
ባሕር ዳር: ጥር 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለጀግና ተጨማሪ ስም ማውጣት፤ ለወታደር ማዕረግ መስጠት በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የተለመደ ጀብዱ ቢኾንም፤ ለአንድ አካባቢ ወታደራዊም ኾነ ዘውዳዊ ማዕረግ መስጠት ግን ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ “ራስ ጋይንት” በብዙ አካባቢዎች ባልተለመደ መልኩ የጦር ባለማዕረግ የኾነ አካባቢ ነው፡፡
ራስ ጋይንት እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት መጠናቀቅ ድረስ በጌምድር ተብሎ ይጠራ በነበረው አውራጃ ውስጥ አንዱ ክፍል ነው፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥትም በጌምድር ጎንደር ክፍለ ሀገር ተብሎ ሲሰየም የጋይንት አውራጃ ከሰባቱ የጎንደር አውራጃዎች አንዱ ኾነ፡፡ በአኹናዊው የአሥተዳደር ወሰንም ራስ ጋይንት ከአምስቱ የጎንደር ዞኖች ውስጥ አንዱ በኾነው ደቡብ ጎንደር ውስጥ ይገኛል፡፡
ዳኛው ገብሩ እና ካሳየ ዓለሙ 2010 ዓ.ም ላይ “ራስ ጋይንት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጻሕፋቸው በየዘመኑ የሚመጡ መሪዎች ለአሥተዳደር ይመቸናል በሚሉት መልኩ ቢያደራጁትም ራስ ጋይንት፤ የላይ ጋይንት፣ የታች ጋይንት፣ የስማዳ እና ሰዴ ሙጃ ወረዳዎችን የሚያካልል ነው ይሉናል፡፡ ጋይንት ለሚለው መጠሪያ ምክንያት ሁለት አፈ-ታሪኮች ቢመዘዙም ሁለቱም ግን ከሀገረ-እስራኤል ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
ጋይንት የሚለው የቦታ መጠሪያ በእስራኤልም የሚገኝ ሲኾን መልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጋይንት ጋር በብዙው ይመሳሰላል ይባላል፡፡ ጋይንት የሚለው ትርጓሜም “የጀግና ሀገር” ማለት ነው ይላሉ ጸሐፊዎቹ፡፡ ጋይንት፣ ኤፍራታ፣ ጋዛ፣ ጎልጎታ፣ ቀራኒዮ እና መሰል በእስራኤል የሚገኙ ስሞች በዚህ አካባቢም ይገኛሉ፡፡ በርካቶቹ የታሪክ ጸሐፊዎችም በዚህ መላምት ይስማማሉ፡፡
“ራስ ጋይንት” የሚለው መጠሪያ ግን መላምት ሳይኾን ታሪክ ኾኖ ዘልቋል፡፡ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንጥረኛ የነበሩት አጼ ቴዎድሮስ ጋይንትን ደጋግመው አምበሳው ጋይንት እያሉ ከመጥራት አልፈው “ራስ” የሚል ማዕረግም ሰጥተውታል፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ የጦር ባለሟል እና ቀኝ እጅ እንደኾነ የሚነገርለት ፊታውራሪ ገብርየ የተሰጠውን ማዕረግ ለአካባቢው እንዲሰጥለት ጠየቀ፡፡ ንጉሱም ጥያቄውን ተቀብለው ጋይንትን ራስ የሚል ማዕረግ ደረቡለት፡፡
በጥንታዊም ኾነ በዘመናዊው የኢትዮጵያ የሥነ-መንግሥት ታሪክ ውስጥ ራስ ጋይንቶች ሕዝብ ተበደለ ፍትህ ተጓደለ ብለው ካመኑ እስከ መጨረሻው እምቢ ማለትን ይችሉበታል፡፡ ራስ ጋይንቶች ላመኑት እውነት እስከ ቀራኒዮ ይዘልቃሉ፡፡ ለጠሉት ባርነትም ደረታቸውን ለጦር፤ እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው ይፋለማሉ፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ” በሚለው መጻሕፋቸው ከገጽ 291 እስከ 292 “በበጌምድር ያለ ግብር በሰማይ ያለ ዱር” ሲሉ አንድ ታሪክ ያጫውቱናል፡፡ የበጌምድር ሰው ሁሉ ተሰባስቦ አጼ ተክለ ጊዮርጊስን “እኛ ለምንወደው ንጉስ ሁሉ በጦር ሜዳ ታግለን፤ ዙፋኑን ደግፈን እንኖራለን እንጂ የማር እና የብር ግብር የለብንምና እርስዎም እንደ ቀደመው ሁሉ አልጋዎን ደግፈን እንኑር” ይላሉ፡፡
ነገር ግን ንጉሱ አጼ ተክለ ጊዮርጊስ በእኔ ስልጣን አሥተዳድራለሁ እንጂ እናንተ እንደምትሉት ከኾነ ምን አልጋ ኖረኝ በማለት ጥያቄያቸውን ውድቅ ያደርጉባቸዋል፡፡ የበጌምድር ሰውም ከመተማ በታች ከጨጭሆ በላይ በሁለት ቀናት ተሰባስቦ የንጉስ ተክለ ጊዮርጊስን ዙፋንን ሽሮ ራስ አሊን አስመጥቶ ሾመባቸው፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ትልቁ ራስ አሊ እስከ ዛሬም ድረስ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሰፊው ሕዝብ መልካም ፈቃድ ስልጣን የያዙ የመጀመሪያው መሪ ሳይኾኑ አይቀሩም ይሉናል፡፡ “በጌምድር ንጉስ መፍጠርም ንጉስ ማጥፋትም ይችሉበታል” የሚባለውም ለዚህ ሳይኾን አይቀርም፡፡
ዛሬ ራስ ጋይንቶች የአጼ ቴዎድሮስን 204ኛ ዓመት የልደት በዓል በነፋስ መውጫ ከተማ ሲያከብሩ እስከ ሞት የታመነውን የጦር ባለሟል እና ቀኝ እጅ ፊታውራሪ ገብርየንም ይዘክራሉ፡፡ የፊታውራሪ ገብርየ ፋውንዴሽን ይመሰረታል፡፡ ፋውንዴሽኑም የባሕል ማዕከል፣ ሃውልት እና ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ጀግናን ማውሳት እና መዘከር ተተኪ ጀግና መፍጠር ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!