ይታያል ብንል ጠባብ አገላለጽ ይኾናል፡፡ ቴዎድሮስ ገና ወደፊት በሚመጣው የኢትዮጵያ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እንቁ ያበራሉ፡፡ የዛሬውን እና የወደፊቱም የኢትዮጵያ ትውልድም በመንፈስ ይገዙታል” ብለዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መንፈሱ አሁንም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የሚንቀለቀል ሁልጊዜም እንደ አዲስ የሚወደድና የሚፈቀር፣ የሀገር ፍቅርና አንድነት በተነሳ ቁጥር የሚነሳም ኀያል ነው፡፡
ቴዎድሮስ በሀገር ፍቅር የተቃጠለ፣ ለሀገር ፍቅር ራሱን አሳልፎ የሰጠ ጀግና ነው፡፡ እርሱ እየተወደደ፣ ፍቅሩ በትውልድ መካከል እየሰረፀ የሚሄድ የዘመናት ንጉሥ ነው፡፡ እርሱ በአንድነት፣ የፀና ኢትዮጵያዊነት፣ የብርታት እና የአሸናፊነት ምልክት ነው፡፡ ንጉሥ ኾይ ስለ ክብር መድከምን፣ ስለ ሀገር መስዋእት መኾንን፣ ስለ ሠንደቅ ክብር ደምና አጥንት መገበርን አስተምረኻል፣ ኢትዮጵያን ወድደህ አስወድደሃል፣ አፍቅረህ አስፈቅረሃል፣ በጀግንነትህ ለትውልድ አቆይተሃልና ሁሌም ትመሰገናለህ፣ ሁሉም በትውልድ መካከል ቴዎድሮስ፣ ቴዎድሮስ እየተባልክ ስትጠራና ስትሞገስ ትኖራለህ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!