
ባሕር ዳር: ጥር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የታሪክ አስኳሎች መገኛ ከኾኑ አካባቢዎች መካከል ሸዋ ተጠቃሽ ነው።ታሪክን እና ድንቅ የተፈጥሮ በረከትን በማስተዋወቅ፣ በመጠበቅና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ደግሞ ከዘርፉ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
የሰሜን ሽዋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ቅመም አሽኔ እንዳሉት “ሸዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው”፣ጥምቀትን በኢራንቡቲ የተሳካ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ሰፊ እንቅስቃሴ አየተደረገ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል ደምቆ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራንቡቲ ቀበሌ ታሪካዊ ናት። ጥምቀትን ከ620 ዓመታት በላይ 44 ታቦታት “አምሳለ ዮርዳኖስ” በሚባለው የሸንኮራ ወንዝ ጥምቀተ-ባሕርን፣ በአንድ ሜዳ በድንቅ ሁኔታ ስታከብር ኖራለች።
የምንጃር ሸንኮራ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ እንዳስታወቀውም የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በኢራንቡቲ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ሥፍራው የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።
ጥምቀትን በኢራንቡቲ ማክበር ታሪካዊነቱንና ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኑን ፤ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ተከታታይነት ያለው የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል ኀላፊዋ።
አካባቢውን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ሥራ ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት እና ውብ አካባቢ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተላይም ጥምቀት በኢራንቡቲ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከኦሮሚያ ክልል አጎራባች ወረዳዎች ጋር በጋራ በአብሮነት እና በአንድነት የሚከበር በዓል ነው ይላሉ ኀላፊዋ።
ከሃይማኖታዊ ፋይዳውም በሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ፤ በጋራ ጉዳይ ላይ በትብብር፣በሕብረት የመስራትን ፤ በዓልን በጋራ የማከበርን ፤ በተግባር የሚታይበት ነውና ማኅበራዊ ፋይዳውም የጎላ ነው ብለዋል።
ጥምቀትን በኢራንቡቲ ታዳሚዎች በሰላም በዓሉን አክብረው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት ተስርቷል ብለዋል ኀላፊዋ።
ከዞን እስከ ወረዳ ወጣቶች፣የጸጥታ አካላት፣የሃይማኖት አባቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር በቂ ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት።
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከተማ አርርቲም እንግዶቿን በምቾት እንድትቀበል ለማድረግ በሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ኑ ጥምቀትን በምንጃር ሸንኮረዋ የውብ ታሪክ ባለቤት በኢራንቡቲ በጋራ እናክብር ጥሪያቸው ነው።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!