
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ይዋጓል እንደ ገብርዬ፤ ይሟሯል እንደ አካልየ›› እንዳሉ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ አካልዬ ብቁ ተማሪዎችን ሊያወጣ፣ የተማሪዎችንና ወላጆቻቸውንም ስጋት ሊቀርፍ እየሠራ ነው፡፡ ለተማሪዎች የደኅንነት ስጋት እና የቤተሰብ ናፍቆት ማስታገሻ ይሆን ዘንድ ዩኒቨርሲው መላ ዘይዷል፤ የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክትን፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህርት ዘመን ከሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የመጡ 5 ሺህ ተማሪዎች ‹‹የጡት እናት›› አዘጋጅቷል፡፡
‹‹የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት›› በሚል በጎንደር ከተማ አስተዳደር እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር የተመሠረተው ይህ ፕሮጀክት ተማሪዎች በቅርብ የሚያማክሯቸው፣ ለበዓላት እና ለእረፍት ቀናት የሚጠይቋቸው እና ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋት ሳይገባቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ወላጆች ተዘጋጅተውላቸዋል፤ ለተማሪዎቹ፡፡ በሀገሪቱ ከሚስተዋለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞም የተማሪዎቹ ወላጆች በጎንደር ልጆቻቸውን ከሚቀበሏቸው ቤተሰቦች ጋር ተከታታይ ግንኙነት እንዲኖራቸውና እፎይታ እንዲሰማቸው ያግዛልም ተብሏል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይዳኙ ማንደፍሮ በተለይም ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት ‹‹የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው ከተመለሱ በኋላም ከጎንደር ሕዝብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው ያደርጋል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሮጀክቱ ለተማሪዎቹ ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው›› ያሉት ዳይሬክተሯ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ በከተማዋ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ጥምረት ቤተሰቦቹ እንደተመረጡም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት ቤተሰቦች የተማሪዎቹን ፍላጎት እና ምርጫ መሠረት አድርገው እንደሚመረጡም ወይዘሮ ይዳኙ አስታውቀዋል፤ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
በተያያዘ መረጃ ‹‹ዩኒቨርሲቲው የመምህራኑን እና ሠራተኞቹን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው›› ተብሏል፡፡ ‹‹መምህራን በተገቢው ሁኔታ የሚያስተምሩት እና የአስተዳደር ሠራተኞቹ ደንበኞቻቸውን በተገቢው ፍጥነት የሚያስተናግዱት ከሥራ ውጪ ያሉ መሠረታዊ ፋላጎቶቻቸው አቅም በፈቀደ መንገድ ሲሟሉ ነው›› ያሉት ዳይሬክተሯ ‹‹የቤት መሥሪያ ቦታ ለደረሳቸው ሠራተኞቹ በአነስተኛ ወለድ ከባንክ ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው እያመቻቸ ነው›› ብለዋል፡፡ የፋላጎት ማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነና የተገኘው ግብረ መልስም አወንታዊ መሆኑን ወይዘሮ ይዳኙ አመልክተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ900 በላይ ለሚሆኑ መምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ገንብቶ መስጠቱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በቀጣይም ከእያንዳንዱ ፕሮጀክት የሚገኘውን የአፈፃፀም ውጤት እየገመገምን ዩኒቨርሲቲውን ከሠራተኛው፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከተማሪዎቹ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስሩ ሥራዎችን ይሠራል ተብሏል፡፡
‹‹የሠላም ዩኒቨርሲቲ›› በመባል የሚታወቀው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2012 የትምህርት ዘመን ከፀጥታ ስጋት ነፃ የሆነ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር በክረምቱ ወራት ሰፊ ሥራ እንደተሠራ የገለፁት ዳይሬክተሯ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የሚያስችል የምክክር መድረክ ከጥቅምት 10 እስከ 14/2012 ዓ.ም ባሉት አምስት ቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር መካሄዱንም ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የክህሎት ስልጠና ፋይል