ʺየንጉሥ ራት፣ በጎንደር አብያተ መንግሥታት”

160

ባሕር ዳር: ጥር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ንጉሡና ንግሥቷ በታላቅ አጀብ ወደ ግብር አዳራሹ ይገባሉ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በታላቅ አጀብ ንጉሡና ንግሥቷን ያጅባሉ፣ የጦር አበጋዞች አስፈሪውን ልብሳቸውን ለብሰው፣ ጋሻና ጦር ጨብጠው ይገባሉ፣ ወይዛዝርቱ አምረውና ተውበው ይታያሉ፡፡ ሊቃውንቱ ካባውን ለብሰው፣ ሻሻቸውን ጠምጥመው በክብር ይመጣሉ፡፡
በታላቅ አጀብ የሚወጡት ነገሥታት በግብር አዳራሹ በክብር ዙፋን ይቀመጣሉ፣ ጦርና ጋሻ በያዙ ጀግኖች በግራና በቀኝ ይጠበቃሉ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ እንደ ማዕረጋቸው በክብር ይታያሉ፣ የጦር አለቆቻቸው እንደ ደረጃቸው ይሰደራሉ፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች ለአገልግሎት ይፋጠናሉ፡፡

የምንትዋብ ልጆች ጠጁን ይጥላሉ፣ ወይኑን ያወርዳሉ፣ ጠላውን ይጠምቃሉ፣ ዶሮ ወጥ አሳምረው ይሠራሉ፣ ምንትዋብ እንደ አደረጉት፣ እርሳቸውም እንደሚወዱት፣ ነገሥታቱም የሚደሰቱበት ባልትና በቤተ መንግሥቱ አጸድ ሥር ይሠራል፡፡ የግብር አዳራሹ በመልካም ማዕዛ ይታወዳል፣ የጎንደር ወይዛዝርት አምረውና ተውበው ድግሱን ይደግሳሉ፣ እልፍኙን ያሳምራሉ፡፡ ጎበዛዝቱ ፍሪዳውን ይጥላሉ፣ ጮማውን ይቆርጣሉ፡፡
ንጉሡ ግብር በሚያበሉበት ጊዜ ገበሬው፣ ነጋዴው፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ታናናሾቹ እና ታላላቆቹ፣ የሩቆቹና የቅርቦቹ ሁሉ ይገኛሉ፡፡ እኒያ ታላላቅ ነገሥታት ግብር የሚያበሉት በአንድነት ነው፡፡ ገበሬዎች ከቀያቸው ይመጣሉ፣ ነጋዴዎች ከንግድ ሥፍራቸው ተጉዘው ይደርሳሉ፣ የንጉሡ ባለሟሎችም ከዚያው ከቤተ መንግሥቱ ይወጣሉ፡፡ በአንድነት በግብር አዳራሽ ይሰባሰባሉ፡፡

ግብሩ በምስጋና ተጀምሮ በደስታና በፍስሃ ሲበላ፣ ጠጅና ፍሩንዱሱ ሲጠጣ አዝማሪዎች ማሲንቋቸውን ይዘው ግጥም ይደረድራሉ፣ አስቀድመው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፣ ለንጉሡና ለንግሥቷ የሙገሳ ግጥም ያወርዳሉ፣ በግጥሞቻቸው ትንቢት ይተነብያሉ፣ ነገን ያሳያሉ፣ ጀግናውን ያጀግናሉ፣ ፈሪውን ይንቃሉ፣ ሰነፉን ይሳደባሉ፣ ብርቱውን ያደንቃሉ፡፡ በዚያ የግብር አዳራሽ ደስታ ይኾናል፣ ዓለም ይታያል፡፡
የቀደመው ዘመን አልፏል፣ የንጉሥ ግብርም ታሪክ ብቻ ኾኗል ተብሎ እንዳይጠፋ ጎንደር ዛሬም በአብያተ መንግሥታቱ አጸድ የንጉሥ ራት ታዘጋጃለች፤ በአንድነት እና በፍቅር ትመግባለች፡፡ በጥንት አባቶች ሲካሄድ የነበረው የግብር ማብላት ሥነ ሥርዓት በጥምቀት ሰሞን ዛሬም በጎንደር ይከናወናል፡፡

ነገሥታቱ ግብር የሚያበሉት ጮማውን እያስቆረጡ፣ ጠጁን እያስጨለጡ ለማስደሰት ብቻ አልነበረም፡፡ የሚመካከሩበት፣ ከሕዝባቸው ጋር ያላቸውን አንድነትና ግንኙነት የሚያጸኑበት፣ ታላላቆቹን ለማክበር፣ ሥራቸውን ለመዘከር፣ ከሕዝባቸው ጋር ለመገናኘት ነው እንጂ፡፡
የግብር ሥርዓት ዝም ብሎ መብልና መጠጥ የሚወጣበት አልነበረም፡፡ ታላላቅ ሃሳቦች የሚፈልቁበት፣ ሀገርን የሚያጸና ምክር የሚመከርበት፣ ምክሮች ፍሬ አፍርተው ወደ ተግባር የሚቀየሩበት አጋጣሚም ነው፡፡ በጎንደር አብያተ መንግሥታት ይደረግ የነበረው የንጉሥ ግብር ዛሬም በጎንደር የንጉሥ ራት ተብሎ ሥርዓቱ ይቀጥላል፡፡
በዓለ ጥምቀት ደርሷልና ጎንደር ለንጉሡ ራት ተዘጋጅታለች፡፡ በቀጣይ በዓለ ጥምቀትን ሳይጠብቅ ቋሚ በኾነ ሂደት የንጉሥ ራቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ዕቅድ መያዛቸውንም የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳዳሪ ጌታሁን ስዩም ነግረውኛል፡፡ በንጉሥ ራቱ ለከተማዋ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሰዎች ይመሰገኑበታል፡፡ በንጉሥ ራቱ ሥነ ሥርዓት በቀደመው ዘመን ነገሥታቱ ሲያደርጉበት እንደነበረው ይደረጋል፡፡
ጠጁ ይጣላል፡፡ ንግሥትና ንጉሡን፣ የጦር አበጋዞችን፣ መኳንንቱን፣ መሳፍንቱን፣ አዝማሪዎችን፣ ጋሻ ጃግሬዎችን፣ እልፍኝ አስከልካዮችን የሚወክሉ በንጉሥ ራቱ ይኖራሉ፡፡ ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶች የአብያተ መንግሥታቱን ታሪኮች፣ በአብያተ መንግሥቱ ውስጥ ይደረጉ የነበሩ ክዋኔዎችን ያውቃሉ፡፡ የቀደመውን ታሪክ ዛሬ ላይም በተግባር፣ እስከነ ክብሩ ያያሉ፣ ትናንትን ዛሬ ላይ ኾነው ይመለከታሉ፤ በአባቶች የቆዬ ታሪክም ይደነቃሉ፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የባሕል እሴት ኢንዱስትሪ ቡድን መሪ ልዕልና አበበ የንጉሥ ግብር አብኖነትን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ የንጉሥ ራት ነገሥታቱ ከሚመሩት ሕዝብ ጋር ምን ያክል የተቀራረቡ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡ የንጉሥ ግብር ከጥንት ጀምሮ የነበረ መሪና ተመሪን የሚያገናኝ መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ የንጉሥ ግብር ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ ዘመናትን የተሻገረ ድንቅ እሴት ነው፡፡
ነገሥታትን በዓይናቸው አይተው የማያውቁት ነገሥታትን በጎንደር አብያተ መንግሥታት ያያሉ፣ መሳፍንትና መኳንንትን የማያውቁት እነርሱን ይመለከታሉ፣ የጦር አበጋዞች ጋር ይቀመጣሉ፣ ነጋድራሶችን፣ የቤተ መንግሥት ባለሟሎችንም ያያሉ፡፡ እንዴት ከተባለ በንጉሡ ራት የቀደውምን እንደጠበቀ ይከወናልና፡፡

ግብር ሁሉም በአንድ አጸድ ሥር የሚሰባሰቡበት፣ የጋራ ማዕድ የሚጋሩበት፣ ፍቅርና ደስታቸውን የሚለዋወጡበት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሀገር የሚመክሩበትና የሚዘክሩበት ነው፡፡ ይሄም እሴት በጎንደር ይከወናል፡፡
በጎንደር ከሩቅ ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች የሚነሱ ነጋዴዎች ከባሕር ወርደው ይመጡባት ነበር። የሲራራ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን እና አጋስሶቻቸውን ጭነው ይመጣሉ። በመናገሻዋ ይከትማሉ። ወርቅ፣ ብር፣ ዝባድ፣ ቡና፣ መስታውት፣ ጌጣጌጥ፣ ነፍጥ፣ ጨው፣ ወይን፣ ዘቢብ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዋንጫ፣ ጋሻና ሌሎችን ይገበያዩባት ነበር። የሲራራ ንግድ መናኸሪያዋ፣ የስልጣኔ ቀንዲልና የኪነ ጥበብ ማህደር፣ የዘመናዊ አኗኗር ተምሳሌት፣ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የፍልስፍና መነሻ ከተማዋ ጎንደር በዚያ ዘመን ነግዶ ለማትረፍ የተመኘ ሁሉ ምድሯን ይረግጣት ነበር፡፡ ይሄን የሚያደርጉ ነጋዴዎች በንጉሡ የግብር ሥርዓት በክብር ይመጡ ነበር፡፡ ዛሬም እነርሱን የሚያስታውስ ሥርዓት በዚያች ከተማ ይካሄዳል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪ ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው አባቶቻችን ነገሥታት ሥርዓት ባለው መልኩ ግብር ያበሉ ነበር፤ በጎንደር እንግዳ ተቀባይነት ከነገሥታት የሚጀምር ነውም ብለዋል፡፡ ያባቶችን ታሪክ፣ ባሕልና ትውፊት በጠበቀ መልኩ የንጉሥ ራት ዛሬም በጎንደር ይከወናል ነው ያሉት፡፡

የንጉሥ ራቱ ሳቢና አይረሴ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የምግብ ዝግጅቱ፣ አለባበሱ፣ መስተንግዶው ሁሉም የቀደመውን ታሪክ በጠበቀ መልኩ ይኾናል ብለውኛል፡፡ የንጉሥ ራቱ ከጥምቀት በዓል ውጭ በሌሎች ጊዜያትም እንዲኖር ብዙዎች እየጠየቋቸው መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ የቀደመውን ባሕልና ታሪክ የጠበቀው እሴት በጎብኚዎች ይወዳዳል፡፡
የቀደመውን ታሪክ እስከነ ክብሩ ለማዬት፣ ከነገሥታቱ ጋር በአንድ አዳራሽ ውስጥ ለመገናኘት ወደ ጎንደር ይሂዱ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በበጌምድር ያለ ግብር በሰማይ ያለ ዱር”
Next article“ሰሜን ሸዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው” የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ